የአፍሪካ ኅብረት መሠረት!



(የቀ.ኃ.ሥ አባታዊ ተሰሚነት!)


በሰሎሞን ተሰማ ጂ. semnaworeq.blogspot.com     Email: solomontessemag@gmail.com

የአፍሪካ አንድነት (ወይም ኅብረት) ባለሙሉ ክብር መሥራች ማነው? ከዚህ አኅጉራዊ ድርጅት ጀርባ ያለው ሰብዕና ማነው? ለመሆኑ፣ ከዚህ ኅብረትና ከዚህ የአፍሪካ አንድነት ጀርባ የነበሩትን ታላላቅ ሰዎች መጥቀስ ሲጀመር፣ እንዴት ሆኖ ነው ኑክሩማህ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን (ቀ.ኃ.ሥን) ቀድሞ ሊወደስም ሆነ ሊሞገስ የሚችለው? ኧረ! እንዴትስ ተብሎ ነው፣ በአፍሪካ ኅብረት አዲሱ አዳራሽ ግቢ ውስጥ የቀ.ኃ.ሥን ክብርና ዝና ችላ ብሎ ለአንድ አገሩንና ህዝቡን ለራሱ ምቾት ሲል ለሸቀጠ “ንክሩማህ” ለተባለ ሰው ሃውልት የሚቆመው? ምንድነው ጉዱ?! ምንድነው አዝማሚያው? (በዛሬው መጣጥፋችን ለነዚህ ጥያቄዎች መጠነኛ ሃተታ እናቀርባለን፡፡ መልሳችን አጥጋቢ ሆኖ እንዲገኝም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጋችንን ከሁሉ አስቀድመን ለአንባቢያን መግለጽ እንወዳለን፡፡)

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን የምናያቸው ማስታወቂያዎችና የማኃዘብ ሥራዎች (ads and publicities) በአፍሪካ አንድነት/ኅብረት የወርቅ ኢዮቤልዩ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ይኼንንም ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “የአፍሪካን ሕዳሴ እናረጋግጣለን!” በሚል መሪ ቃል ሥር ከፍተኛ ዋጋ የሚያስወጣ የማስተዋወቅ ተግባር እየፈፀመ ነው፡፡ የማስተዋወቅ ተግባሩ ከፍተኛ ሥራ ቢሆንም፣ ጉልህ-ጉልህ ስህተቶችንም አካቷል፡፡ ከቀላሉ ስህተት እንጀምር፡፡ በዜና እወጃዎች መካከል የሚተላለፈው ማስታወቂያ ላይ እንዳየነው ከሆነ፣ የአፍሪካ አንድነት (ኅብረት) ግንባር ቀደም ተጠቃሽ እንዲሆን እየተደረገ ያለው “ሟቹን ንክሩማህ” ነው፡፡ ይህ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሕዝብን ለማደናገርና ሕዝብን ለማጃጃል ካልተፈለገ በስተቀር በየትኛውም መስፈርት ንክሩማህ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ክብርና ሞገስ ሊነጥቅ አይገባውም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ይህ “ታሪክን ያላነበቡ ሰዎች፣ ታሪክን በሚፈልጉት መንገድ የመዘከር አባዜአቸው” አንዱ ማሳያ ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም ድሎቻችንንና ታሪኮቻችንን በተለያዩ ምክንያቶች እንዳስነጠቅን ነው፡፡ ከሰባ (ከሰማኒያ) ዓመታት ወዲህ ያለውን ታሪካችንን አንኳን ብንወስድ በርካታ ድልቻችንን አውላላ ሜዳ ላይ በትነናቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ የአምስቱ አመት የጣሊያንን ወረራ ዘመን አክትሞ ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት ሲመለሱ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ድላቸውን በእንግሊዝ ጮሌዎች ተነጥቀው ነበር፡፡ የ1956ቱንና የ1969ኙንም የሱማሌ ወረራዎች ለመቀልበስ በተደረገው ተጋሎ ወቅት፣ ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት ከተከፈለበት በኋላ ድላችንን አንዴ ለአሜሪካንና እንግሊዝ፣ ሁለተኛውን ደግሞ ለሶቪየት ኅብረት ቄሳራዊያን ኃይሎች አሳልፈን ሰጠነው፡፡ ለሠላሳ ዓመታት የተደረገውንም የርስ-በርስ ጦርነት ድልና ውጤት ለባዕዳን ኃይሎች የስርቆሽ በር “ዲፕሎማሲ” እና ደባ ካስረክበነው በኋላ አጨብጭበን ተቀመጥን፡፡ አሁን በቅርቡ እንኳን ከኤርትራ ጋር በተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ የሆነውን የወታደራዊ ድላችንን “የአልጀርሱ ስምምነት” በሚባለው የባዕዳን ሸምቀቆ ውስጥ ዘው ብለን ገብተን አስነጠቅነው፡፡ ይኼንን ሁሉ ውርጅብኝና ኪሳራም የተከናነብነው በመሪዎቻችን አርቆ አሳቢ አለመሆንና ጊዜያዊ የጀብደኝነት (ወይም የነጭ-አምላኩነት) ስሜት ነው (ዝርዝር ሃተታውን ኋላ እመለስበታለሁ)፡፡

በዘመናችን በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደፓን-አፍሪካኒስት የሚቆጠረው ንክሩማህ በእንግሊዝና በአሜሪካውያን ዩኒቨርሲቲዎች የተማረ ሰው ነበር፡፡ ምን አለፋችሁ፣ ቄሳራዊያኑ እንደፈለጉ አድርገው የሸምኑበት መወርወሪያ አድርገው ነበር የቀረጹት፡፡ ንከሩማህ የብሪታኒያን ጥቅሞችና የእንግሊዝን የበላይነት በጋና ምድር ለማስቀጠል የተፈበረከ “ምሁር” ነበር፡፡ ይህ ሰው፣ ለአፍሪካና አፍሪካውያን ከእጅ-አዙር ቅኝ አገዛዝ ነፃ የሚወጡበትን ረጅም ዲስኩር ያደርግም እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ከጥር 17-19/1954 ዓ.ም በተደረገው የሌጎሱ የ19ኙ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤም ላይ ሠፊ የሚባል ዲስኩር አቅርቦ ነበር፡፡ ያ ዲስኩር፣ ገና ከቅኝ ግዛትነት ሙሉ ለሙሉ ነፃ ላልወጡት አፍሪካውያን ትርጉም የለሽና ርባና ቢስም ነበር፡፡ በዚሁ የሌጎሱ ጉባዔ ላይ ታዲያ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አንድ አጀንዳ አቀረቡ፡፡ ይህም አጀንዳ የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግሉን ማጠናከርና አፍሪካውያንን ከዘር መድሎ ተጽዕኖ ማላቀቅ” የሚል ነበር፡፡ ይህም፣ አጀንዳቸው ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቶ ጉባዔው በሙሉ ድምጽ ቅድሚያ ለአፍሪካውያን ነፃነት ለመሥራት ተስማማ (አዲስ ዘመን፣ ጥር 20/1954 ዓ.ም፣ ገጽ-  1 እና 5)፡፡

በዚህ ዓላማ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉት ቀ.ኃ.ሥ ከጥር 26-የካቲት 2/1954 ዓ.ም ድረስ የቆየ “የማዕከላዊና የምስራቅ አፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ ድርጅት ጉባዔን” ጠሩ፡፡ ከሌጎሱም ጉባዔ በተሻለና በተጠናከረም መልኩ፣ ይህ የአዲስ አበባው ጉባዔ የአፍሪካን አንድነትና ኅብረትን የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ የተቀመጠ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረውን የአፍሪካውያን አንድነት ተስፋ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በየካቲት 3/1954 ዓ.ም እንዲህ ብሎ ገልጾት ነበር፤ “አፍሪቃ አንድነቷን ጠብቃ የምትጠናከርበት ተራራ-ጫፍ ላይ ተቃርባለች፡፡ ለዚህ አፍሪካዊ አንነትና ኅብረትም፣ ኢትዮጵያ ያላሰለሰ ጥረትና ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ግርማዊ ጃንሆይ በተለይ በዚህ ጉባዔ ላይ ያሰሙት መሪ-ቃል እንደሚለው ከሆነ፣ የአፍሪካን ኅብረትም ሆነ አንድነቷን የምንፈልገው ከቅኝ-ግዛት ተላቀን አፍሪካውያን በገዛ-ባህላችንና ማንነታችን ኮርተን እንድንኖር ስለምንሻ ነው፤” ብለዋል (ገጽ-3)፡፡ ያሉትን ከማከናወን የምይገቱት ጃንሆይ፣ ሩጫቸውን አጣደፉት፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዴስክም ውስጥ የነበሩትን ከፍተኛ ባለሙያዎች አስተባብረው “የአፍሪካን አንድነት/ኅበረት” ዕውን ለማድረግ ተንቀሳቀሱ፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሕያውነትም በየካቲት 1955 ዓ.ም በግልፅ መታየት ጀመረ፡፡ ሆኖም ግዙፍ ችግሮችና ተግዳሮቶች ከፊቱ ተደቀኑበት፡፡ እነርሱም የምዕራብ አፍሪካውያኑ የመካከለኛውና የደቡባዊው አፍሪካውያን ፉክክር ነበር፤ (ሞንሮቭና የብራዛቪል ቡድኖች) እየተባሉ የሚጠሩት ናቸው፡፡ እነዚህን ተሻኳች ቡድኖች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማግባባት፣ ጃንሆይ አቶ ከተማ ይፈሩንና አቶ ጌታቸው መካሻን ወደተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ልከዋቸው ነበር፡፡ እነዚህም ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ባለበሌለ ኃላቸው የሁለቱን ቡድኖች ሽኩቻ ወደ ጤናማ የፖለቲካ ግብ ለመቀየር ሠፊ ጥናቶችንና ትግሎችን አካሂደዋል፡፡ በመጨረሻም፣ በግንቦት 14/1954 ዓ.ም በተጀመረው የአፍሪካ አንድነት/ኅብረት መስራች ጉባዔ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በጃንሆይ መሪነት አስታራቂ የሆነውን የአፍሪካ አንድነት የመስማሚያ ረቂቅ ቻርተር አቀረበች፡፡

ኢትዮጵያ ያቀረበችው ረቂቅ ቻርተር አራት (4) ነጥቦችም ያካተተ ነበር፡፡ “ኢትዮጵያ የአፍረካ አንድነት/ኅብረት (ድርጅቱ) እንዲኖሩት” ያቀረበቻቸው ዓላማዎች የሚከተሉት ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ አለች፡፡ “ኅብረቱ (አንድነቱ)፡- 1ኛ) በአፍሪካ አገሮች መካከል የወንድማማችነትና (የሰሊዳሪቲ) መንፈስ እንዲዳብር ይሠራል፤ 2ኛ) ለአፍሪካ ሕዝቦች የተሻለ ኑሮ ለማስገኘት፣ የአገሮችንም ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት ለማሳካት ጥረት ያደርጋል፤ 3ኛ) በሀገሮች መካከል ያለውን መንግስታዊ ሥልጣንና ሉዓላዊነትን (ሶቨርኒቲ)፣ በሕጋዊነት፣ ለእኩልነታቸው፣ ለነፃነታቸውና የግዛት አቋማቸውን ለመጠበቅ የሚያስችል ተቋም ሆኖ እንዲደራጅ ይደረጋል፤ እና በመጨረሻም (ወይም 4ኛ) ከአፍሪካ አህጉር ላይ ኮሎረያልዝምን ለመደምሰስ የሚያስችል አቅምን ያለው ድርጅት እንዲሆን” የታሰበ ነው -ይላል፡፡ በማስከተልም፣ “ለእነዚህም ዓላማዎች መሳካት፣ የአባል አገሮች ሁሉ ጠቅላላ ፓሊሲያቸውን ያስማማሉ፤ ያዋሕዳሉ፡፡ በተለይም፣ በኤኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በጤና አጠባበቅ፣ በፖለቲካና በዲፕሎማቲክ፣ በሳይንሳዊና በቴክኒክ፣ በመከላከያም ዘርፎችም በጋራ ይተባበራሉ፡፡” በማለት የድርጅቱን (የኅብረቱን) አላማዎች ያብራራል፡፡ (ልብ በሉ፣ እነዚህን ዓላማዎች ነው ከማርኩስ ጋርቬይ ጀምሮ እስከ ንኩሩማህ ድረስ ፓን-አፍሪካኒዝም በሚል የፖለቲካ አውድ ሥር የሚያስቀምጧቸው፡፡ እነዚህን መርሆችና አሴቶች ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ባቀረበችው ቻርተር ውስጥ በግልፅ ሰፍረው እናገኛቸዋለን፡፡) እና ከዚህ በላይ ፓን-አፍሪካኒስትነት ከየት ሊመጣ ነው? በርግጥም ጃንሆይ (ቀ.ኃ.ሥ) በተግባር ፓን-አፍሪካኒስት ነበሩ፡፡ ነገር ግን፣ በተግባር እንጂ በአፍ ልፈፋና በምላስ ጮሌነት ያንን እንደሌሎቹ ሲያንፀባርቁት አልታዩም፡፡ በመሆኑም፣ የአፍሪካ መሪዎች “ፓን-አፍሪካኒስት” ላሉት ንክሩማኅ ሃውልት አቆሙለት፡፡ አይዱት ዓይነት አሸዋወድ ተሸወዱ፡፡

ካፈርኩ እመልሰኝ ያሉት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም አምና በፓርላማ ሲጠየቁ፣ ማን እንደንክሩማህ ያለ ፓን-አፍሪካኒስት አለና ነው፣ ለቀ.ኃ.ሥ ሃውልት ካልቆመ እያላችሁ” የምትነዘንዙን” ሲሉ በተለመደው ያላዋቂ ማጣጣል ስልታቸው ተጠቅመው ሸወዱን፡፡ እስከምናውቀው ድረስ፣ ሃውልቱ የቆመው ለአፍሪካ ኅብረት መሥራች እንጂ ለፓን-አፍሪካኒስት አይደለም፡፡ በየትኛውም ሂሳብ ቢሰላ ደግሞ ቡድን አደራጅቶ (የሞንሮቪያውን ተሻኳች ቡድን ይዞ) ኅብረቱ እንዳይሳካ ሲጎነጉን የነበረው ኩዋሚን ንክሩማኅ የመታሰቢያ ውልት ሊቆምለት አይገባውም፡፡ ያንን የቀኝ-ገዢዎችና የቅጥረኞቻቸውን አጀንዳ ሲያራምድ ለነበረ ሰው ሃውልት ማቆም ማለት ምን እንደሆነ ይገባናል፡፡

በመጋቢት 1968 (እ.አ.አ) የወጣው የNEWSWEEK መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ፣ ንክሩማህ ከስልጣን የተባረረው ለጋና ሳይሆን ለምዕራባውያን ቅጥረኛ ሆኖ እንደሚሠራ ስለታወቀ ነው-ይላል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ከሥልጣን ተወግዶ በኩባ መጠጊያ ሲሰጠው፣ ከሥልጣን ያባረሩት ጎበዞች አንድ ምስጢር አወጡ፡፡ እርሱም፣ “ንክሩማኅ ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ሮልስ-ሮይስ መኪናና ከአስር ሚሊዮን ዶላር በላይም የሚያወጣ ቅንጡ መርከብ” ገዝቶ ይንፈላሰስ እንደነበረ ይፋ ወጣ፡፡ በወቅቱ ጋና ከፍተኛ የሆነ የውጭ ዕዳ ጫና ያናጥርባትም እንደነበረ የNEWSWEEK ዘገባ ገልፅዋል፡፡ ታዲያ፣ ንክሩማህ ከሥልጣኑና ከሀገሩ ጋና አንዲሁም ከአህጉሩ አፍሪካ ከተባረረ ከአርባ አመታት በኋላ ሃውልት ይቁለት ብለው የተስማሙት የአፍሪካ መሪዎች ብዙዎቹ በሙስናና በሕዝብ ሃብት ዝርፊያ የተጨማለቁ አስገድዶ ገዣችና አሽከሮቻቸው እንጂ እውነተኛ አፍሪካውያን አይደሉም፡፡

የኢትዮጵያ ወደ አቀረበችው ረቂቅ እንመለስ፤ እንዲህ ሲል ይቀጥላል፤ “ከፍ ብለው የተጠቀሱትን ዓላማዎች ለማስፈጸም ከድርጅቱና ከአባል አገሮች በሙሉ የሚከተሉት መሠረታዊ ነገሮች ይጠበቃሉ፤
1.  የአፍሪካ አገሮችን መንግስታዊ እኩልነት፣
2.  በሀገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት ስምምነትና፤
3.  የእያንዳንዱን ሀገር በነፃነት የመኖር መብትና መንግስታዊ ስልጣን (ሉዓላዊነት)ና ግዛታዊ አቅዋም የማክበር ግዴታዎች ተፈጻሚ” ናቸው - ሲል ይደነግጋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ አህጉራዊ ተግባራቱን በሚከተሉት ዋና ዋና ተቋሟችን በኩል ይፈጽማል፡፡ 1. የመንግስታትና የሀገር መሪዎች ጠቅላላ ጉባኤ፤ 2. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ፤  3. በጠቅላይ ጽ/ቤት፤ 4.በኤኮኖሚና የሶሻል ኮሚቴ፤ 5. የትምህርትና የባህል ኮሚቴ፤ 6. የመከላከያ ቦርድና 7. የሳይንስ ማሰልጠኛና የጥናት ተቋማት በኩል ይሆናል፤” ይላል፡፡

እነዚህ “ኮሚቴ” የተባሉት ናቸው-በ2002 ዓ.ም በተደረገው የአፍሪካ ሕብረት ምስረታ ወቅት “ኮሚሽን” የሚል የክርስትና ስም አግኝተው ብቅ ያሉት፡፡ “ጉባኤው በተከፈተበት ወቅት የ30 የአፍሪካ መሪዎች የተገኙበት ጉባኤ” ሲሆን ግርማዊ ጃንሆይን የጉባኤው የክብር ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጥ ነበር የተጀመረው፡፡ 250,000,000 በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን በንቃት ይከታተሉት ነበር፡፡ በግንቦት 14 ቀን 1955 ዓ.ም ጉባኤው በአፍሪካ አዳራሽ ተጀመረ፡፡ ከ2000 በላይ ተካፋዮች ተሳታፊ ነበሩ፡፡  (አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 15/1955)፡፡ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ረቂቅም ላይ፤ “ግንቦት 17 ቀን የአፍሪካ የነፃነት ቀን ሆኖ ይከበራል፤” የሚል ብሩህ ተስፋ ተካቶ ነበር፤ የተባለውም ሆነ፡፡

ለዚህም፣ ድርጅት እውን መሆን ኢትዮጵያ በወቅቱ ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ መጪ አድርጋ ነበር፡፡ የአፍሪካ አዳራሽን በልዑል ራስ መንገሻ ስዩም የሥራ መሪነት ለማከናወን፣ ኢትዮጵያ መሬትና ሃብቷን በነፃ ሰጥታለች፡፡ የጊዮን ሆቴልና የኢትዮጵያ ሆቴልንም በመሥራት በኩል ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጋለች፡፡ የንክሩማህን ፎቶ ከጃንሆይ ፎቶ በፊት እያመጣ የሚያበሳጨንንም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ሥራ ለማስጀመር በርካታ ወጪ ጠይቋል፡፡ (ይህ ድርጅት በአቶ ሃረጎት አባይ መሪነት (ያን ጊዜ በማስታወቂያ ሚኒስትር፣ በሚነስቴር ዲኤታ ማዕረግ ይሠሩ ነበር) የተከናወነና ከአዳራሹ ውጪ ያሉት የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኖች ስብሰባውን በቀጥታ መከታተል እንዲችሉ ተብሎ የተቋቋመ ነው (አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 24/1955 ዓ.ም፣ ገጽ-2)፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ነገሮች ላይ ዳር ቆመን የመመልከት ልክፍት አለብን፡፡ ይኼ ምናልባትም ከሦስት መቶ አመታት በፊት እንግሊዛዊው ኤድዋርድ ጊበን ያለውን ሃሳብ ያስታውሰናል፡፡ ጊበን እንዲህ አለ፤ “ዓለም ረስታቸው፤ እነርሱም ዓለምን ረስተው፣ ኢትዮጵያውያን ለሺህ ዓመታት ያህል አሸለቡ፡፡” እንግሊዛዊው የታሪክ ጸሐፊ በጥቅሱ ላይ፣  ባንድ በኩል ኢትዮጵያ ከቀረው ዓለም ተነጥላ፤ ለብዙ ዘመናት በብቸኝነት መኖሯን ይገልፃል፡፡ የሐሳቡ ትክክለኝነት ከዚህ ጭብጥ አያልፍም፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ጊቦን በጥቅስ አመራረጡ በጣም ተሳስቶም ነበር፡፡ ምናልባትም አብዛኛው ዓለም ረስቶን ኖሮ ይሆናል፡፡ ምናልባትም ሌላ ሰፊ ዓለም መኖሩን እስከ መርሳት ደርሰን ሆኖ ይሆናል፡፡

ግን በማሸለብ አይደለም፤ አልነበረምም፡፡ ጭልጥ ያለ እንቅልፍም ወስዶን በመተኛታችንም አይደለም፤ ይኼ ከቄሳራዊያን አንጎል የሚወጣ ተራ ቧልት ነው፡፡ ሺህ ዓመታት ያህል ነቅተው የጠበቁ ሕዝቦች ቢኖሩ፣ በእርግጥ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ የነፃነትን ችቦ ለኩሰው ከፍ አድርገው በመያዝ ለአፍሪካ ሕዝቦች ለማረካከብ የበቁት አሸልበው ሳይሆን ነቅተው በመጠባበቃቸው ነው፡፡ የዛሬዎቹ አፍሪካውያን ግን ችቦአችንን ነጥቀው፣ ሊወስዱ “ቃዛፊ” በሚባለው ሰው አማካይነት ተፍጨርጭረው ነበር፡፡ ሙዓማር ቃዛፊ (ቀጣፊው) የኦቶማኖች የመንፈስ ልጅ ነው፡፡ የማያሸልቡት አትዮጵያውያን ደግሞ ኦቶማንን አሳፍረውታል፡፡

በመጀመሪያ የአቶማንን፣ ቀጥሎም የኮሎኒያልስቶችን ወረራ ለማስቆም ነቅተው የተከላከሉት ያላሸለቡት ናቸው፡፡ ባንድ በኩል በጠላት መከበባቸው ከውጪኛው ዓለም ሲነጥላቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ እየተደጋገመ የደረሰባቸው ወረራና ክህደት ውጪኛውን ዓለም በመጠራጠር እንዲመለከቱት ስላደረጋቸው፤ በራሳቸው ዓለም ውስጥ በራሳቸው ብሔራዊ ምሽግ ውስጥ መኖርን አስመረጣቸው፡፡ ለብዙ ዘመናትም ራሳቸውን አፍሪካዊ ሳይሆን “አበሻ ነን” እያሉ የጠሩት ለዚ ነው፡፡ ጊቦን የዘነጋው ይሄንን ሁናቴ (ወይም አውድ) ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት በእርግጥ በብቸኝነት (ብቸኛ ሆና) ኖራለች፡፡ እንደገና ወደኋላ ተመልሰን ስንመለከተው መልካም ብቸኝነት ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡ ሌላ ምርጫ ቢኖራት ደግሞ፣ ያ በባርነት ሥር መውደቅ ነበር፡፡ እንደሚታወሰው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሌላው ዓለም ጋር በገሀድ የተቀላቀለችው በ1916 ዓ.ም የቀድሞውን የአለም ማህበር አባል (League of Nations) አባል ስትሆን ነው፡፡ ከዚያን ያገኘችው ልምድ/ተሞክሮ ጣፋጭ አልነበረም፡፡ ወረራ በተነሳበት ጊዜ አሁንም ሌላው ዓለም ብቻዋን ተዋት፡፡

ሆኖም፣ “ደኅንነትና ሰላም የሚመሠረተው በዓለምአቀፍ ትብብር እንጂ በኩርፊያ አይደለም” ብለው የሚያምኑት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያለፈውን ታሪክ ይቅር ብለው “የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሲቋቋም መስራች አባል በመሆን ኢትዮጵያን እንደገና በዓለም አቀፍ ኑሮ ውስጥ አስገቧት፡፡ ይህም ድርጅት በ1990ው የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ወቅት ተመሳሳይ ስህተትን ደገመ፡፡ ሆኖም፣ ኢትዮጵያ ለድርጅቱ በዝምታና በጽሞና በማገልገል ላይ ናት፡፡

በ1947/8 ዓ.ም በኮሪያ፣ በ1952 ዓ.ም በኮንጎ ጀግና ልጆቿን አሰልፋ የዓለምአቀፍ ግዴታዎቿን ከሚጠበቅባት በላይ ስትፈጽም ኖረች፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የዓለም አቀፍ ተግባራቶች ሁሉ ጨኸት አታሰማም፡፡ አንድ ጋዜጠኛ እንደጠቀሰው “ኢትዮጵያ ዝምተኛዋ የዓለማችን አገልጋይ ናት!”

የአፍሪካ አንድነት (ኅብረት) ጉባኤ ውጤታማ ሊሆንና ሊሰምር የቻለው በግርማዊ ንጉሠ ነገስት በምትመራው ኢትዮጵያ ጥረትና ቁርጠኝነት ነው፡፡ ራሳችንን በማመስገን አንጃጃልም እንጂ፣ በወቅቱ የነበሩት የአፍሪካ መሪዎች ይኼንን ሀቅ በደንብ አድርገው መስክረውታል፡፡ የፕሬዝዳንት ጁሌስ ኔሬሬን፣ የጆሞ ኬንያታንና የጋማል አብደል ናስርን፣ እንዲሁም የኬኔት ካውንዳን እማኝነት ተፈላልጎ ማንበቡ ይጠቅማል፡፡ እነዚህ የታሪኩ አካላትና የዐይን ምስክሮች የጃንሆይን ጥረትና ባለሙሉ ክብር ተቀዳሚ የአፍሪካ አንድነት (ኅብረት) መሥራችነት በደንብ ገልፀውታል፡፡ (እነዚህን መሪዎች የጠቀስነው ሆን ብለን ነው፡፡ እንደዛሬዎቹ መሪዎች ሙሰኞችና “ሥልጣኔን አለቅም ባዮች” ስላልሆኑ ነው፡፡ ለእውነትና ለሕዝባቸው ክብር እንዲሁም ለአፍሪካዊነት ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ በዚህም እናከብራቸዋለን፡፡

ኢትዮጵያ የነፃነት ብቸኛ በነበረችበት ጊዜ ስለአፍሪካ ነፃነት ስትከራከርና ስትታገል ቆይታለች፡፡ አሁን ደግሞ ለአፍሪካ አንድነት (ኅብረት) ተቀዳሚውን እርምጃ በመውሰድ “ዝምተኛ አገልጋይነቷን” በተግባር አሳየች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ በብቸኝነት እስከ አፍሪካ አንድነት የፈጸመችው ረጅም ጉዞ ከግርማዊነታች የፖለቲካ ችሎታ ጋር አብሮ የሚወሳ ታሪክ ነው፡፡ ማንም በአፈጮሌነት ሊያድበሰብሰውም ሆነ ሊደባብቀው አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ አንድነትን በንጉሠ ነገሥቷ አማካይነት ነፍስ እንዲዘራ ያደረገችው፣ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ከጠንካራ አፍሪካዊነት የተሳሰረና የተጋመደ ነው በላ እንጂ፣ የኖራና የሸክላ ሃውልት እንዲቆምላት አስባ አይደለም፡፡ (ዘላለማዊ ክብር ለአፍሪካዊው ድርጅት መሥራቾች ይሁን፡፡ በተለይም ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ!.... የሳምንት ሰዎች ይበለን፡፡)

አስተያየቶች