ጎንደርነት እና ሐረርነት !!!

በሰሎሞን ተሰማ ጂ.  semnaworeq.blogspot.com  Email: solomontessemag@gmail.com
ባለፈው ሳምንት በወጣው የአዲስ ጉዳይ ቅጽ 7፣ ቁጥር 150 (የካቲት 2 ቀን 2005 ዓ.ም) ዕትማችን ላይ ወይም ደግሞ http://semnaworeq.blogspot.com/2013/06/blog-post.html  ስለሐረርነት እና ስለጎንደርነት ተናግረን ነበር፡፡ በዚህ ዕትማችን (በቁጥር 150ኛው) ላይ ደግሞ ስለ“ጎንደርነት እና ሐረርነት” እንጽፋለን፡፡ ባለፈው ዕትማችን ላይ እንደገለጽነው ስለጎንደርነትና ስለሐረርነት ማውራት ማለት ስለጎንደሬዎች እና ስለሐረሮች ማውራት ማለት አይደለም፡፡ ልናወሳ የምንፈልገው፣ ስለጎንደር እና ስለሐረር (ስለቦታዎቹ) ነው፡፡ በመሆኑም፣ በዚህ መጣጥፍ ውስጥ በምናነሳቸው አንኳር-አንኳር ነጥቦች፣ የዛሬዎቹን ሐረሮች እና ጎንደሮች እያሰብን አልጻፍነውም፡፡ እንዲያውም ፍላጎታችን፣ ከደርግ መራሹ ወያኔ-ኢህአዲግ መምጣት በፊት ስለነበሩት ጎንደር እና ሐረር ለመዘከር ነው፡፡ በመሆኑም፣ አንዳንድ ነጥቦችን ስታገኙ በቀጥታ ከዚህ ዘመንና ከዚህ ወቅት ጋር ባታናጽሩት ይመከራል፡፡ (ካነጻጸራችሁትም፣ የእናንተ የአንባቢያኑ ነፃነት እንጂ የጸሐፊው ፍላጎት አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡)



                                    *******************
ደስታ ተክለወልድ “ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት” ባሉት መጽሐፋቸው በገጽ 285 ላይ “ጎንደር” የሚለውን ስም እንዲህ ይበይኑታል፡፡ “ጎንደር” ማለት ይላሉ፣ “ጉንደ ሀገር፣ ዋና አገር፣ ያገር ግንድ፣ ያገር ቀንድ፣ ፋሲል የሠራው መናገሻ፤ የበጌምድር ከተማ፣ መዲና፣ ባለ44 ደብር” ማለት ነው፡፡ በአንጻሩ፣ “ሐረር” ማለት ደግሞ፣ “ሐረረ፣ ከሚለው ግስ የሚወጣ ሲሆን፣ የከተማ ስም፤ በሸዋ በስተምስራቅ ያለ ታናሽ ከተማ፣ በግንብ ቅጥር የተከበበና የታጠረ ነው” ይላሉ፡፡ “ሐረራዊ” ማለትም፣ “የሐረር ሰው ከትግሬ የኼደ፣ እና ሐረርኛ ቋንቋ የሚናገር ነው፤” ካሉ በኋላ፣ “ከግዕዝ፣ ከዐማርኛ፣ ከትግርኛ፣ ከትግረ፣ ከአርጎቢኛ እና ከጉራጌኛ የሚገጥም” ቋንቋ መሆኑንም ያወሳሉ (ገጽ 527)፡፡

የ“ጎንደርነት” ኩራት በዋናነት የነገሥታቱ አብያተ-መንግስታት እና ከጢስ ዐባይ አጠገብ/ዝቅ ብሎ ያለው፣ “የአፄ ፋሲል ድልድይ” ወይም “የዕንቁላል ድልድይ” ነው፡፡ ያሬድ ግርማ ኃይሌ የተባሉ ፀሐፊ በ1999 ዓ.ም ባሳተሙት “የጎንደር ታሪክ፣ ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር” በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ “አፄ ፋሲል፣ የተለያዩ የእደ ጥበብ ሙያ ያላቸውን፤ የሽመና፣ የግንብ ሥራ፣ የብረታ ብረት ሥራ፣ የአንጥረኝነት፣ የኖራ አቡኪ፣ ሸክላ ሠሪዎችን፣ ኮርቻ ሠሪዎችን፣ እና ወዘተ… ከተለያዩ ቦታዎች አሰባስበው በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ አስፍረው ማሠራት ጀመሩ፤” እያለ ይቀጥላል፡፡ ደራሲው ያሬድ ግርማ ዋናውን ምስጢር አልተናገረም፡፡ ዋናው ቁምነገር፣ እነዚህ የስነ ሕንጻና የዕደ-ጥበብ ባለሙያዎች “ከየትኞቹ የተለያዩ ቦታዎች ነው አሰባስበው ያመጧቸው?” የሚለው ነው፡፡ “ከተለያዩ ቦታዎች” የሚለው ሃረግ አሻሚ ነው፡፡ “ከሀገር ውስጥ ነው ወይስ ከውጭ አገር?”  የሚለውን አያሳይም፡፡ “ፋሲል ይንገስ! ሃይማኖት ይመለስ!” ተብሎ ፋሲል ሲነግስና አባቱ አፄ ሱስንዮስም በአዋጅ ቀይሮት የነበረው ካቶሊክነት ተወግዶ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሲመለስ፣ “አፄ ፋሲል ሙሉ ለሙሉ ፖርቹጋሎቹን ከኢትዮጵያ አስወጥቷቸዋልን?” ወይስ “የተወሰኑ የስነ-ሕንጻ ባለሙያዎችን መርጦ አስቀርቶ ነበር?” “የፋሲል/የእንቁላል-ድልድይ” የሚባለውንስ ከጢስ ዐባይ ዝቅ ብሎ የሚገኘውን ድልድይስ ማነው የገነባው?” በዕርግጥ፣ ኢትዮጵያውያን ናቸውን ወይስ ከክርቶፎር ዳጋማ ጋር የመጡት 400ዎቹ ፖርቹጋሎች መካከል የስነ-ሕንጻና የድልድይ ሥራ መሃንዲሶችም መጥተው ነበር?” እነዚህንና እነዚህን መሠል ጥያቄዎች ደህና አድርገን እንዳናገኝ ያገደን፣ የአፄ ፋሲል ዜና መዋዕል ያለመገኘቱ ጉዳይ ነው (ሥርግው ኃብለ ሥላሴ (1957)፤ አፄ ምንሊክ የአዲሷ ኢትዮጵያ ስልጣኔ መስራች  ገጽ 47-8)፡፡  

በተመሳሳይ መልኩም፣ የ“ሐረርነት” ኩራት የሆነው የጀጎል ግንብና በውስጡም ያሉት መኖሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ አረብ ፋቂህ የተባለው ፀሐፊ በፃፈውና ሬኔ ባሴት በተረጎሙት “ፍቱሕ አል ሀበሽ” በተባለው መጽሐፍ ላይ (በገጽ 168) እንዳሰፈረው ከሆነ፣ “በ1540-42 ባሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ አሚር ኑር ኢብን ሙጃሂድ፣ 481,812 ሜትር ካሬ ያለውን የጀጎል ግንብ፣ ከክርስቲያኖችና ከኦሮሞዎችም እየተከላከለ ሐረርጌ ተቀምጦ በሚያስተዳድርበት ጊዜ፣ ከተማዋ ሐረር የወረራ አደጋ እንዳይደርስባት ዙረያዋን በግንብ አሳጠራት” ይላል፡፡ ባሳየውም መልካም አስተዳደርና ባሠራውም በዚህ ግንብ የተነሣ በዘመኑ በነበሩ የእስልምና ተከታዮች ዘንድ እንደጻድቅ የሚቆጠር መልካም አሚር (መስፍን) እንደነበረ፤ በዘመኑ ከነበሩት ታሪክ ፀሐፊዎች መኻከል እነአቡበከር ኢብን መሐመድ (አልዊ ሰንባል)ም ያረጋግጣሉ፡፡  ነገር ግን፣ በግራኝ ዘመን የመጡትና ከልብነ ድንግል እንዲሁም ከገላውዲዮስ ጋር ለአህመድ ግራኝ ወግነው ይዋጉ የነበሩት የቱርክ ወታደሮች፣ በአሚር ኑር ዘመን ሙሉ ለሙሉ ከሐረር ይውጡ ወይስ አይውጡ፣ አረብ ፋቂህም ሆነ እነአቡበከር መሐመድ አይገልጹም፡፡ ምናልባትም፣ መድፍና ዐረር ይዘው ከቱርክ የመጡት ሙጃሂዲኖች መካከል የተወሰኑት የስነ-ሕንፃና የግንባታ ባለሙያዎች የነበሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼንን የሚያሰኘውም፣ ከአሚር ኑር በኋላ፣ ሌላ ተመሳሳይ ጀጎል ወይም ግንብ በቅርብ እርቀት ላይ ወይም የወላስሞች መናገሻ በሆነችው ሰመራ ወይም ሚሌ አካባቢ እንኳን አለመሰራቱን ስለምናውቅ ነው፡፡ 

የጎንደርንም ሆነ የሐረርን ግንባታዎች ማንም ሠራቸው ማንም፣ ትልቁ ቁምነገር ያለው “ማን አሰባቸው?” የሚለው ጥያቄ ላይ ነው፡፡ የጎንደርን እና የሐረርን ግንቦች ከሠሯቸው ግንበኞች ይልቅ፣ “ሐረር እና ጎንደር በግንብ መታጠር አለባቸው!” ብለው ያሰቡትና ያቀዱት አሚር ኑርና አፄ ፋሲል ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ለመገንባት ሲነሱም ከጎናቸው ሌሎች ሕዝቦችና ወገኖች ነበሩ፡፡ ጎንደርነት የተገነባው የሸዋን፣ የወሎን፣ የጎጃምንና የጎንደርን እንዲሁም የትግራይንና የባሕረ-ነጋሽን ሕዝብ ግብር በመቀበል ነው፡፡ “ፃዲቁ ዮሐንስ” እየተባሉ ከሚጠሩት፣ ከአፄ ዮሐንስ 1ኛ (1659-1674) እና ከመናኒው ንጉሥ አድያም ሰገድ እያሱ በስተቀር፣ ሌሎች ነገስታት ከፍተኛ ግብር ይሰበስቡ ነበር፡፡ ያንንም ግብር ለአብያተ-ክርስቲያናትና ለአበያተ-መንግሥታት መሥሪያ አዋሉት፡፡ በተለየ መልኩም፣ አሚር ኑርና ቀዳሚው ኢማም አህመድ ግራኝ፣ ከሸዋ፣ ከወሎ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከትግራይና ከደቡብ ኢትዮጵያ አብያተ-ክርስቲያናትና የነገሥታት አምባዎች በበዘበዙት ሀብትና ቅርስ የራሳቸውን ግንብ፣ ለራሳቸውና ለሕዝባቸው ሠሩበት፡፡ ዞሮ ዞሮ፣ “የጎደርነት ኩራት” የሆነውም የፋሲል ግንብ ሆነ፣ “የሐረርነት ኩራት” የሆነው የጀጎል ግንብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብትና ንብረት እንጂ የጎንደሬዎች ወይም የሐረሬዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ (የሚያሳዝነው የኢትዮጵያውያን ሀብትና ንብረት በግብርም ሆነ በዘረፋ ሲበዘበዝ ኖሮ፣ ላለፉት አራት መቶ ሃምሳ ዓመታትና ከዚያም በላይ ለሚሆኑ ዘመናት፣ ሌላ የመሳፍንትና የሕዝብ መኖሪያ የሆነ “የጀጎል ግንብ” እና ሌላ የነገሥታት መናገሻ የሆነ የ“ፋሲል ግንብ” አለመሥራታችን ነው፡፡) 

ባለፈው ጽሑፋችን፣ “ጎንድርነት ማለት የትም ፍጪው ስልጣኑን አምጪው!” እንደማለት ነው ስንል አውስተን ነበር፡፡ ለዚህ አባባላችን ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው፣ ርጉም ተክለ ሃይማኖት ነው፡፡ አባቱን መናኒ መንግሥት አድያም ሰገድ እያሱን አስገድሎ የነገሠው ርጉም ተክለ ሃይማኖትን የመሰለ ግፈኛ መሪ፣ ጎንደርነት ውስጥ ነበረ፡፡ አባቱን አስገድሎ ዙፋኑ ላይ ከወጣ በኋላም፣ ያላዋረደው ሹምና ያላስመረረው ካህን አልነበረም፡፡ መጨረሻም ላይ፣ ካህናቱና መኳንንቱ በጋራ አድመው፣ ርጉም ተክለ ሃይማኖት በነገሠ በሁለተኛ ዓመቱ፣ ጎጃም ሄዶ አንበሳና ዝሆን ማደን ላይ ሳለ፣ አልሞ ተካሽ ከበቅሎው ላይ በተኩስ መትቶ ጣለው፡፡ በዚያውም ሞተ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም፣ ባለፈው ሳምንት ጽሑፋችን ላይ እንደገለጽነው፣ “ሐረርነትም ውስጥ የትም ፍጪው ገንዘቡን አምጪው!” የሚል አመለካከት ስለመኖሩ ጽፈን ነበር፡፡ ለዚህ አባባላችንም ማስረጃ የሚሆነው፣ ሙሴ ደወ የሚባለው የፈረንሳይ ጸሐፊ በ1855 ዓ.ም ሐረር መጥቶ በነበረበት ወቅት የታዘበው ማሳያ ነው፡፡ ግፈኛው የሐረር አሚር መሐመድ ኢብን ዐሊ፣ የሐሰት ገንዘብ/መሐለቅ (forgery) ሠርቶ በማውጣትና በማታለል ንግዱን ሁሉ የግሉ አድርጎት ሀብቱን ሁሉ በመሰብሰብ፣ ሕዝቡንም በማጉላላቱ የተጠላ አሚር ስለነበር፣ ግብፆች መጥተው ሐረርን በሕዝቡ ትብብር ተቆጣጠሯት እያለ ያትታል፡፡ “ሕዝቡም፣ ከዚያ ግፈኛ አሚርና ከግብረ-አበሮቹ ብዝበዛ ለጥቂት ተረፈ፤” ሲል ያክላል ሙሴ ደወ፡፡ 

በጥር 1879 ዓ.ም የእስልምና መናኸሪያዋ ሐረር፣ በክርስቲያኖች መዳፍ ውስጥ ገባች፡፡ (በአፍጋኒስታን ታሊባንን መራሹ የአሜሪካን ጦር ሐሚድ ካርዛይን ፕሬዝዳንት ብሎ እንዳነገሰው ሁሉ፣ በሐረርም ግፈኛውን አሚር መሐመድ ኢብን ዐሊን በሕዝቡ ትብብር ያስወገደው የግብፁ ቄሳራዊ ጦር ሐረርን ለቆ በ1878 ሲወጣ አሚር አብዱላሂን አንግሦ ወጣ፡፡) ከሸዋ በዘመተው ጦር የተሸነፈው የአሚር አብዱላሂ “ፈሪ የናቱ ልጅ ነው!” ብሎ ወደሶማሊያ ፈረጠጠ፡፡ አፄ ምንሊክም፣ ሁሉም የያዘውን ሃይማኖት ሳይቀይር “ሃይማኖት የግል፣ አገር የጋራ ነው!” ብለው አዋጅ ስላስነገሩ፣ እስልምና የሐረርነት የተከበረ ሃይማኖት ሆኖ ቀጠለ፡፡ አንዲትም መስኪድ ያለዲፕሎማሲያዊ ድርድርና ታክቲክ አልፈረሰም፡፡ በጀጎል ውስጥ ያለውን ዋና መንገድ (“አንደኛ መንገድ” ይባላል) ለማውጣት ሲስማሙ የአሚር አብዱላሂ አጎት አቡበከርና ሌሎች የሐረር ሽማግሌዎች ከምንሊክ ጋር ፊት-ለፊት “በሰጥቶ መቀበል መርህ” ተደራድረዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ በጥር 1880 ዓ.ም ወደ ጎንደር የገሠገሠው ጂሃዳዊው የደርቡሽ ጦር፣ የጎጃሙን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን አሸንፎ፣ ጎንደርን በዘበዛት፤ አቃጠላት፡፡ ከአርባ-አራቱ አብያተ-ክርስቲያናት ውስጥ አራቱ ብቻ በተዐምራት ተረፉ፡፡ አርባዎቹ ሙሉ ለሙሉ ወደሙ፡፡ በርካታ ክርስቲያኖች ተማርከው በመተማ በኩል ወደሱዳን ተወሰዱ፡፡ “አይታሰስም ምጣድ በግምጃ፤ ዘንድሮ ደርቡሽ መጽረፉን እንጃ!” ብሎ ፎክሮ ሄዶ የነበረው የጎጃም ጦር ክፉኛ ተመታ፡፡ ወታደሩም ተፈታ፡፡ የሞተው ሞቶ፤ የሸሸውም ፈርጥጦ፣ የተያዘውም ተማረከ፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትና ጥቂት አዛዦቹም ምንትዋብ የምትባለውን የተክለ ሃይማኖትን ሁለተኛ ሚስት እንኳን ሳይዙ ሸሽተው አመለጡ፡፡ ለዚህም ነው፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በጎንደሬዎች ዘንድ “አትከልክልሞይ (ተክለ ሃይማኖት)፣ ይዘህ አለንጋህን፤ አሞራ (ደርቡሽ) ሲበላው የገዛ ገላህን (ምንትዋብህን)!” ተብሎ የተወቀሰው፡፡ ሐረርነት ውስጥ “ሃይማኖና ሀገር” የተለያዩ መሆናቸው ተስተውሎ ሐረር ከጥፋትና ከቃጠሎ ስትድን፤ ጎንደርነት ውስጥ ግን “ሃይማኖትና ሀገር አንድ ናችሁ!” ተብለው፣ በአንድነት ተገደሉ፤ ተቃጠሉ (ተክል ጻድቅ መኩሪያ (1982) አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት፣ ገጽ 292 እና 450-451 ላይ ይመልከቱ)፡፡

ሌላው ጎንደርነትን እና ሐረርነትን የሚያመሳስላቸው የጣሊያን ወረራ ነው፡፡ ጣሊያን ከወረራው ሦስት ዓመታት ቀደም ብሎ በሐረርና በጎንደር ላይ ቆንስላ ከፍቶ ነበር፡፡ ሕዝቡንም በስኳርና በሳሙና፣ በፓስታና በሹታ (እርዳታ ስም) መደለል ጀምሮ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎችንም ልብ አሸፍቶ ነበር፡፡ በተለይም የወጣቶችን ልብ አማልሎ ነበር፡፡ (መንግሥቱ ለማ፣ “ኧረ ሄደ-ሄደ፣ ሄደ ኮበለለ፤ በስኳር ብስኩት እየተደለለ!” ያሉት ነገር ለዚህም ጊዜ ይሠራል፡፡) ጥሊያን ሲኒማ ቤቶችን ያሠራው ከ1927 በፊት ነበር፡፡ ለወጣቶቹም የፋሺስትን መርዘኛ ፊልሞች ማሳየት ጀምሮ ነበር፡፡ “ባሊላ” የተባሉትም የፋሺስት ትምህርት ቤቶች በሐረርና በጎንደር ተከፍተው ነበር፡፡ የሐረሩ ልዑል ራስ መኮንን ትምህርት ቤትን ለወንዶቹ ልጆች፤ የወይዘሮ የሺ እመቤትን ትምህርት ቤትንም ለሴቶች ያሠራው በወረራው ወቅት ነበር፡፡ (ዛሬ፣ እነዚህ ትምህርት ቤቶች በሌላ መጠሪያ ስም ነው የሚታወቁት፡፡) በጎንደርም፣ የፋሲለደስ ትምህርት ቤትን ሕንጻ ገንብቶ በርካታ ወጣቶችን ለፋሺስታዊ እኩይ ተግባሩ እያዘጋጃቸው ነበር፡፡ ጣሊያን ከሐረር 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ጠመዝማዛ የደንገጎ መንገድ ለወታደርና ስንቅ ማመላለሻ በ1827/28 ሲሠራው፤ ከደባርቅ ወረድ ብሎ ያለውንም የሊማ-ሊሞን ጠመዝማዛ መንገድ ለተመሣሣይ ዓላማ ከ1927-1929 ዓ.ም ባሉት ጥቂት ዓማታት ውስጥ አጠናቋቸዋል፡፡

ጎንደርነት፣ በደርግ ዘመን ክፉኛ በቀይ ሽብር ቸነፈርና አለንጋ ተመቶ ነበር፡፡ ግፈኛው መላኩ ተፈራ የጎንደርን ወጣቶች ለሶሻሊዝም ባዕድ ርዕዮት-ዓለም/አምልኮው ሲል አስፋልት ላይ ረፈረፋቸው፡፡ የጎንደሩ ሰው መላኩ ተፈራ በገዛ ወገኖቹ ላይ ከኔሮና ከግራዚያኒም የማይተናነስ ጭካኔ አሳየ፡፡ ጎንደርነት ከፍተኛ አደጋ ተጋረጠበት፡፡ የጎንደር ወጣቶች በበረሃ እያሳበሩ ወደሱዳን ተመሙ፡፡ አንዲት ጎስቋላ እናት “መላኩ ተፈራ የእግዜር ታናሽ ወንድም፤ የዛሬን ማርልኝ ሁለተኛ አልወልድም!” ያለችው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ በአንፃሩ፣ ሐረርነት በብዛት በቀይ ሽብር አልተጎደም፡፡ በመጠኑም ቢሆን ግን በተለይ የአማርኛና የኦሮሚኛ ተናጋሪ ወጣቶችን ገሏል፡፡ በኮሎኔል ዘለቀ በየነ ይመራ የነበረው የቀይ ሽብር ገዳይ ግብረ-ሃይል በርካታ ወጣቶችን ያለ ፍርድ ገድሏል፡፡ ብቻውን አልነበረም፡፡ የሐረር ተወላጆቹን እነአዲል አሊን ይዞ ነበር፡፡ (አዲል አሊ፣ ኢህአዲግ በግንቦት 26 ቀን 1983 ዓ.ም ሐረርን ሲቆጣጠር ፈርጥጦ ሶማሊያ ሞቃዲሾ ተቀመጠ፡፡) የሐረር ወጣት የሚሰደደውም በጅቡቲ በኩል ነበር፡፡ ብዙ ወጣቶች እግሬ አውጭኝ ብለዋል፡፡ ብልጦቹም፣ “ቪቫህ ደርጎ-ቪቫህ ደርጎ! ይገባሃል ወተቲና ኢርጎ!” ብለው ዘፍነው ዘመኑን አጎንብሰው በጥበብ ተርፈዋል፡፡ ሐረርነት እና ጎንደርነት ብዙ ልጆች በውጭ ሀገራት ስላሏቸው፣ ከውጭ የሚላክ ዶላር (Remittance)ና ወርቅ አላጡም፡፡ ዛሬ አቦከርና አዘዞ የሚገነቡት ምርጥ ምርጥ ቪላዎች ከውጭ አገር በሚላኩ ገንዘቦች መሆኑን ማስታወስ ይገባል፡፡

ከሼክ አባድር ዘመነ ጀምሮ እስልምና በጎንደር እና በሐረር ፀንቶ የቆየ ነበረ፡፡ የሼክ አባድርን በረከት ለማግኘት (ለመዘየር) አንድ ሺህ ኪሎ ሜትሮች በላይ ተጉዘው የጎንደር እስላሞች ሐረር ይመጡ ነበር (መርደቻይ አብር፤ ኢትዮጵያ፤ በዘመነ መሳፍንት) ባለው መጽሐፉ እንደገለፀው፡፡ አንድ ቀን ታዲያ በነዚህ ጎንደሬዎች ድካም ያዘኑት ሼክ አባድር፣ የብረት ዘንጋቸውን አርቀው ሲወረውሩት ተሰወረ፡፡ ከጎንደር ለመጡት በረከት ፈላጊዎችም እንዲህ አሏቸው፤ “ሂዱ፣ ይሄንን ዘንጌን ከአንገረብ ወንዝ ማዶ ታገኙታላችሁ፡፡ እዚያ ሆናችሁ ጸልዩ፡፡ እዚህ (ሐረር) ያለውን በረከት ሁሉም እዚያው (ጎንደር) ታገኙታላችሁ!” አሏቸው፡፡ መንገደኞቹም ዝየራቸውን ፈጽመው ተመልሰው ጎንደር ሲገቡ ዘንጉን ፈለጉት፡፡ ከአንገረብ ወንዝ ማዶም ተሰክቶ አገኙት፡፡ ዘንጉም ሲነቀል ቅዱስ ውሃ ፈለቀ፡፡ በአው አባድርም ትዕዛዝ ሐረርነትና ጎንደርነት አንድን በረከት እየተካፈለ፣ በ1,101 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በየፊናው ሥልጣኔውንና ባሕሉን ሲከተል ለዘመናት ኖረ፡፡ (ያንን ቦታ ከ1966 ዓ.ም በፊት ልዕልት ተናኘ ወርቅ፣ የአባድር እርሻ ልማት ብላ ለበጎአድራጎት ስራ ታሳርሰው ነበር፡፡ ደርግ መጣና በ1967 ዓ.ም ለሕብረተሰቡ ጥቅም ወረሰው፡፡) 

ማጠቃለያ፤
በጎንደርነት እና በሐረርነት መካከል ያለውን ዋነኛ የመንፈስ ልዩነት ማውሳት ያሻል፡፡ ልዩነታቸውም የተገነባው አው አባዲር አትመላለሱ ስላሏቸው ሳይሆን፣ ከግንቦቻቸው እና ከቅጥሮቻቸው አሠራር ጋር በተገናኘ ነው፡፡  የሐረርነት እና የጎንደርነትም ፖለቲካዊ ፍልስፍና የሚያጠነጥነው እዚህም ላይ ነው፡፡ ሐረርነት በአሚር ኑር አማካይነት የሐረርን ጀጎል ሲገነባ፣ ለአሚሮቹ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም ደኅነነትና ሰላም መጨነቁንና መጠበቡን ያሳያል፡፡ “በአሚርነት ክብርና” በተራው “የሐረር ሕዝብ ክብር” መካከል የሠፋ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ልዩነት እንዳይኖር አድርጎ ወጠነው፡፡ በዚህም የተነሳ እስከ ዘመናችን ድረስ እንደምናየው፣ ሐረርነት ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሕዝቡ የስነ-ልቦና ትስስር በጣም የተራራቀ አይደለም፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ በቀላሉ (በአይን ጥቅሻ ፍጥነት) ከፍተኛ መግባባትና መተማመን ይታያል፡፡ መስኪዶች እና ሕንጻዎች በያመቱ በረመዳን ወር ይታደሳሉ፡፡ የፈረሰና የተደረመሰም ካለ በሕዝቡ ትብብር ይገነባል፡፡ ይህም ነገር ለመጤዎችና ለአንዳንድ ጉዳዩን በቅጡ ለማይረዱት ሰዎች “ዘረኝነት ወይም ጠባብነት” ይመስል ይሆናል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ላለፉት 450 ዓመታት ያህል “ለሐረርነትና ለደኅንነት አስፈላጊ ነው” ተብሎ የተያዘ የኑሮ ዘዴ ነው፡፡ ሐረርነትን ከኦሮሞዎችና ከሌሎችም የጦርና የባህል ወረራዎችም የታደጋትም ይኼው (ሕዝባዊነቷ) ነው፡፡

በአንፃሩ፣ ጎንደርነት በአፄ ፋሲል አሳቢነት ስትገነባ የነገሥታቱን እና የሕዝቡን ልዩነት በጉልህ አስምሮበት ነው፡፡ ነገሥታቱ በረጃጅም ግንብ በታጠረውና በምቹ ሁኔታ በተሠራው ቅንጡ ቤተ-መንግሥታቸው ሲኖሩ፣ ሕዝቡ ግን ከግንቡ ውጭ በጎጆ ቤት እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ነገሥታቱ ከሕዝባቸው ደኅንነት ይልቅ የራሳቸውን ክብር አስበልጠዋል፡፡ በዚህም የተነሳ፣ በ1880 የመጣውን የደርቡሽ ጦር ሕዝቡ በትጋት ሳይከላከለው ቀርቶ ከፍተኛ ጉዳት በአብያተ-መንግሥቱ ላይና በአብያተ-ክርስቲያናቱ ላይ ደረሰ፡፡ አሁንም ቢሆን፣ የጎንደርነት ኩራት የሆኑትን የፋሲልን ግንብና አብያተ-ክርስቲያናቱን ለማደስ ሲፈለግ ለጋሾች ተለምነው ነው፡፡ ሕዝቡ የእኔነት ስሜት እንዳይሰማው ስለተደረገ፣ የጎንደርነት ኩራቶች በአግባቡ አይጠበቁም፤ በወቅቱም አይታደሱም፡፡ (ቸር እንስብት!)  

የአዲስጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7፣ ቁጥር 150 (የካቲት 2 ቀን 2005 ዓ.ም) የታተመ ነው፡፡ 

አስተያየቶች