“እኛና አብዮቱ” –
“የጓድ ፍቅረ ሥላሴ ውዳሴ ከንቱ!”
ትናንት ታኅሣስ 02/2013 ዓ.ም ጓደኛዬን ጥየቃ ወደፈረንሳይ
ሌጋሲዮን አካባቢ ብቅ ብዬ ነበር፡፡ ሻይ ቡና ካቀረበልኝ በኋላ አንድ ቆየት ያለ መጽሔት አሳየኝ፡፡ መጽሔቱም አዲስ ጉዳይ ነበር፡፡
እዚያም ላይ ታትሞ የነበረውን የመጽሐፍ ግምገማ ትችት ተመለከትኩት፡፡ እኔም ሆንኩ ጓደኛዬ የሟቹን የደርግ ዘመን ጠ/ሚ/ር ፍቅረ
ሥላሴ ሞት አልሰማንም፡፡ ለማንኛውም፣ ጥራትም ባይኖረው የመጽሔቱን ሽፋን ፎቶ አንስቼዋለሁ፤ ብታዩት ለማመሳከሪያም ያህል ይረዳችሁ
ይሆናል፡፡ … ጽሑፉ/ሐቲቱ የተጻፈው የዛሬ ሰባት ዓመት ከስምንት ወር ገደማ ነው፡፡ በመጋቢት 8/2006 ዓ.ም ነበር ታትሞ
የወጣው፡፡ ጽሑፉ፣…የዚያን ጊዜውን ሰሎሞን አተያይም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ አሁን ላይ በብዙ መልኩ የተለወጥኩ ያህል ይሰማኛልና
ነው፡፡ ማለትም፣ ፈረንጆቹ “Critical Ditance” የሚሉትን ጽንሰ-ሃሳብ (ዘይቤ) አሁን ላይ አለኝ ለማለት ነው፡፡ ለማንኛውም፣
…መልካም ንባብ እመኛለሁ፡፡
0. መንደርደሪያ፤
1. መግቢያ፤
ስለጓድ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኩትም ሆነ ያነበብኩት
በ1976/7 ዓ.ም ነው፡፡ በጊዜው ገና የስድስት ዓመት ታዳጊ ነበርኩ፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ይሠራ የነበረው አባቴ
አንድ ጋዜጣ ይዞ ወደቤት መጣ፡፡ በቀይ የተንቦገቦገ ቀለም የተጻፈው የጋዜጣውም ርእስ “ሠርቶ አደር” የሚል ነበር፡፡ ይህንን ጋዜጣ እድሜ ልኬን
የማልረሳው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰበብ ስለጋዜጣና ስለጋዜጠኝነት የተወሰነ መረጃ ያገኘሁበት ዕለት ስለነበረ
ነው፡፡ ሁለተኛው አጋጣሚ ደግሞ በጋዜጣው የፊት ገጽ ላይ የወጡትን የኢሠፓ ግንባር ቀደም መሪዎች ፎቶም ያወቅኩበት ጊዜ ነው፡፡
ቀደም ብዬ በየሬዲዮው ዜና እወጃና ሃተታ ወቅት ስማቸውን ደጋግሜ እሰማቸው የነበሩት ከፍተኛ ሹማምንት መልክ ለመጀመሪያ ጊዜ
በጋዜጣው ላይ አየሁት፡፡ የጓድ መንግሥቱን ቆጣ ያለ ፊት፣ የጓድ ፍስሐ ደስታ አምታች ገጽታ፣ የጓድ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ
ጭንቅላት ላይ በስተቀኝ በኩል የምትንቦገቦገውን ሽበት በደንብ አድርጌ አስተዋልኩኝ፡፡ ከዚያን ቀንም ጀምሮ ስለነዚህና ስለሌሎች
ባልደረቦቻቸው በየመገናኛ ብዙኃኑና ላይ ይወጡ የነበሩትን ሃተታዎች ያለማሰለስ እከታተል ነበር፡፡ (አብሮ አደጎቼ በብዛት
“ሠርቶ አደር”፣ “የካቲት” እና “ታጠቅ” እያሉም ነበር የሚጠሩኝ፡፡)
ከዓመታት በኋላ፣ በግንቦት 1983ዓ.ም እንደዚያ ከፍ አድርጌ አያቸው የነበሩት
“ጎበዞች”፣ “እጅ ወደላይ!” ተብለው ወደዘብጥያ ሲወርዱ በአዲስ ዘመን ጋዜጣና በቴሌቪዥን መስኮት ላይ የተመለከትኳቸው ጊዜ
በእጅጉ ተደናግጬ ነበር፡፡ እነዚያ ቀንና ሌት ስለጽርዓ-አርያምነታቸው ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ፣ ጋዜጣና መጽሔቱ ሲሰብክላቸው የነበሩት
ሰዎች፣ “ፎጣ በትከሻ!” ተብለው ዘብጥያ ይወርዳሉ የሚል ቅንጣት ታክል ግምት አልነበረኝም፡፡ ሆኖም ግን ሆነ፡፡ ሌላው
ያሳስበኝ ነበረው ነጥብ፣ “አሸናፊዎቹ ጓዶች በምን አንቀጽና ቁጥር ይከሷቸው ይሆን?” የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ ጉዳያቸው
ለዓመታት ሲንከባለል ከቆየ በኋላም “በዘር ማጥፋት” ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት መመላለስ ጀመሩ፡፡ መጀመሪያ ላይ ለመቀበል
አዳግጾኝ ነበር፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎች በፍፁም የሰውን ዘር እንደሒትለርና እንደግብረ-አበሮቹ ለማጥፋት አልተነሱም የሚልም
አቋም ነበረኝ፡፡
ነገር ግን፣ በአቶ ግርማ ዋቅጂራ (በም/ል ሚኒስትር ማዕረግ) ይመራ የነበረው
የፌዴራል አቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ተቋቁሞ ክሶቹን ማሰማት ሲጀምር፣ እነዚያ “ቅዱሳን” ይመስሉኝ የነበሩት ሰዎች፣ የሌሎች
ሰዎችን ሰብዓዊ ክብር እየገፈፉ፣ “ፀረ-አብዮተኛ”፣ “አድኃሪና የቀኝ-መንገደኛ” እያሉ ሰዎችን መፍጀታቸውን መረዳት ጀመርኩ፡፡
በ1948ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረትም፣ “የትኛውንም ቡድን፣ ወይም የፖለቲካ ማኅበር፣ ወይም የሃይማኖት
ተከታይ፣ ወይም የርዮተ-ዓለም አቀንቃኝ” በያዘው አቋም ምክንያት ከተደበደበ፣ ከታሰረ፣ ወይም ከተገደለ እንደ “ዘር ማጥፋት
ወንጀል” መቆጠሩን ተረዳሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን የአቃቤ ሕግ የክስም ሂደት በተቻለኝ መጠን ለመከታተል ጥረት አድርጌያለሁ፡፡
ከዓመታት በኋላም ተፈረደባቸው፡፡ የፍርድ ቤቱ የግራ-ቀኝ ክርክር ምን ያህል ፍትሐዊ እንደነበርና እንዳልነበር ማረጋገጫ
የለኝም፡፡ ሆኖም ግን፣ እያንዳንዳደው የእድሜ ልክ እስራትና ጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ደግሞ በሌሉበት የሞት ቅጣት
ተፈረደባቸው፡፡ ሆኖም፣ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ሰው የመጨረሻ የእስራት ጣራው ሃያ-አምስት
ዓመታት ብቻ ስለሆነ፣ እነዚህ ባለስልጣናትም ሃያ ዓመታት ከታሰሩ በኋላ አምስቱ ዓመታት በአመክሮ ተቀንሰውላቸው ተፈቱ፡፡
መንግሥትም ለወንጀለኞቹ ?“ምህረት አደረኩላቸው!” ሲል የፖለቲካ ትርፍ ሊሸምትባቸው ተጣጣረ፡፡ ይህ አካሄድም ጉንጭ አልፋና
“ዶሮን ሲያታልሏት፣….” የሚባል ዓይነት ነበር፡፡
2. የመጽሐፉ
ግምገማ፤
ወደዋናው ጉዳያችን እንመለስና፣ የጓድ ፍቅረ ሥላሴን መጽሐፍ ከአንድ ወዳጄ ተውሼ
አነበብኩት፡፡ መጽሐፉን ሳነብ አገኛቸዋለሁ ብዬ የምጠብቃቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ነበሩኝ፡፡ እነርሱም፣ ጸሐፊው የመጽሐፋቸው ርእስ
ያደረጓቸውን ሁለት ሃሳቦች በፈርጅ-በፈርጁ አደራጅተው ያቀርቡልናል በሚል ግምት ነበር፡፡ እነዚህም ቃላት፣ “እኛ” እና “አብዮቱ” የተባሉት ናቸው፡፡ ጸሐፊው “እኛ” ሲሉ፣ ደርግ በተባለው የወታደሮች ኮሚቴ እና “አብዮቱ” ሲሉ
ደግሞ በየካቲት 11/1966ዓ.ም የተለኮሰውን ችቦ ማለታቸው እንደሆነ ነበር የተገነዘብኩት፡፡ ነገር ግን፣ ደራሲው የተነሱለትን
ዋነኛ አላማ ዘንግተው፣ እራሳቸውንና አዛዥና-ናዛዥ ሆነው ያገለግሉበት የነበረውን ሥርዓት ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡
ጸሐፊው ከኅዳር 1967ዓ.ም (60ዎቹን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናትና የደርጉ ሊ/መንበር አድርገው የሾሟቸውን ሌ/ጄኔራል
አማን አምዶምን፣ የጄነራል ተፈሪ በንቲን፣ የሻምበል ሞገስ ወልደሚካኤልና መቶ አለቃ አለማየሁ ሀይሌን እንዲሁም ሌሎችን በደርጉ ውሳኔና በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ትዕዛዝና ዋና ፈፃሚነት የተከናወነውን የግፍ አገዳደል “ድራማ”/ጭካኔ ይተርኩልናል፡፡ ነገር ግን ያንኑ ያረጀና ያፈጀ
የደርግ ዘመን የማስተባበል ፕሮፓጋንዳቸውን በሚያስታውስ መልኩ እንዲህ ይላሉ።
“የኢህአፓ መሪዎች (የ)ፖለቲካ…..ስልጣን ለመያዝ ይቻላል ብለው በቀየሱት ከጀብደኝነት የመነጨ ስልት ምክንያት የደርግ አባላትን ለእሳት ዳረጉ” ይሉናል(ገጽ 127)። ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ተከስተው የነበሩትን ችግሮች ሁሉ አንዴ ለሻዕቢያና ወያኔ፣
ሌላ ጊዜ ደግሞ ለውጭ መንግሥታትና የስለላ ተቋማት እየሰፈሩ ሊሰጡ ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ በሌላም በኩል፣ የነበረው ስርዓትና
የገዢዎቹ መላ-ቅጥ ያጣ ጭቆና አስመርሯቸው የተሰደዱትን ወገኖች በሙሉ በሲ.አይ.ኤ እና በምዕራባውያን የስለላ ተቋማጽ ላይ
ሲያላክኩ ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህም ጥሩ ማስረጃ የሚሆነው በገጽ-440 ላይ የቀረበው ሃተታ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፣ “የኛን መንግስት ለማዳከም ታዋቂና የተማሩ ግለሰቦችን ጠላቶቻችን አስከድተዋል። የአሜሪካ መንግሥት የስለላ ድርጅት (ሲ አይ ኤ) ከፍተኛ በጀት በመመደብ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን፣ ታዋቂ ስፖርተኞችን በብዛት አስኮብልሏል።” እያሉ ይከሳሉ፡፡ በደርግ ዘመን
የነበረውን ያንን ሁሉ መፈናቀልና ስደት በራሳቸው እይታ ብቻ (ወደውጪ ብቻ) ስለሚመለከቱትም መዘንጋት ያልነበረባቸውን ግዙፍ
ጭብጦች በሾርኔ አለፏቸው፡፡ ለምሳሌ፣ የጎንደርና የሐረር ልጆች ለምን ወደ ሱዳንና ጅቡቲ ያለማቋረጥ ይሰደዱ እንደነበር
ትንፍሽም ሳይሉ ቀሩ፡፡ የነበረውን ውስጣዊ የኢኮኖሚ ፍልሰትና የመንደር ምስረታ (የሠፈራ መርሃ-ግብር) ጉዳይም በቸለልታ
ዘለሉት፡፡ በወቅቱ ግን ገበሬው፣ “ዘመን ሰባ-ሰባት የሰራኸኝ ሥራ፤ በሬዬን ለካራ፣ እኔንም ለሠፈራ!” እያለ ነበር የሚያንጎራጉረው፡፡
“እኛ” እያሉ የሚጠሩት እርሳቸውና ሌሎች “የአብዮቱ ልጆች” ደግሞ ከሞስኮ የመጣ ቮድካና ውስኪ እየኮመኮሙ ነበር፡፡ ይህ አያዎ
ግን አንድም ቦታ ላይ ሲወሳ አላየንም፡፡
የጓድ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ወግ ይቀጥላል፡፡ በቀጠለ ቁጥር ግን የበለጠ ጎምዛዛ፣
እጅግም መራራ እየሆነ ነው የሚሄደው፡፡ “ማላከክ፣ መወንጀልና መፈረጅ” ጸሐፊው ታጥቀው የተነሡላቸው ኹነኛ አቋሞች እስከሚመስሉ
ድረስ፣ እግረ-መንገዳቸውን ያገኙትን ግለሰብ፣ የፖለቲካ ማኅበር ወይም ድርጅት ሁሉ ይወነጅሉታል፡፡ ከውንጀላቸውም በፊት
አስተካክለውና አስተማምነው ሊፈርጁት ይጥራሉ፡፡ በመጨረሻም፣ ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ተጠያቂነቱንና እርግማኑን ያ የተፈረጀ
አካል እንዲሸከመው ያደርጋሉ፡፡ ይህ አቋም በሚደንቅ መልኩ በጓድ ፍቅረ ሥላሴ መጽሐፍ ውስጥ ይንጸባረቃል፡፡ ከእድሜው ላይ ሃያ
አንድ ዓመታትን ያህል በከርቸሌ(ሸቤ) ቆይቶ ከወጣ አደገኛ ወንጀለኛ እንኳን በማይሞክረው ስህተት ውስጥ ገቡ፡፡ ለምሳሌ ከገጽ 275 – 296 ድረስ ያሉት
ሃተታዎች ለዚህ የውንጀላ፣ የማላከክና የመፈረጅ አካሄድ በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ጓዱ ሌላም ባሕሪያቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ ይኼንን ባህሪያቸውን
ገስጥ ተጫኔ በጻፈው “ነበር” መጽሐፍ ላይ ሳነበው ለማመንም ሆነ ለመቀበል አዳግቶኝ ነበር፡፡ እንደገስጥ ተጫኔ ገለፃ ከሆነ፣
ጓድ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ማለት ወጪት ሰባሪ ናቸው፡፡ ለዚህ የገስጥ ሃቲት ተገቢ የሆነ መገለጫ በገጽ-226 ላይ ማመሳከር
ይቻላል፡፡ ፍቅረ ሥላሴ እንዲህ ይላሉ፤ “ገበሬው ንቃቱ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ የመንግስትን አወቃቀርና አሰራር ማወቅ ቀርቶ የሚኖርበትን አካባቢ እንኩዋን እንዴት እንደሚተዳደር ለይቶ ለማወቅ ችሎታ የሌለው መደብ ነበር” ይሉናል። ጓድ ፍቅረ ሥላሴ ምነው ረሱት? ያኔ (በ1970/71 ዓ.ም)
የመላ ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማኅበርን በእርሶና በጓድ መንግሥቱ ቀጭን ትዕዛዝ ሲፀነስና ሲወለድ ምን እንደሉ ዘነጉት እንዴ?
“ያለጭቁኑ ገበሬ አብዮታዊ ትግል የምርቱ ዘመቻ ግቡን አይመታም?” እያሉ ግራ እጅዎትን ሽቅብ ወደሰማይ ሲያወጡ አልነበረምን?
እንዴት ይረሳል?! ሌላም ቦታ ላይ ተመሳሳይ ገለፃ አድርገዋል፡፡ እርሱም፣ ስለፋብሪካ “ወዝ-አደሮች” አድማና የምርቱን ዘመቻ
የማደናቀፍ ተልዕኳቸው በተመለከተ በገጽ-253 “በተለያዩ የተንኮል ዘዴዎች የማምረቻ መሳሪያዎች በማበላሸት ወይም በማቃጠል የምርት እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ፤” ያደርጉ ነበር ሲሉ ይስተዋላል፡፡ ይህ ዓይነቱ በአንድ ሰይፍ
ሁለት ስለት ዓይነት አመካከት ነው፡፡ ወዛደሮቹ፣ የኢህአፓ ወኪሎች ነበሩ ብሎ ለመወንጀልና ለመግደልም ያወቻል፡፡ ደግሞም
ተደርጓል፡፡ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ወዛደሮች በምን ንክኪ እንደተገደሉና እንዳስገደሏቸውም ቅልጥጥ
አድርገው ነገሩን፡፡ (በእግዚአብሔር/በአላህ ቢያምኑም-ባያምኑም፣ አንድዬ ይባርክዎት፡፡)
ሁለተኛው የጓድ ፍቅረ ሥላሴ ወጪት ሰባሪነት የተንፀባረቀበት
ሃተታ ደግሞ በገጽ-226 ላይ ያለው ነው፡፡ እንዲህ ይላል “ተማሪዎች የስራም ሆነ የኑሮ ልምድ የላቸውም። ቤተሰብ ማስተዳደር እንኩዋን በቅጡ አያውቁም። . . . . . . . መንግስት ስልጣን ውስጥ ተካፋይ መሆን አለባቸው የሚል ሀሳብ ማቅረብ ከግዴለሽነት ወይም ግራ ከመጋባት የመነጨ ይመስላል” ይላሉ። የሚገርም ነው፡፡ ታዲያን ለምን የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር (አ.ኢ.ወ.ማ) እንዲቋቋም አመራር ሰጡ?
ለብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት የሚታፈሱትን የሚጠቁሙ፣“አስተኳሾችን” ነበር እንዴ ስታደራጁ የነበራችሁት? ገዋድ ፍቅረ ሥላሴ
አንዳችም ጥቆማ አልሰጡንም፡፡
ጓዱ ሌላም ስህተት
ላይ ወድቀዋል፡፡ መጀመሪያ ላይ እንኳን የቃላትና ሃረጋትን በተገቢው ኹኔታ የማሳካት ችግር አድርጌ ነበር የወሰድኩት፡፡ ነገር
ግን ስለወጣቶቹና ስለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያተቷቸውን ሳይ አንዳች ትርጓሜ አገኘሁበት፡፡ ስለወጣቶቹ አቅምና ክህሎት ችግር ሲጽፉ፣
“ብረትን እንደጋለ ነው ማዝበጥ!” የሚለውንም ተረትና ምሳሌ ዘንግተውት ነበር፡፡ እርሳቸውና አንድ መቶ ሃያ ምናምኑ የወታደራዊ
ኮሚቴ አባላት ተጠራርተው የመጡት ወጣቶቹ ኢትዮጵያውያን በለኮሱት ህዝባዊ ፋና-ብርሃን እንደሆነም ችላ ብለውታል፡፡ ከዚህም
ሌላ፣ “ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን አደራ ተረካቢ ነው!” እያሉ ያሰሙት የነበረውን መፈክርና ተስፋም ባዶነት ጠቁመዋል፡፡ ያንን
ችቦ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት ያቀጣጠሉትን ለኳሾችም ሁሉ ከፖለቲካው መድረክ አሽቀንጥሮ ለመጥረግ እንዲያመቻቸው ሲፈልጉ
አንዱን መኢሶን፣ ሌላውን ደግሞ ኢህአፓ እያሉ ይፈርጁታል፡፡ ከዚያም በኋላ እንዴት አድርገው እንደልባቸው ሊያስሯቸው፣
ሊገሏቸውና ሊያጉሯቸውም እንደቻሉ ይነግሩናል፡፡ ለአብነትም ያህል እነዚህ ዐ.ነገሮች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ “የመኢሶን መሪዎች ከኮበለሉ ብኋላ በርካታ አባሎቻቸው ላይ የመጉላላት ፣ የመታሰርና ከሥራ መባረር ብሎም የመገደል አደጋ ደርሶባቸዋል። ይህ የመኢሶን የስልጣን ጉጉትና የአመራር ድክመት ውጤት መሆኑ ነው።” (“እኛና አብዮቱ” ገጽ-342 ላይ ይመልከቱ፡፡) ልብ በሉ፣ ለጓድ ፍቅረ ሥላሴ
ወግደረስ “….መታሰርና ከሥራ መባረር ብሎም የመገደል፣” የሚባሉት ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች
በመኢሶን መሪዎች ኩብለላ ምክንያት የተከሰቱ “አደጋ”ዎች
ናቸው፡፡ ምን ዓይነት አማርኛ ነው? (ይህንን የመሰለ እጅግ የሚገርም መመጻደቅ ለምን ሊጠቀሙት እንደፈለጉም ግራ ያጋባል፡፡
ጥቂት ገፆች አለፍ ብለው በገጽ-364 ላይ ደግሞ ኢህአፓ
የተባለውን የፖለቲካ ማኅበርና አባላት ይወነጅላሉ፡፡ “የኢትዮጵያ ጦር የያዘውን ቦታ እየለቀቀ እንዲያፈገፍግ የተደረገው በሶማሊያ ጥንካሬና ግፊት ብቻ ሳይሆን በጦሩ ውስጥ የተሰገሰጉት የኢህአፓ አባላት ጦሩን በማሸበራቸውና እንዲሸሽ ቅስቀሳ በማካሄዳቸው ጭምር ነው። ……………… የኢህአፓ አባላት በጦሩ ውስጥ ሽብር ነዙ።….. ከዚህም አልፈው በግርግርና በተኩስ መሀል መሪዎችን ከጀርባቸው እየተኮሱ ገደሉ፡፡” የሚያስደነግጥ ነው፡፡
በ1970ዎቹና 80ዎቹ ውስጥ የበርካታ ወጣቶችን ዐይንና ልብ መሳብ ችሎ የነበረውን ፓርቲ (ኢህአፓን) በካልቾ ብለው ሊያስወጡት
ሞከሩ፡፡ ሙከራቸውንም ደግሞ በ1969/70ዓ.ም ተደርጎ የነበረውንና የብዙ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት የጠየቀውን
የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ያልተጠበቀ ሽንፈት በፓርቲው ላይ ለማላከክ ጣሩ፡፡ ይህ መቼም አደገኛ አካኄድ ነው፡፡ ሆኖም ግን
ለውንጀላቸው ማጠናከሪያ የሚሆን አንዳችም ማስረጃ ሳያቀርቡ ሹልክ ብለው ያመልጣሉ፡፡
እዚህ ላይ አንዳንድ ጥያቄዎችን ማንሳትም የተገባ ነው፡፡
“ለመሆኑ እርሶና እኛ ያሏቸው የሥራ ባልደረቦቻችሁ፣ ስንቶቹን የህዝባዊ ሠራዊትና የወታደራዊ መኮንኖች፣ የአድኃሪው የዚያድ ባሬ
ሰላዮች ናችሁ፤ ሰርጎ-ገቦች ናችሁ፤ ወይም ደግሞ አድኃሪያን ኃይሎች ናችሁ እያላችሁ አስገዳችኋቸው?” “ስንቶቹንስ በሱማሊያ
እስር ቤቶች ውስጥ በግፍ ሲገደሉና ሲሰቃዩ ሰምታችሁ እንዳልሰማችኁ ሆናችሁ?” “ስንቶቹስ፣ ናላቸው ዞሮ በየጎዳናውና በየመንገዱ
ላይ ጭቃ እያቦኩ ቂጣ እንዲጋግሩ አደረጋችኋቸው?” (መጽሐፍዎትን በድጋሚ ሲያርሙና ሲያስተካክሉ ሊመረምሩና ሊያስተካክሏቸው
ከሚገቡት ጥያቄዎች መካከል ናቸው፡፡) በተለይም ደግሞ፣ እንደቀሽም አቃቤ ሕግ፣ ሳር-ቅጡን ሁሉ በወንጀልና በጥርጣሬ ከመፈረጅ
ተቆጥበው ተገቢነት ያላቸውን ሰነዶችና ማስረጃዎች እያጣቀሱ ቢጽፉም መልካም ነው፡፡ የጓድ ፍቅረ ሥላሴን መጽሐፍ በእጅጉ የመታው
ምች የመጀመሪያ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ማጣቀሻ ዋቢዎችንና ማጣቀሻዎችን አለማካተቱ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ የፖለቲካ ቀመስ
ታሪኮችን አጻጻፍና አዘገጃጀት የሚችል ሙያተኛ አግኝተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ መልካም መጽሐፍ ማዘጋጀት ይችሉ እንደነበረ መገመት
አያቅትም፡፡ ነገር ግን፣ የቀድሞ አለቃቸውን፣ የጓድ መንግሥቱን መጽሐፍ (“ትግላችን”ን እንደልከኛ መነሻ አድርገው በመውሰዳቸው
ከፍተኛ ዳፋ ገጠማቸው፡፡ መጽሐፋቸውንም አዳፋ አደረገባቸው፡፡) አንድ አብነት ጠቅሼ ላጠቃልለው እወዳለሁ፡፡ ቀድሞ አዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ውስጥ ይሠራ የነበረው አቶ ብርሃኑ ደቦጭ የመረጃ አቀራረቡንና የማጣቀሻ የግርጌ ማስታወሳቹን ከደራሲው ከአቶ
ብርሃኑ አስረስ ጋር ሆኖ ባያስተካክለው ኖሮ፣ “ማን ይናገር
የነበረ፣….የታኅሣሡ ግርግርና መዘዙ?” አሁን የያዘውን ቅርጽና ይዘት አይኖረውም ነበር፡፡ (በየትም ቦታና በየትም ጊዜ
ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ ፀሐይ ፐብሊሸርም ተገቢውን ባለሙያ በተገቢው ሰዓትና ቦታ የመጠቀም ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡)
ማጠቃለያ፤
በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት አብዛኛዎቹ ሃተታዎች የጓድ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ነጻ እይታዎች ናቸው። አቶ ፍቃደ ሸዋቀና እንዳሉት “ትልልቅ ድምዳሜዎች ላይ የደረሱባቸውን ነጥቦችና በፖለቲካ ባላንጦቻቸው ላይ የሚያቀርቡትን ክስ ተዓማኒ የሚያደርግ ወይም የሚያረጋግጥ ወይም ደርግን ከክስ የሚያነፁበት ማስረጃ የሚሆን የግረጌ ማስታወሻም (Footnote) የዋቢ ዝርዘርም (Reference list) የለበትም።” ከዚያ ይልቅ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምን ገድል እና በርካታ የደርግ ባለሥልጣናት ላይ ይቀርቡ የነበሩትን ወንጀሎችና ጥፋቶች ሁሉ የተገቢነት የማረጋገጥ (justify) የማድረግ ሥራ ሢሰሩ ይታያሉ፡፡ ይህም አካሄድ
ወድቆ የቆመውን ሽቅብ እንደመጎተት ያህል ነው፡፡ ማንንም፣ ምንም አያስተምርም፡፡ ስለሆነም፣ ከውንጀላ. ከማላከክና ከፍረጃ
የነፃ ሥራ ደግመው ሊሠሩ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ በመጽሐፋቸው ውስጥ የማኅበራዊ ሳይንስና የሥነ-ምግባር ትንታኔያቸውን
ተወት አድርገውት፣ አንኳር-አንኳር በሆኑት የአብየቱ ሂደቶች ላይ ቢያተኩሩ የተሻለ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ በአንድ ርዕሰ-ጉዳይ
ላይ በርካታ ተያያዥ ክስተቶችን ለማስታወስ ይረዳቸው ዘንድ፣ የሌሎቹንም ጓደኞቻቻንና የሥራ ባልደረቦቻቸውንም ትውስታ ቢጠቀሙ
ሳይሻል አይቀርም፡፡ እኛ ባለን ንባብና መረጃ መሠረት፣ ጓድ ፍቅረ ሥላሴ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ማጠናቀር ችግሮችን በመጽሐፋቸው
ውስጥ አንፀባርቋል፡፡ በቅን ልቦና ቢያስተካክሏቸው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለታሪክና የፖለቲካ ተመራማሪዎች እንደሚያበረክቱ መዘንጋት
የለበትም፡፡ (በቸር ይግጠመን!)
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ
Thanks a lot for your comments.