የጀግንነት (የወኔ) ዘይቤ!

በሰሎሞን ተሰማ ጂ. semnaworeq.blogspot.com
ገና
ከሕፃንንታችንም ጀምሮ “ጀግንነት/ወኔ” የሚሉትን ቃላት የሕይወታችን ዋናዎቹ ቃላት እስኪመስሉን ድረስ፣ ከአባቶቻችን አንደበት ስንሰማቸው
ነው የደግነው፡፡ “ወኔ” የሚጠይቀውን የገና ጨዋታ ወይም የኳስ ቅብብሎሽ ስንጫወት፣ ከሌላ ልጅ ጋር ብንሰዳደብ ወዲያው ክብራችን ተነክቶ፣ ወይም
ደግሞ ካላቅማችን በአፍ እልፊት የሌላውን ክብር ቀንሰን እንደዋዛ ማምለጥ አልነበረም፡፡ ከመካከላችን አንዱ ተነስቶ ምራቁን ከመዳፉ
ላይ “ቱፍ!” ብሎ፣ መዳፉን ወደታች እየዘቀዘቀ የአንደኛውን ልጅ ስም እየጠራ፣ “የእከሌ አባት ደም እንደዚህ ፈሰሰ!” ሲል ጠቡን
ያውጃል፡፡........
በአንድ የዘመነ መሳፍንት ጦርነት ወቅት፣ ጦራቸው ሊሸነፍ እንደሆነ የገባቸው አንዱ መስፍን
ሊሸሽ የነበረውን ፊታውራሪ አዩትና መላ ዘየዱ፡፡ እቁባቱን/የጭን ገረዱን አስመጥተው አፋፍ ላይ ቆማ እንድትሸልል አደረጓት፡፡ ፊታውራሪውም
ውጊያውን ቀጥሎ በርሱ የጦር ግንባር በኩል ከፍተኛ ድል ተገኘ፡፡ ‘እንዴት ብሎ ወንድ በጭን ገረዱ ፊት ይሸሻል?’ ያ ፊታውራሪ ሲያስበው ነውር ሆነበትና ፍርሐቱን ተቆጣጥሮ ተዋጋ፡፡ አሸነፈም፡፡ (እልልል........!)
በሌላ በኩል ደግሞ ይኼኛውም ዓይነት “ወኔያም” አለ፡፡ ሰውዬው ቆሞለት ሲዋጋለት የነበረው ጦር ተፈታ፤ ተሸነፈ፡፡ ስለዚህም፣ ይኼኛው
ተዋጊ መላ ዘየደ፡፡ ባቅራቢያው ወዳለው መንደር ገብቶ ቀሚስ ለበሰ፤ ሻሽም አሠረ፡፡ ሚኒቅ-ሚኒቅ እያለ ሲወጣ ያየው ያሸናፊው
ወገን ወታደር ተጠግቶ፣ “አንተ ነህ ወይስ አንቺ ነሽ?” አለው፡፡
“ኧረ አንቺ ነኝ” አለ አይነ-ደረቁ ሰው፡፡ “ቀሚሱ ተልጦ ይታይ ወይ!” አለው፡፡ ተስማማ፡፡ ከቀሚሱም ሥር የወንድ “ጉዱ” ታየ፡፡
“እና፣ይኼ ምንህ ነው?”አለው፡፡ አይነ-ደረቁም ሰው፣ “በውነት ካለዛሬም አላየሁት!” ሲል ሽምጥጥ አድርጎ ካደ፡፡
(የዚህ ሰው መጨረሻ ምን እንደሆነ እስከዛሬም ድረስ አላረጋገጥንም፡፡ ኡ!-ኡ!-ኡ! ሳይል ግን አልቀረም፡፡) “የወኔ-ቢስነት”
ዋጋውን እንዳገኘ አይጠረጠርም፡፡


“አንተ የዘፈን ወኔያም፣ የመንደር ተባዕቱ፤ ተባዕቱ፤
ጦር ሜዳ እስኪንይህ፣ እንደድግስ ቤቱ፡፡”
ለሀገር
እድገት የሚያተጋው አይነትም “ወኔ” ይላል ብርሃኑ፣ “የጥንቱም ሆነ ያሁኑን ገበሬና ላብ-አደር የሚመለከት ነው፡፡ ወፍ “ጭ-ጭ!”
ሳይል በጧት ተነስቶ፣ ባጭር ታጥቆ፣ እህል ሳይቀምስ ቤተሰቡንና ወገኖቹን ለመመገብና ለማገልገል ሲል፣ ቁርና ሐሩርም ሳይበግረው/ሳይፈራ
የቀኑን ሥራ በሙሉ ልብ እንዲጋፈጥ የሚገፋፋው፣ ያ ካባቶቹ የወረሰው የእድገትና የመሻሻል ወኔ እንደሆነ፤” ያትታል፡፡
በአጠቃላይ
ሲታይም፣ የሰው ልጅ ሐሞቱ ካልተቆጣ፣ ወኔውም ካልገነፈለ በተቀር፣ በድንና መንፈሱም ሙት የሆነ ፍጡር እንደሆነ ይታመናል፡፡ ገና
ከሕፃንንታችንም ጀምሮ “ጀግንነት/ወኔ” የሚለውን ቃል የሕይወታችን ዋናዎቹ ቃላት እስኪመስሉን ድረስ ከአባቶቻችን አንደበት ስንሰማቸው
ነው የደግነው፡፡ በእኛ ሕፃናቶች በነበርነውም ሆነ፣ በታላላቆቻችንና በእድሜ በገፉትም አዛውንቶች ዘንድ እሊህ “ጀግንነት/ወኔ”
የተባለሉት ቃላት በጣም ትልቅ ግምት ነበራቸው፡፡ እጅግም የሚከበሩና ባለ“ወኔ”ውንም የሚያስከብሩ እንደነበረ አይረሳንም፡፡ ስለወኔም
ክብር ሲባል ብዙ ክፉም ሆኑ ደግ ድርጊቶች ይፈፀሙ እንደነበረ ተመልክተናል፡፡ ምን ማየት ብቻ፣ እኛም በግላጭ ተካፋዮች ሆነን አልፈንበታል፡፡
ለምሳሌ
“ወኔ” የሚጠይቀውን የገና ጨዋታ ወይም የኳስ ቅብብሎሽ ስንጫወት ሳለ፣ ከሌላ ልጅ ጋር ብንሰዳደብ ወዲያው ክብራችን ተነክቶ፣ ወይም
ደግሞ ካላቅማችን በአፍ እልፊት የሌላውን ክብር ቀንሰን እንደዋዛ ማምለጥ አልነበረም፡፡ ከመካከላችን አንዱ ተነስቶ ምራቁን ከመዳፉ
ላይ “ቱፍ!” ብሎ፣ መዳፉን ወደታች እየዘቀዘቀ የአንደኛውን ልጅ ስም እየጠራ፣ “የእከሌ አባት ደም እንደዚህ ፈሰሰ!” ሲል ጠቡን
ያውጃል፡፡ በዚያን ጊዜ፣ ጠብታ ምራቁ መሬቱን ሳይነካ በፊት፣ ተሽቀዳድሞ እፍስ አድርጎ የጠበኛውን ሰውነት በምራቁ ካልቀባው፣ ያ
ስሙ የተጠራ ልጅ ከ“ወኔያምነት” መደብ ወጥቶ ወደር የሌለው “ቦቅቧቃ ነው” ተብሎ መዘባበቻ ይሆናል፡፡ ያኛውም ኮበሌ፣ ምራቁን
ተቀብቶ ዝም ካለ/ያለ እንደሆነ፣ “ፈሪነቱን” አረጋገጠ ማለት ይሆናል፡፡ ከዚያማ ትንሽ-ትልቁ በስድብም በኩርኩምም ያቀምሰዋል፡፡
“ወኔ-ቢስነት” በሌሎች ዘንድ መናቅንና መዋረድን ያስከትላል፡፡
ሆኖም፣
በእልህና በልበ-ሙሉነታችን ተነሣስተን፣ ክብራችን ለመጠበቅ፣ የአባታችን ደም እንዳይፈስ በ“ወኔ” ተነሳስተን ብንፈነከት ወይም ብንጎዳ፣
ወይም ቀንቶን አሸንፈን ወደቤታችን ብንሔድ በጣም አናዝንም፡፡ ቤተሰቦቻችንም ያን ያህልም አይቆጡንም፡፡ “ምንም አትይ፣ ወኔያም
ብጤ ነሽ!” ተብለን ክብርንና ሞገስን እናገኛለን፡፡ ወኔያም ሰው አሸነፈም-ተሸነፈም ክብር አለው፡፡ ጠላቱ እንኳን ሊቀብረው ይመጣል፡፡
ገብረ ክርስቶስ ደስታ “ሀገሬ” በሚለው ግጥሙ ውስጥ “ጠላትም አንዳንዴ ይመጣል መቃብር፤ ባላጋራም ቸር ነው፣ ያገር ልጅ ሲቸገር፡፡”
ያለው ጠበኛው “ወኔያም” ከሆነ ብቻ ነው፡፡ “ከበላይ ዘለቀ ከተሰቀለው፣ ይሻላል ሽፈራው-ዠማ የቀረው!” የሚለውም ግጥም እንደአፄ
ቴዎድሮስ ጠመንጃውን ጠጥቶ የሞተውን የመርሐቤቴውን “ወኔያም” አርበኛ ታሪክ ያስታውሰናል፡፡ ሽፈራውን ጠላቶቹ ሳይቀሩ በክብር አልቅሰው
እንደቀበሩት የሕይወቱ-ገድል ያብራራል፡፡
በዕለት
ተዕለት ኑሮአችንም እንዳየነው ከሆነ፣ ውኃ ልትቀዳ ወንዝ ወርዳ በአሽሟጣጮች ዐይን ሚስቱ የተዘለፈችበትም አዳኝ
“ወኔያም”፣ በነጋው ጧት ወደጫካ ተጉዞ ትልቅ አውሬ በመግደል፣ “ወኔያምነቱን” ወይም “ጀግንነቱን” ካስመረቀላት በኋላ ጆሮውን
ተበስቶ ሎቲውን ሲያደርግ፣ ሚስቱንም ስለክብሯ ያለወረፋ ወኃ እንድትቀዳ ያደርጋታል፡፡ ዘመኑ እንደዚያ ነበር፡፡ እሊህ ምሳሌዎች፣
የ“ወኔ”ን ነባራዊ ትርጉምና የ“ጀግንነት”ን ዘይቤም በኢትዮጵያዊ ቀልብ ለመግለጽ የሚያስችሉ መሆናቸውን እንተማመናል፡፡ ሆኖም ግን፣
ይህ ከላይ የቀረበው ሃተታ ከኢትዮጵያ ባሕል፣ ትውፊትና ታሪክ አንጻር ብቻ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡
ስለሆነም፣ ከጠቅላላው የፍልስፍና
አኳያ የ“ጀግንነት”ን ወይም “የወኔን” ዘይቤ እንደሚከተለው እናየዋለን፡፡ በቅድሚያ ግን እያለዋወጥን “ጀግንነትና ወኔ” ስንል፣
የእንግሊዝኛውን (Courage እንጂ Heroism) አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡ “ጀግና” ስንል ግለሰቡን ሲሆን፣ “ጀግንነት”ም ስንል
“ምግባሩ”ን ለማመልከት እንደሆነ ለአንባቢያን ማውሳት የግድ ይላል፡፡ ስለጀግናና ስለጀግናውም አምልኮ ምንነት ለማንበብ የሚሻ ካለ
የThomas Carlyleን “Heroes and Hero Worship” የተባለውን መጽሐፍ ቢያነብ ጥሩ እውቀትን ይገበያል፡፡ ካርላይል፣
በስድስት ገላጭ-የንግግር ምዕራፎች (Lectures) አማካይነት ስለጀግናና ስለጀግናው አምልኮ ምንነት በዝርዝር አቅርቧቸዋልና፣
አሊህን እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ገለፃዎቹን አንባቢያን ማየት እንዳለባቸው ልናስታውስ እንወዳለን፡፡
ለመሆኑ የጀግንነት (የወኔ) ዘይቤ ስንል ምንድነው?

አሪስቶትል በበኩሉ፣ “Nicomachean
Ethics (ኒኮማቺያን ኤቲክስ)” በተባለው ጥራዙ በ3ተኛው መጽሐፉ ውስጥ (ከቁጥር 1106 እስከ 1117 ድረስ ባሉት አንቀፆች)
በሠፊው ስለጀግንነት ዘይቤ ያትታል፡፡ እንደአሪስቶትል አባባል ከሆነ፣ “ጀግንነት ማለት አንድ ሰው ተግባራዊ የሆነውን ፍርዱን የሚያሳይበት
ጥበብ ነው፡፡” በማስከተለም እንዲህ ይላል፣ “ሁሉንም ነገር የሚፈራ ሰው፣ ወደር የለሽ ፍርሐት ስላለበት አቋም ለመያዝ ይፈራል፡፡
ስለዚህም፣ ቦቅቧቃ ነው፡፡” በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ምንም ነገር የማይፈራና ውስጡ ፍርሐት ያልፈጠረበት ከሆነ፣ ማንኛውንም አደጋ
ፊት-ለፊት የሚጋፈጥም ከሆነ ጅልና ደደብ ነው፤” ሲል ይዘልፈዋል፡፡ በመሆኑም፣ ትክክለኛውና ላቅ ያለው የጀግንነት ምግባር የሚገኘው፣
ልክ-በሌለው በራስ መተማመንና ልክ-በሌለው ቦቅቧቃነት ሳይሆን፣ መሀከለኛውን መስመር መርምሮ በመጓዝ ነው፤” ይላል፡፡ ነገሩን በምሳሌ
ማስቀመጡ ይበጀናል፡፡ አንድ ባዶ እጁን ያለ ሰው አስር ሰዎች ሊያጠቁት ሲመጡ ካልሸሸ፣ ጀግና ሳይሆን “ጀርጃራ” ይሆናል፡፡ አንድ
ባዶ እጁን ያለ ሰው ሲመጣበትም ከሸሸ፣ እርሱ “ቦቅቧቃነቱን” እያሳየ ነው፣ ለማለት ነው-የፈለገው፡፡ ስለዚህም፣ የጀግንነት ዘይቤ
መሠረቱ ያለው ከመጠን በላይ በራስ በመተማመንና ባለመፍራት ሳይሆን፣ አገናዝቦ የመጣውን ችግር/መከራ በድል አድራጊነት በመወጣቱ
ላይ ነው፡፡
አሪስቶትል እንደሚለው ከሆነ፣ የጀግንነት
ዘይቤ ልክ የሚሆነው ጀግናው ሦስት መመዘኛዎችን ካሟላ ነው፡፡ አንደኛ፣ ሰውዬው የቆመለት ትክክለኛ ዓላማ ሲኖረው ሲሆን፤ ሁለተኛው
ደግሞ፣ በትክክለኛ ፀባይ/ባሕሪ ከተከወነና ከተደረገ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃም፣ በትክክለኛው ዝንባሌ ለትክክለኛው ግብ ከተፈፀመነ
ነው፡፡ አለበለዚያ፣ “ጀግንነት ሳይሆን ጅልነት መሆኑ አይቀሬ ነው፤” ሲል ያስተምራል፡፡ ወደመድረሻ ግባቸው በተሳሳተ ዓላማና በስሕተተኛ
ባሕሪ (ማለትም በጭካኔ፣ በግፍና በአድሏዊነት) የሚሄዱ ሰዎች፣ “የጀግንነትን ካባ ፈፅሞ አይጎናፀፏትም፤” ለማለት ነው የፈለገው፡፡
በዚህም አተያይ መሠረት ስንቶቹ ተንኮለኞችና መሠሪዎች “በጀግንነት ካባ” ምትክ፣ “የጅልነት ዳባ” እንደለበሱ ማስታወሱ ይበጃል፡፡
በስህተት ጎዳና እብስ ብለው እየሄዱ ሳለ፣ በቲፎዞዎች ብዛት ብቻ “የለውጡ ጀግና፣ የሕዳሴው ጀግና!” እየተባሉ መሞካሸታቸው፣ ቆም
ተብሎ ሊመረመር እንደሚገባው ልናስታውስ እንወዳለን፡፡
ከአሪስቶትል አስተምህሮት ጋር በአብዛኛው
የሚመሳሰል ሃሳብ ወዳለው ቅዱስ አኳይናስ የጀግንነት እሳቤ እንሻገር፡፡ “Fortitude” በተባለው መጽሐፉ፣ በጥያቄ ቁጥር
123 ላይ እንደሚያትተው ከሆነ፣ የአሪስቶትልን የጀግንነት ዘይቤ የጋራል፡፡ “ጀግንነት ማለት ፍርሐት አልባ መሆን ሳይሆን፣ በአደገኛ
ኩነቶች ውስጥ ትክክለኛውን ፍርድ መበየን” እንደሆነ ያምናል፡፡ የተጋነነና ያልተገባ ስሜታዊነትን ማሳየት በተአምር ወደጀግንነት
ሳይሆን፣ አንድም ወደ ጭካኝነት/አንባገነንነት ወይም ደግሞ ወደለየለት ፍርሐት/ቦቅቧቃነት ይወስዳል ሲል ያትታል፡፡ በመቀጠልም፣
“ሁሉም ሰው እራሱን ከምንም በላይ ይወዳል፡፡ ነገር ግን፣ ፍቅርና መረዳት ያለው ሰው ከራሱ ጉዳት ይልቅ የሌሎችን መዳን ስለሚያስቀድም፣
ከፍተኛ የሆነ ጀግንነትን ያሳይል፡፡ በመሆኑም ጀግንነት ማለት “መጋፈጥ” ሳይሆን፣ በምክንያት ላይ የተመሠረተ ራሮትን በአግባቡ
ማንፀባረቅ እንደሆነ ያሳስባል፡፡
በ1978 እ.አ.አ ባሳተሙት መጽሐፋቸው
ላይ፣ ቮን ራይትና ፉት በበኩላቸው፣ ስለጀግንነት ምንነት ሲገልጹ፣ “ጀግንነት ማለት ፍርሐትን የመቆጣጠር ወይም በፍርሐት ላይ የበላይነትን
የመቀዳጀት አቅም ነው፡፡ ስለሆነም፣ ትክክለኛው ጀግንነት የሚለካው ጨርቅን ጥሎ በመጋፈጥ ችሎታ ሳይሆን፣ በውስጣችን ያለውን መጠነኛ
ፍርሐት ተቋቁሞ ወዳሰቡት ድል በመድረስ እንደሆነ ያትታሉ፡፡ በመቀጠልም እንዲህ ሲሉ ጥሩውን/ዋን ጀግና ይገልፁታል/ይገልፁዋታል፡፡
እርሱ/እርሷ “ለመፈርጠጥ እየፈለገ ወይም እየፈለገች ሳለ ፍርሐቱን/ቷን ተቋቁሞ/ተቋቁማ የሚገኝ/የምትገኝ ከሆነ/ከሆነች የጀግንነት
ክብር ይገባዋል/ይገባታል፤” ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ዋሊስ የተባለው የስነ ልቦና ሊቅ በበኩሉ፣ “ጀግንነት ማለት የቦቅባቃነት ታቃራኒ
አይደለም!” ይልና፤ ቦቅቧቃነት ማለት “በፍርሐት ማቅ ተጀቡኖ የመታወክ ዝንባሌ ነው” ይለናል፡፡ በሌላ በኩልም፣ ጀግንነት ማለት
የፍርሐትን ስሜት ከአእምሮ የማጥፋትና በልበ-ሙሉነት የመገኘት ዝንባሌ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
ማጠቃለያ፤
ጀግንነት ወይም ወኔ ማለት የላቀ
ምግባራዊነት ሲሆን በመከራም ሆነ በጭንቅ ወቅት መዝኖና አመዛዝኖ በፍርሃት ላይ በትክክሉ ድልን መቀዳጀት ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ጀግንነት
ማለት እንደእነሰሳቱና እንደሕፃናቱ አልቦ-ፍርሐት መሆን ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን፣ ፍርሐትን ተቆጣጥሮ ለለውጥና ለድል መትጋት
ነው፡፡ ፍርሐት በቅዱስ መጽሐፍትም ሆነ በስጋዊ ድርሳናት በጎ ትርጉም የለውም፡፡ በአዲስ ኪዳን ላይ በጀልባ ሲጓዙ ሳለ፣ የባሕሩ
ወጀብ አስደንግጧቸው “መምህር ሆይ አድነን!” እያሉ የጮኹትን ደቀመዛሙርት እንዳሳሰባቸው፣ የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል እምነት ያለው
ሰው አይምቦቀቦቅም፡፡ በዚያም ላይ፣ ቦቅቧቃነት ሀጢያት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን፣ በአጉል ጀብደኝነትም ተገፋፍቶ፣ “ተጋፋጭ መሆንም”
ጅልነት/ጀርጃራነት እንጂ፣ በምንም መልኩ ጀግንነት ሊሆን አይችልም፡፡ (“ዘመናችንን የኢትዮጵያዊ ጀግንነትና ወኔያምነት ዘመን ያድርግልን!”
እያልን እንሰናበችኋለን፡፡ ቸሩን ሁሉ ይግጠማችሁ!)
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ
Thanks a lot for your comments.