የገናው
መልእክት
በሰሎሞን ተሰማ ጂ. http://semnaworeq.blogspot.com
Email: solomontessemag@gmail.com

ዛሬ በዓለማችን ላይ
ከሦስት ቢሊዮን በላይ ክርስቲያኖች እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ ሆኖም፣ የገና በዓል መንፈሥ የክርስቲያኖች ብቻ አይደለም፡፡ በወንድማማችነት፣
በፍቅርና እርስ-በርስ በመዋደድ ላይ የተመሠረው የክርስቶስ ትምህርት ዋና ዓላማው፣ ሁሉንም ሃይማኖቶች የሚያጠቃልልና ዓለም አቀፋዊ
እሴትም ነው፡፡ ጉልሁ ጥያቄ ታዲያ፣ “ዓለማችን ታዲያ፣ ወደክርስቶስ መልእክት ምንያህል ተቃርባለች?” የሚለው ነው፡፡ ይህ ጥያቄ
ዓመት አልፎ ዓመት ቢተካም ለሕሊናችን የሚቀርብ ዘላለማዊ ጥያቄ ነው፡፡ ዘንድሮም ታዲያ ይህንኑ ጥያቄ መልሰን ብናነሳው የሚያጽናና
መልስ አናገኝም፡፡ እርግጥ ነው ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ገና አልተነሣም፡፡ ደግሞም ግን፣ በሰው ልጆች መካከል ዘላቂ ሰላም ገና
አልተመሠረት፡፡ በመካከለኛው አፍሪካ፣ በተለይም-በዛየር፣ በቡሩንዲ፣ በኮንጎ ብራዛቪል ሠላም ደፍርሷል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅና
በሰሜን አፍሪካም የፀደዩ የአረብ አብዮት ጣጣ-ፈንጣ ገና አላበቃም፡ ንፍፊቱና መገረኑ፣ ከሊቢያና ከሶሪያም አልፎ የመንን ዶግ-አመድ
አድርጓታል፡፡ እንዲያውም ስድስት ገናዎችን አስቆጥሯል፡፡ መቼም የአፍጋኒስታንና የኢራቅ ውጥንቅጥ ወደአስራ ስድስት ገናዎች ሊሆኑት
ነው፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ፣ የአይ.ኤስ.አይ.ኤስና የታሊባንም ክንዶች የመፈርጠም ምልክት አሳይተዋል፡፡ በቅርባችን
በሶማልያም የርስ-በርስ ገጭቱና አለመረጋጋቱ ሃያ-ስምንተኛ ገናውን አስቆጥሯል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውም መፋጠጥ
የኼው አስራ ስምንተኛ ገናውን ሊደፍን ወራት ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡
የበለፀጉት አገሮች/ኃያላኑም
በኤኮኖሚ (በነገረ-ነዋይ) ቀውስ ውስጥ ከተዘፈቁ እነሆ ዘጠኝ ገናዎች ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም፣ በግሪክ፣ በስፔንና በፖርቹጋል እንደምናየው
ከሆነ፣ ችግሩ ከመሻሻል ይልቅ እጅግ ስለተባባሰ፣ ብዙዎች የገና ካርድ እንኳን ለመግዣ የሚሆናቸውን “ማህለቅ” ማግኘት ተስኗቸዋል፡፡
ነገር ግን፣ ብዙ ሃገሮች የጦር መሣሪያና ትጥቅ አሁንም ያከማቻሉ፡፡ የለየለት የጦርነት ሥጋት እየገነነ ኼዷል፡፡ የአልቃይዳና የእህት
አሸባሪ ድርጅቶቹ ስጋት መኻል ፓሪስም አደባባዮች ላይ ተደጋግሞ ተከስቷል፡፡ ከሰሞኑ ያየነው የትምህርት ቤት ጥቃት የአደጋው ደንበኛ
ማሳያ ነው፡፡ በሊቢያ፣ ሶርያ፣ በየመንና በኢራቅ ያለው የአልቃይዳ አልሞት-ባይ ተጋዳይነት ተባብሷል፡፡ በቅርባችንም የሶማሊያ ሁኔታ
“ከድጡ-ወደ-ማጡ” እንደሚባለው ሆኗል፤ አልሸባብ፣ አልሂዝቡል፣ አልመንጁስ፣ አልነጂስ፣…..ወዘተርፈ በሚባሉ ጎሰኛና ነውጠኛ ቡድኖች
ደቡብ ሶማሊያ እየራደች ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ባለቤት
-ክርስቶስ ራሱ እንዳለው፣ “እርስ በርሱ የተከፋፈለ ቤት ሊፀና አይቸልም፡፡” አብያተ ክርስቲያነትም በዚህ ዓብይ የሆነ የገና መንፈሥ
ወደኋላ ተመልሰው፣ በበረት የተወለደውን፣ የትሑቱን መምህር ትምህርት ቢያስታውሱትና ከሚለያዩበት ይልቅ የሚገናኙበት መብዛቱን ሊገነዘቡ
እንደሚገባቸው ለማውሳት እሻለሁ፡፡ ለሰው ልጆች ታላቁ መተሣሠሪያ ኃይላቸው-“በጎ ፈቃድ” ነው፡፡ በዚህ የገና መልእክታችንም፣ በሁሉም
ሕሊና ውስጥ “በጎ ፈቃድ በሰው ልጆች ሁሉ መካከል ይሁን!” የሚለውን የመላእክት ዝማሬ፣ በቤተ ክርስቲያንና በቤተ መንግሥትም መሪዎች፣
በገዢዎችና በተገዢዎች፣ በመሪዎችና በተመሪዎችም መካከል በመላው ዓለምና በኢትዮጵያም ሕዝብ ልቦና ውስጥ እንዲያሠርፅ በእጅጉ እንመኛለን፡፡
(አሜን!)
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ
Thanks a lot for your comments.