በነፃነት የማሰብ መብት!
በሰሎሞን
ተሰማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)
“ፀረ-ዘውድና ፀረ-እድገት ኃይሎች፣ “የክፉ ሃሳብ” መፈልፈያዎች ናቸው፡፡” አዲስ ዘመን፣1959/60ዓ.ም
“የጥንቆላና የባዕድ አምልኮ የሚተገብሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለመጀመር “ሃሳብ” ያላቸውም ለፍርድ ይዳረጋሉ፡፡” አዲስ ዘመን፣ መስከረም፣
1957ዓ.ም
በዘመነ ደርግ፤
“የኢትዮጵያ ሕዝብ የፀረ-አብዮት ኃይሎችን “ሃሳብ” ነቅቶ እንዲጠብቅና በብርቱ ክንዱም
እንዲያደባያቸው ደርግ መመሪያ ሰጠ፡፡” አዲስ ዘመን፣ ታኅሣሥ 1967/68ዓ.ም
“የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱንና የኢትዮጵያ አንድነትን ከገንጣዮችና ከቅጥረኞች “ሰይጣናዊ
ሃሳብ” እንዲጠብቅ ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ አሳሰቡ፡፡” አዲስ ዘመን፣ ሰኔ 1979ዓ.ም
በዘመነ ኢሕአዲግ፤
“ሕዝቡ ልማቱን ከፀረ-ልማትና ከፀረ-ሰላም ሃይሎች “ከንቱ ሃሳብ” ነቅቶ እንዲጠብቅ የኢሕአዴግ
ማዕከላዊ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡” አዲስ ዘመን፣ መስከረም 1998ዓ.ም
“ሕዝቡ፣ ከንግዲህ ሽብርተኞችን ገና “ሲያስቡም” ለፍርድ ያቀርባቸዋል፡፡” አዲስ ዘመን፣
ጥር 2001ዓ.ም
ውድ አንባቢያን፣ አንድ ትልቅ ቁምነገር ሳትረዱ አልቀራችሁም፡፡ እርሱም፣ በሦስቱም አገዛዞች
አንድን ነገር ማድረግ ቀርቶ፣ “ማሰብ” ራሱ እንደወንጀል ተቆጥሮ ለፍርድ ያስቀርባል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ዜጎች የፈለጉትን ሃሳብ በነፃነት መናገር ቀርቶ በነፃነት ማሰብም የማይችሉባት ሃገር
ነበረች፤ ናትም፡፡ ሃሳብና አሳቢ ለምን እንደጦር እንደሚፈራ ገና አልታወቀም፡፡ እንደምንገምተው ከሆነ፣ ያው
ከገዢዎቹ የሥልጣን-ጥም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ገዢዎቹ ሁሉ፣ ለሥልጣናቸው ደንቃራ ነው/ናቸው ብለው ያሰቡትን ወይም ያሰቧቸውን ዜጎች
ሁሉ፣ “ፀረ-ማርያም!” “ፀረ-ዘውድና ፀረ-እድገት ኃይሎች፤” ወይም “ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አንድነትን ኃይሎች፤” ወይም ደግሞ፣ “ፀረ-ልማት፣
ፀረ-ሰላምና ሽብርተኛ ሃይሎች” ናቸው ብለው የፕሮፓጋንዳ ታርጋ የመለጠፍ ሥራ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ፕሮፓጋንዳውም፣ ከላይ ባያችሁት
መልክ በገዢዎቹ ልሳን ላይ ያለ-ሃፍረት ታትሞ ይወጣል፡፡
ጉዳዩ ቆየት ያለና ቢያንሰው ቢያንስም አምስት ምዕተ-ዓመታት
ያህል አስቆጥሯል፡፡ ባጠቃላይ ሃሳብ ማሰብ፣ በተለይም ደግሞ “አዲስ
ሃሳብ” ለማሳየት ወይም ለማመንጨት መሞከር፣ “ዝቅ ብሎ ባት፣
ከፍ ብሎም አንገት!” ያስቆርጣል፡፡ ያለ ርህራሔ ሕይወትን ያስገብራል፡፡ ለዚህ ደግሞ የደቂቀ እስጢፋኖስ አሳርና
መከራ ከፍ ያለ ማሳያ ነው፡፡ የፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ቀዳሚ-ቃልም ይህንን ሃቅ በገሃድ ያሳየናል፡፡ “በደቂቀ እስጢፋኖስ
ሰቆቃ በግልፅ የምናየው ግን በእኛ ማህበረሰብ አዲስ ሀሳብ ጠላት ሆኖ መታየቱን ነው፤ ህገ ኀልዮት በህገ አራዊት መደቆሱን ነው፡፡
ሀሳብን በሀሳብ መቋቋም የማይችሉ የስልጣን ጉጉት የአእምሮ ስንኩላን ያደርጋቸው የሚቀናቸውና የሚቀልላቸው የሚጠሉት ሐሳብ ማህደር
የሆነውን ሰው ማጥፋቱ ነው፡፡ የኖረውን ያለውን በግድ ተቀበሉ እየተባለ አዲስ ነገርን ማሰብና መግለጽ አደገኛ ተግባር እየሆነ ይሄዳል፡፡
በዚህም ምክንያት ማሰብን ማስቀረት የማይቻል ቢሆንም ሐሳብን በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ ማውጣቱ ለኢትዮጵያውያን እስከዛሬ አስቸጋሪ ነው፤ ስውርና የተለባበሰ አነጋገር እስከዛሬም ባህላችን ሆኖ የቆየው…፤” ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡ ( ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ “ቀዳሚ ቃል” ላይ የተወሰደ፡፡) ምን ማብራሪያ ያስፈልገዋል?!
ሃቁ ይኼው ነው፡፡ ማሰብ አሁንም ቢሆን ያስወነጅላል፡፡
እኚሁ ሊቅ፣ “አገቱኒ፤ ተምረን ወጣን” ብለው
በመጋቢት 2002ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ እንደገለፁት ከሆነ፣
የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በበርካታ ወንጀሎች የተከሰሱት “ሕጋዊዎቹ” የቅንጅት መሪዎች ከተከሰሱባቸው ወንጀሎች አንዱ (3ተኛው ክስ)፣ መሪዎቹ የትጥቅ ትግል እንዲነሳ “አስበው” የሚል ነበር (ገጽ 69)፡፡ አስበው ምን አደረጉ? ለሚለው ጥያቄ አንዳችም ማስረጃ አልቀረበበትም፡፡
እንኳን ማስረጃ፣ ዋሽቶና ቀላምዶም የሚዘላብድ፣ አንድም “የተገዛ” ምስክር አልቀረበም፡፡ ቁምነገሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ “ማሰብ/ሃሳብ”ራሱ ወንጀል ሆኖ ማስከሰሱ ነው፡፡
ይህ ፀረ-ሕገ መንግሥታዊ
አካኼድ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፣ ለዜጎች የገባውን ቃል ላለማክበሩ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ (1) ከሚለው ውጭ ነው፡፡ አንቀጹ እንዲህ ይላል፤ “ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነጻነት
አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም
ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡” በዚህ
አንቀጽታ ውስጥ በርካታ አሻሚ ነጥቦች አሉ፡፡ ከማሰብም ነጻነት በተጨማሪ ሌሎች መብቶችንም የያዘ ነው፡፡ ስለሕሊና ነጻነትና ስለሃይማኖት ነፃነትም ያትታል፡፡ የሃይማኖት ነፃነትና እምነት አንድ አይደሉም፤ እነዚህ የተጠቀሱት ሀሳቦች አንድ አይደሉም ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ ይቃረናሉ፡፡ ኅሊናና እምነት፣ ወይም ኅሊናና ሃይማኖት፣ ወይም እምነትና ሃይማኖት አንዳንድ ጊዜ አይስማሙም።
ስለዚህም አንድ ሰው የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ ሳለ፣
የፈለገውንና የፈቀደውን እምነት/አምልኮ ሊተገብር ይችላል፡፡ ለሃይማኖቱ ሕግጋትና ለሃይማኖቱ ቀኖናም ሙሉ ለሙሉ ልቡን መስጠት ተስኖት
የሕሊና ነፃነቱ ባቀዳጀው ጎዳና ሊነጉድ ይችላል፡፡ ያን ጊዜ ታዲያ፣ በበፊቱም ሆነ በአሁኑ ዘመን ግለሰቡን ሊያስወነጅለው ይችላል፡፡
ምክንያቱም፣ ሰውየው መሠረታዊው የማሰብ መብት የለውምና ነው፡፡ እንዲሆን ከተፈቀደለትና ከተከለለት አጥር ውጭ ወጥቶ የሚያስብ ሰው
ምክንያት ተፈልጎለት ሸቤ/ከርቸሌ ይገባል፡፡ ዘብጥያ ካልናፈቀው በስተቀር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አሳብን መተግበር፣ ማስተማር ወይም መግለጽ
እንጦሮጦስ ያወርዳል፡፡ የኼው ነው ሃቁ!
ያም ሆኖ፣ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የማሰብንና የመናገር ነፃነት ውልን (The Universal Declaration of Human Rights)ን የፈረመችው በታኅሣሥ 1/1941ዓ.ም
ነበር (አዲስ ዘመን፣ ጥር 5/1951ዓ.ም፤ ገጽ 1 እና 3)፡፡ በውሉም መሠረት ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ሙሉ የማሰብ መብትንና የመናገርንና የመጻፍን ነፃነትን ልታቀዳጅ፣ ያለግድ-በውድ ፈርማለች፡፡
ታዲያን፣ ሕጉ ለምን ኢትዮጵያ ውስጥ ረቂቅ ተዘጋጅቶለትና በቂ ክርክሮች ተደርገውበት ሳይጸድቅ ቀረ? ለምንስ፣ ኢትዮጵያዊያን
ተፈጥሮአዊ የሆነውን የማሰብ፣ የመናገርና የመጻፍ መብታቸውን ለማስከበር ሳይችሉ ቀሩ? የተደረጉት ጥረቶች ሁሉስ ለምን
ዒላማቸውን ስተው የገዢዎቹና የማስታወቂያ ሚኒስትሮቻቸው መፈንጫ ሆኑ? ለምንስ፣ አንዴ “ፀረ-ዘውድ”፣ ሌላም ጊዜ
“ፀረ-አብዮት”፣ በሌላው ወቅት ደግሞ “ፀረ-ልማት” አሳቢዎች እየተባልን ስንፈረጅና ስንታሰር፣ ስንሰደድና በከፋ ድኅነት ውስጥ
ስንታሽ፣ “አሻፈረኝ! አንገፈገፈኝ! በቃኝ!” ማለት ተሳነን? ይህ ጽሑፍ፣ ለነዚህና ለነዚህ መሰል ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት
ጥረት ያደርጋል፡፡
በመጀመሪያም፣ በጥር 4 ቀን 1951ዓ.ም፣ የሕግ መምሪያና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች መማክርቶች
የአንድነት ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ ከጧቱ 4፡15 ላይ ተጀምሮ በነበረው የሁለቱ ምክር ቤቶች ስብሰባ ወቅት ዋነኛ አጀንዳ የነበረው፣
“የማሰብ ነፃነት”ን በተመለከተ ነበር፡፡ ስብሰባውም፣ በወቅቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ም/ፕሬዝዳንት በነበሩት ልዑል ደጃዝማች
(ያን ጊዜ) አስራተ ካሣ የሚመራ ነበር፡፡ በዕለቱም ከነበሩት የሕግ መምሪያ ምክር ቤቱ አማካሪዎች መካከል ፊታውራሪ አመዴ ለማ
(ያን ጊዜ አቶ)፣ ፣ የሕግ መምሪያ ምክር ቤቱ ም/ፕሬዝዳንት የተከበሩ ልጅ ኃይለ ማርያም ከበደ እንዲሁም ባላንባራስ አሸብር ገብረ
ሕይወት ግንባር ቀደም የማሰብ ነፃነትን ደጋፊዎችና ተከራካሪዎች ነበሩ፡፡
በአንፃሩም፣ ከሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የመጡት፣ ለምሳሌ እንደክቡር ደጃ/ በቀለ ሀብተ
ገብርኤል፣ ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ፣ ፊታውራሪ ሐጂ በዳሶ፣ ፊታ/ ደምሴ ከበደና ደጃ/ ደምሴ ወልደ አማኑኤል የማሰብ
ነፃነትን ተቃውመው ተከራክረዋል፡፡ ከሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የማሰብ ነፃነትን የደገፉትና በዋናነት ተጠቃሽ የሆኑት፣ የሐረርጌ
ጠቅላይ ግዛት እንደራሴና ሊቀ ጳጳስ የነበሩት (ያን ጊዜ) ፣ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ እና ክቡር ደጃዝማች መኮንን ደስታ ናቸው፡፡
አቡነ ቴዎፍሎስ አሻሚ የሆነውን ክርክር ፈር ለማስያዝ እንዲህ አሉ፣ “ማንኛውም ሰው የማሰብና ሐሳቡን በቃል ወይም በጽሑፍ የመግለጽ
ሙሉ ነፃነት አለው፤” የሚል ንዑስ አንቀጽ እንዲገባ ሲሉ ማሻሻያ አቅርበው ነበር (አዲስ ዘመን፣ ጥር 27/1951ዓ.ም፤ ገጽ
3)፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም፣ ክቡር ደጃዝማች መኮንን ደስታ በበኩላቸው፣ “ኢትዮጵያ እ.አ.አ በታኅሣሥ
10/1948ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ያዘጋጀውን የሰብዓዊ መብትና የማሰብ ነፃነት ውል ከፈረሙት 89 አገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡
ነገር ግን፣ እነዚህ የማሰብና የመናገር እንዲሁም የመፃፍ ነፃነቶች ለሕዝቡ ሊሰጡት የሚገቡ መብቶቹ ሆነው ሳለ፣ ከአስር አመታት
በላይ ሕጉ ሳይወጣ ዘግይቷል” ሲሉ ወቅሰዋል (አዲስ ዘመን፣ ጥር 5/1951ዓ.ም፤ ገጽ 1)፡፡
በሌላ በኩልም፣ ከሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የመጡት ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘንና ክቡር ደጃ/ች
ደምሴ ወልደ አማኑኤል በየኩላቸው ክርክሩ እንዲቆምና በይደር እንዲታይ ጠየቁ፡፡ በዋናነት ያቀረቡትም ሐሳብ፣ የማሰብ ነፃነት ከሃይማኖት
ነፃነት ጋር የሚጣረስ አንቀጾች ይዟል- ብለው በመስጋታቸው ነው፡፡ ለዚህ ስጋታቸውም አፋጣኝ ምላሽ የሰጡት ፊታውራሪ (ያን ጊዜ
አቶ) አመዴ ለማ ነበሩ፡፡ አመዴ ፈጠን ብለው የማሻሻያ ሐሳባቸውን አቀረቡ፡፡ እንዲህ አሉ፤ “የማሰብ ነፃነትን ከሃይማኖት ነፃነት
ጋር እንዳይዳበል ለማድረግ ካስፈለገ፣ ክፍል 1. ስለማሰብ ነፃነት፤ 1ኛ. ማንኛውም ሰው የሚስማማውን የፍልስፍና ሐሳብ
ለመምረጥ ሙሉ ነፃነት አለው፡፡ 2ኛ. ይህንንም ነፃነቱን ሊቀንሱበት የሚችሉት የሌሎችን መብቶች የማክበር ግዴታዎች፣ መልካም ባሕሎችንና
ሕጎችን አክብሮ የመጠቀም ግዴታዎች ብቻ ናቸው፡፡” ካሉ በኋላ፣ “ስለሃይማኖት ነፃነትም በተመለከተ፣ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት
ለመያዝ ነፃነት አለው፤” ሲሉ አጠቃለሉ፡፡
ሆኖም ግን፣ ማሻሻያ ሃሳቡን ራሱን ብዙዎቹ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት የጎሪጥ ነበር
ያዩት፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን፣ እንደሕግ አውጭው ም/ሚኒስትር ክቡር ብላታ ቅጣው ይታጠቁ የተቆጣም የተናደደም አልነበረም፡፡ “ሕግ
መምሪያውም ሆነ፣ የሕግ መወሰኛው አባላት የማሻሻያ ሐሳብም ሆነ አዲስ ሐሳብ ማመንጨት ያለባቸው፣ በተናጠል በየምክር ቤቶቻቸው እንጂ፣
በሁለቱ ምክር ቤቶች የወል ስብሰባ ላይ/እዚህ አይደለም፤” ሲሉ በዘለፋ ተናገሩ፡፡
ከላይ የቀረበው የማሰብ ነፃነትና የሃይማኖት ነፃነት ማሻሻያ ቀድሞ ያስቀየማቸው ነበሩ፡፡
በተለይም፣ ከሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የመጡትን-ሊቀ ሊቃውንት መሐሪን እንዲህ አሰኝቷቸው ነበር፡፡ ሃይማኖትና ሐሳብ ባይን የማይታዩ
ነገሮች ቢሆኑም ቅሉ፣ ሃይማኖት በአማኙ ዘንድ ውሳኔ ያለው ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ተብሎ ነው - ሃይማኖት የሐሳብ ጭፍራ የሚሆነው?”
ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ለዚህም ይሆናል፣ ባላንባራስ አሸብር ገ/ሕይወት፤ “የማሰብ መብትና ነፃነት ለሰው ልጆች
በሞላ ያስፈልጋል፡፡ ሰው በስጋትና በመሸማቀቅ ከመኖር የሚገላግለው የማሰብ መብቱ ነው፡፡ አለበለዚያ፣ ተሸማቆና አሸምቆ እንዲኖር
ይገደዳል፡፡ ስለማሰብም ነፃነት ሆነ ስለማንኛውም የሰው ልጅ መብቶች ሕግ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥታት ማተሚያ ቤት አቋቁመው
ጋዜጦችን እንዲስፋፉ ማድረጋቸው፣ ብዙኃን መገናኛዎችን ከፍተው ሃሳቦች እንደገለጹ ማድረጋቸው፣ ሙሉ የሐሳብ ነፃነት ለመስጠት ነው፡፡
ሰው ሳያጠፋ መብቱ እንዳይቀነስበትና ነፃነቱን እንዳያጣ የማሰብ መብት ሕግ ሆኖ ሊፀድቅለት ይገባል፡፡ አጥፊዎች ያላግባብ የሐሳብ
ነፃነታቸውን ይጠቀሙበታል ተብሎ፣ አልሚዎች ነፃነታቸውን የሚገፈፉበት ምክንያት የለም፡፡ መጥፎ
ነገር አለ ተብሎ፣ ደግ መታለፍ የለበትም፡፡” ሲሉ አስረዱ፡፡
ከላይ የተባለውም ሁሉ ተብሎ፣ በጥር 13 ቀን 1951ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ ላይ የማሰብ
መብትና ተስፋው ሁሉ ጨነገፈ፡፡ ክርክሩ ቆሞ በድምጽ ብልጫ እንዲቋጭ በቀረበው አቅጣጫ መሠረት፣ በ126 አብላጫ ድምጽ ተደግፎ ክርክሩ
ውድቅ ሆነ፡፡ ግዙፉ የማሰብ መብትም ረቂቅ ሕግ ተሸርሽሮና መንምኖ፣ በጥር 27 ቀን 1951ዓ.ም በቀረበው “የሰው መብት” ረቂቅ
ሕግ ውስጥ፣ በአንቀጽ 14 ላይ ሁለት ንዑስ አንቀፆችን ብቻ ይዞ መጣ፡፡ ዝሆን የሚያክለው የኢትዮጵያዊያንም የማሰብ መብት፣ የትንኝ
ክንፍ የሚያክል ሆኖ ተገኘ (አዲስ ዘመን፣ ጥር 30/1951ዓ.ም፤ ገጽ 2)፡፡ ይኼው እስከዛሬም ድረስ የማሰብ ነፃነት በሕገ መንግሥቱ
አንቀጽ 27/1 ላይ የተደነገገ ቢሆንም፣ በተግባር ግን ደብዛውም አይገኝም፡፡ ይህም ትውልድ ገቢራዊ ሊያደርገው እንደሚታገል እምነቴ-የፀና
ነው፡፡ (መልካም የገና በዓል ይሁንልን!)
በሳምናታዊው የአዲስጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7፣ ቁ.
145 ላይ፤ በታኅሣሥ 27 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣ፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ
Thanks a lot for your comments.