የገናው መልእክት
Solomon Tessema G. /The Editor of: semnaworeq.blogspot.com

ዛሬ በዓለማችን ላይ ከሁለት ቢሊዮን በላይ ክርስቲያኖች እንደሚገኙ ይታመናል፡፡ ሆኖም፣ የገና በዓል መንፈሥ የክርስቲያነች
ብቻ አይደለም፡፡ በወንድማማችነት፣ በፍቅርና እርስ-በርስ በመዋደድ ላይ የተመሠረው የክርስቶስ ትምህርት ዓላማ፣ ሁሉንም ሃይማኖቶች
የሚያጠቃልልና ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ ዓለማችን ታዲያ፣ ወደክርስቶስ መልእክት ምንያህል ተቃርባለች? ይህ ጥያቄ ዓመት አልፎ ዓመት
ቢተካም ለሕሊናችን የሚቀርብ ጥያቄ ነው፡፡ ዘንድሮም ታዲያ ይህንኑ ጥያቄ መልሰን ብናነሳው የሚያጽናና መልስ አናገኝም፡፡ እርግጥ
ነው ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ገና አልተነሣም፡፡ ደግሞም፣ በሰው ልጆች መካከል፣ ዘላቂ ሰላም ገና አልተመሠረት፡፡ በመካከለኛው
አፍሪካ፣ በተለይመ አዛየር ሠላም ደፍርሷል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ የፀደዩ የአረብ አብየት ገና አላበቃም፡፡ እንዲያውም
ሁለት ገናዎችን አስቆጥል፡፡ አፍጋኒስታንና የኢራቅ ውጥንቅጥ ወደአስር ገናዎች ሆኑት፡፡ በቅርባችን በሶማልያም የርስ-በርስ ገጭቱና
አለመረጋጋቱ ሃያ-አራተኛ ገናውን አስቆጥሯል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውም መፋጠጥ የኼው አስራ ስድስተኛ ገናውን ሊደፍን
ወራት ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡
የበለፀጉት አገሮች/ኃያላኑም በኤኮኖሚ/በነገረ ነዋይ ቀውስ ውስጥ ከተዘፈቁ እነሆ አምስት ገናዎች ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም፣
በግሪክ፣ በስፔንና በፖርቹጋል እንደምናየው ከሆነ፣ ችግሩ ከመሻሻል ይልቅ ተባብሶ፣ ብዙዎች የገና ካርድ እንኳን ለመግዣ የሚሆናቸውን
ማህለቅ ማግኘት ተስኗቸዋል፡፡ ነገር ግን፣ ብዙ ሃገሮች የጦር መሣሪያና ትጥቅ አሁንም ያከማቻሉ፡፡ የለየለት የጦርነት ሥጋት አየገነነ
ኼዷል፡፡ የአልቃይዳና የእህት አሸባሪ ድርጅቶቹ ስጋት መኻል ኒውዮርክም ላይ በድጋሚ ተክቷል፡፡ ከሰሞኑ ያየነው የትምህርት ቤት
ጥቃት የአደጋው ደንበኛ ማሳያ ነው፡፡ በሊቢያ፣ ሶርያና በየመን ያለው የአልቃይዳ አልሞት-ባይ ተጋዳይነት ተባብሷል፡፡ በቅርባችንም
የሶማሊያ ሁኔታ “ከድጡ-ወደ-ማጡ” እንደሚባለው ሆኗል፡፡
ይህም ሀሉ ስለተባለ፣ ለዘንድሮው ገና ካፉት ገናዎች የተለየ ግምት የሚሰጠው፣ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የተጀመረው
አዲስ የመሻሻልና የመቀራረብ መንፈስ እየታየ በመሆኑ ነው፡፡ በተለይም በምስራቅ አብያተ-ክርስቲያናት በኩል ያለው መቀራረብ ይበል
የሚያሰኝ ነው፡፡ ክርስቶስ አንድ ቤተ-ክርስቲያን ብቻ መሠረተ፤ አንዲቷ ቤተ-ክርስቲያንም ተከፋፍላ፣ ብዙ አብያተ-ክርስቲያናት ተፈጠሩ፡፡ይባስ
ብሎ ችግሩ በቤተ-ክርስቲያን መሪዎች መካከል ተካሮ ሁለት ፓትረያርክ፣ ሁለት ሲኖዶስና ሁለት ጎራም እስከመፍጠር ደርሷል፡፡ ይህ
ገና፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን ሕመም ፈውሶ ለቤተክርስቲያኗ አንድነትን፣ ለመሪዎቹም መከባበርንና
ፍቅርን፣ ለምዕመናኑም እድገትንና ብልጽግናን ይሰጥልን ዘንድ እንመኛለን፡፡ መከፋፈል ማንንም በምንም ኹናቴ ሊያፀና አይችልም፡፡
የቤተ ክርስቲያን ባለቤት -ክርስቶስ ራሱ እንዳለው፣ “እርስ በርሱ የተከፋፈለ ቤት ሊፀና አይቸልም፡፡” አብያተ ክርስቲያነትም
በዚህ የገና መንፈሥ ወደኋላ ተመልሰው፣ በበረት የተወለደውን የትሑቱን መምህር ትምህርት ቢያስታውሱ፤ ከሚለያዩበት ይልቅ የሚገናኙበት መብዛቱን ሊገነዘቡ ይችላሉ፡፡
ለሰው ልጆች ታላቁ መተሣሠሪያ በኃይል፣ “በጎ ፈቃድ” ነው፡፡ በዚህ የገና መልእክታችንም፣ በሁሉም ሕሊና “በጎ ፈቃድ በሰው ልጆች
መካከል” የሚለውን የመላእክት ዝማሬ፣ በቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያንና በቤተ መንግሥትም መሪዎች፣ በመላው ዓለምና በኢትዮጵያም
ሕዝብ ልቦና እንዲሠርፅ በእጅጉ እንመኛለን፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ
Thanks a lot for your comments.