የገናው መልእክት


በሰሎሞን ተሰማ ጂ.   http://semnaworeq.blogspot.com   Email: solomontessemag@gmail.com


ከሁለት ሺ  ስምንት (2008) ዓመታት ገደማ በፊት፣ በይሁዳ አውራጃ ልዩ ስሙ ቤተልሔም በተባለ ሥፍራ፣ ከድንግል ማርያም አንድ ሕፃን ተወለደ፡፡ ይህም ድርጊት፣ የዓለም የታሪክ አቅጣጫ የተለወጠበት መሆኑን ሰዎች ለሃያ ክፍለ ዘመናት ያህል ተርከውታል፡፡ ፈጣሪ አምላካችን፣ በማይተረጎም ምሥጢር ሰው ሆኖ የተወለደው የዛሬ 2009 ዓመታት ገደማ ነው፡፡፡፡ በሮማውያን አምባገነኖች ትእዛዝም፣ እንደ አደገኛ ወንበዴዎች በመስቀል ላይ ተቸንክሮ እንዲሞት ሆነ፡፡ ከዚያም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው የሞትን ግዛት ድል እንደነሣና፣ በትምህርቱም ዘላለማዊ ደኅንነትን እንደገለጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ስለዚህም፣ በየዓመቱ - በገና ዳቦ፣ በመዝሙርና በዝማሬ፣ በገና ጨዋታ፣ በድግስና በደስታ፣ እንዲሁም በእልልታ - ተከታዮቹ ሁሉ የቤተልሔም በረት ውስጥ የተወለደውን ሕፃን ልጅ ታሪክ ይጫወታሉ፤ ያወጋሉም፡፡ ይኼ መቼም ካመት ዓመት የማይጠገብ ታሪክ (story) ነው፡፡ የልደት በዓል-ያለፈ ታሪክ ትውስታም ብቻ አይደለም፡፡ የወደፊቱንም ዘላለማዊ ተስፋ መግለጫም ጭምር ነው፡፡ “ሰላም በምድር ትሁን፣ በሰዎችም መካከል በጎ ፈቃድ ሁሉ ይሁን!” ሲሉ መላእክትም ከአርያም ዘምረዋልና፣ የገና በዓል ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ ክርስቶስም፤ “እኔ፣ እስከ ዘመናት ፍፃሜ ድረስ ከናንታ ጋር ነኝ፤” ብሏልና በዓሉ ዘላለማዊ ተስፋም ነው፡፡ 

ዛሬ በዓለማችን ላይ ከሦስት ቢሊዮን በላይ ክርስቲያኖች እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ ሆኖም፣ የገና በዓል መንፈሥ የክርስቲያኖች ብቻ አይደለም፡፡ በወንድማማችነት፣ በፍቅርና እርስ-በርስ በመዋደድ ላይ የተመሠረው የክርስቶስ ትምህርት ዋና ዓላማው፣ ሁሉንም ሃይማኖቶች የሚያጠቃልልና ዓለም አቀፋዊ እሴትም ነው፡፡ ጉልሁ ጥያቄ ታዲያ፣ “ዓለማችን ታዲያ፣ ወደክርስቶስ መልእክት ምንያህል ተቃርባለች?” የሚለው ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ዓመት አልፎ ዓመት ቢተካም ለሕሊናችን የሚቀርብ ዘላለማዊ ጥያቄ ነው፡፡ ዘንድሮም ታዲያ ይህንኑ ጥያቄ መልሰን ብናነሳው የሚያጽናና መልስ አናገኝም፡፡ እርግጥ ነው ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ገና አልተነሣም፡፡ ደግሞም ግን፣ በሰው ልጆች መካከል ዘላቂ ሰላም ገና አልተመሠረት፡፡ በመካከለኛው አፍሪካ፣ በተለይም-በዛየር፣ በቡሩንዲ፣ በኮንጎ ብራዛቪል ሠላም ደፍርሷል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካም የፀደዩ የአረብ አብዮት ጣጣ-ፈንጣ ገና አላበቃም፡ ንፍፊቱና መገረኑ፣ ከሊቢያና ከሶሪያም አልፎ የመንን ዶግ-አመድ አድርጓታል፡፡ እንዲያውም ስድስት ገናዎችን አስቆጥሯል፡፡ መቼም የአፍጋኒስታንና የኢራቅ ውጥንቅጥ ወደአስራ ስድስት ገናዎች ሊሆኑት ነው፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ፣ የአይ.ኤስ.አይ.ኤስና የታሊባንም ክንዶች የመፈርጠም ምልክት አሳይተዋል፡፡ በቅርባችን በሶማልያም የርስ-በርስ ገጭቱና አለመረጋጋቱ ሃያ-ስምንተኛ ገናውን አስቆጥሯል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውም መፋጠጥ የኼው አስራ ስምንተኛ ገናውን ሊደፍን ወራት ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡  

የበለፀጉት አገሮች/ኃያላኑም በኤኮኖሚ (በነገረ-ነዋይ) ቀውስ ውስጥ ከተዘፈቁ እነሆ ዘጠኝ ገናዎች ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም፣ በግሪክ፣ በስፔንና በፖርቹጋል እንደምናየው ከሆነ፣ ችግሩ ከመሻሻል ይልቅ እጅግ ስለተባባሰ፣ ብዙዎች የገና ካርድ እንኳን ለመግዣ የሚሆናቸውን “ማህለቅ” ማግኘት ተስኗቸዋል፡፡ ነገር ግን፣ ብዙ ሃገሮች የጦር መሣሪያና ትጥቅ አሁንም ያከማቻሉ፡፡ የለየለት የጦርነት ሥጋት እየገነነ ኼዷል፡፡ የአልቃይዳና የእህት አሸባሪ ድርጅቶቹ ስጋት መኻል ፓሪስም አደባባዮች ላይ ተደጋግሞ ተከስቷል፡፡ ከሰሞኑ ያየነው የትምህርት ቤት ጥቃት የአደጋው ደንበኛ ማሳያ ነው፡፡ በሊቢያ፣ ሶርያ፣ በየመንና በኢራቅ ያለው የአልቃይዳ አልሞት-ባይ ተጋዳይነት ተባብሷል፡፡ በቅርባችንም የሶማሊያ ሁኔታ “ከድጡ-ወደ-ማጡ” እንደሚባለው ሆኗል፤ አልሸባብ፣ አልሂዝቡል፣ አልመንጁስ፣ አልነጂስ፣…..ወዘተርፈ በሚባሉ ጎሰኛና ነውጠኛ ቡድኖች ደቡብ ሶማሊያ እየራደች ነው፡፡

ይህም ሁሉ ስለተባለ፣ የዘንድሮውን ገና ካለፉት ገናዎች የተለየ ግምት የሚያሰጠው አንድ ግዙፍ ቁምነገር አለ፤ እርሱም፣ በአብያተ-ክርስቲያናት መካከል የተጀመረው አዲስ የመሻሻልና የመቀራረብ መንፈስ እጎለበተ የመኼዱ ተስፋ ነው፡፡ በተለይም በምስራቅ አብያተ-ክርስቲያናት በኩል ያለው መቀራረብ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ለዚህ ደሞ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ-ጳጳስና ባልደረቦቻቸው ከፍተኛ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡ ክርስቶስ አንድ ቤተ-ክርስቲያን ብቻ መሠረተ፤ አንዲቷ ቤተ-ክርስቲያንም ተከፋፍላ፣ ብዙ አብያተ-ክርስቲያናት ተፈጠሩ፡፡ ይባስ ብሎም ችግሩ በቤተ-ክርስቲያን መሪዎች መካከል ተካሮ ሄደና በርካታ ፓትረያርኮች፣ በርካታም ሲኖዶሶችና በርካታም ጎራዎች እስከመፍጠር ደርሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁለት ፓትረያርኮች፣ ሁለት ሲኖዶሶች፣ በሁለት ጎራም የሚተሙ አማኒዎች ከተከሰቱ ሃያ አራት ገናዎች ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ገናም፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን ሕመም ፈውሶ ለቤተክርስቲያኗ አንድነትን፣ ለመሪዎቹም መከባበርንና ፍቅርን፣ ለምዕመናኑም እድገትንና ብልጽግናን ይሰጥልን ዘንድ እንመኛለን፡፡ መከፋፈል ማንንም በምንም ኹናቴ ሊያፀና አይችልምና፡፡

የቤተ ክርስቲያን ባለቤት -ክርስቶስ ራሱ እንዳለው፣ “እርስ በርሱ የተከፋፈለ ቤት ሊፀና አይቸልም፡፡” አብያተ ክርስቲያነትም በዚህ ዓብይ የሆነ የገና መንፈሥ ወደኋላ ተመልሰው፣ በበረት የተወለደውን፣ የትሑቱን መምህር ትምህርት ቢያስታውሱትና ከሚለያዩበት ይልቅ የሚገናኙበት መብዛቱን ሊገነዘቡ እንደሚገባቸው ለማውሳት እሻለሁ፡፡ ለሰው ልጆች ታላቁ መተሣሠሪያ ኃይላቸው-“በጎ ፈቃድ” ነው፡፡ በዚህ የገና መልእክታችንም፣ በሁሉም ሕሊና ውስጥ “በጎ ፈቃድ በሰው ልጆች ሁሉ መካከል ይሁን!” የሚለውን የመላእክት ዝማሬ፣ በቤተ ክርስቲያንና በቤተ መንግሥትም መሪዎች፣ በገዢዎችና በተገዢዎች፣ በመሪዎችና በተመሪዎችም መካከል በመላው ዓለምና በኢትዮጵያም ሕዝብ ልቦና ውስጥ እንዲያሠርፅ በእጅጉ እንመኛለን፡፡ (አሜን!)

አስተያየቶች

አስተያየት ይለጥፉ

Thanks a lot for your comments.