ሻምበል አበበ ቢቂላ፤

የኢትዮጵያ አልማዝ፣ የአፍሪቃ እንቁ! 

(ክፍል 1) በሰሎሞን ተሠማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)

“በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ዋናው ጉዳይ ተሳትፎ ነው፡፡ አሸናፊነት ከትጋት፣ ከልምድና ከወኔ የሚመጣ ነው፡፡” ይህንን ቃል በተደጋጋሚ የሚናገረው ስዊድናዊው የአበበ ቢቂላ አሰልጣኝ ሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን ነበር፡፡ 


“....በዘመናችን ያቋቋነው የስፖርት ድርጅት፣ ዛሬ የመጀመሪያውን የድል አክሊል ሲያገኝ በማየታችን ደስ ብሎናል.....መጪው ትውልድ የበለጠ ድልና ዕድል ለማግኘት መንገዱ ተከፍቶለታ.....” ቀ.ኃ.ሥ. (አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 16 ቀን 1966 ዓ.ም፤ ገጽ 1)፡፡

 
ንጉሡ ያሉት ትክክል ነበር፡፡ አልጋ ወራሽ ሳሉ በ1924 እ.ኤ.አ ፓሪስ ላይ የተደረገውን የኦሎምፒክ ውድድር በታዛቢነት ተጋብዘው ነበር፡፡ የመዝጊያው ዕለት በማራቶን ውድድር ያሸነፈው ፊላንዳዊ አትሌት፣ ስሙ ኤ.አ. ስቴንሮስ ይባላል፤ 2፡41፡22.6 ሰዓት ሲገባና ስታዲዮሙ ሲናወጥ አይተው ፈገግ አሉ፡፡ “እኛ ኢትዮጵያዊያንም ከዚህ በተሻለ ሰዓት መግባት እንደምንችል አሳያቸዋለሁ!” ሲሉ ለራሳቸው ዛቱ፡፡ ከፓሪስ ከተመለሱ ከሁለት ዓመት በኋላም ለኢንተርናሽናል ኦሎምፒክ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ስም የአባልነት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ሆኖም፣ የኢንተርናሽናል ኦሎምፒክ ኮሚቴው ፕሬዝደንት ሄነሪ ዲ ቢዬ-ላቶ፣ “አፍሪካዊያን በመጀመሪያ ስፖርትን በየአገሮቻቸው ማዘውተርና መማር አለባቸው፤” በሚለው ደብዳቤያቸው ውስጥ፣ “ለኢትዮጵያም ቦታ የለንም!” ሲሉ ፊርማቸውንና ማህተማቸውን አሰፈሩበት (ሮማን የወረረ ጀግና፣ ገፅ 64-5)፡፡ 


በመሴ ሄኔሪ ምላሽ፣ ንጉሡ ተናደዱ፤ ተቆጩ፡፡ ስለዚህም፣ እስከሜልቦርን ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ድረስ ለሰላሳ ዓመታት ያህል ታግሰው ቆዩ፡፡ የጦር ሰራዊትንና የፖሊስ ሠራዊት ሻምፒዎናዎችንም ሲያቋቁሙና ሲያደራጁ ቆዩ፡፡ በሜልቦርን ኦሎምፒክም ላይ ትልቁ ውጤት ማሞ ወልዴ በአስር ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር የአራተኛነት ደረጃን ማግኘቱ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ አንድም ሜዳሊያ አላገኘችም ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር፣ የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ቡድን የመራው አሠልጣኙ ሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን “በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ዋናው ጉዳይ ተሳትፎ ነው፡፡ አሸናፊነት ከትጋት፣ ከልምድና ከወኔ የሚመጣ ነው፤” ያለው፡፡ እውነቱን ነበር፡፡ ከሜልቦርን ተሳትፏቸው መልስ እነባሻዬ ፈለቀ፣ እነዋሚ ቢራቱና እነማሞ ወልዴ በጦር ሠራዊቱ የስፖርት ውድድሮች ላይ የበላይነትን ተቀዳጅተው ነበር፡፡  


አበበ ቢቂላ ለሮም ኦሎምፒክ ተሳትፎ ባጋጣሚ ነበር የሄደው፡፡ አበበ ከወር በፊት ማራቶንን 2፡21፡23 ሮጧል፡፡ ያ ማለት፣ እያንዳንዱን ኪሎ ሜትር 03 ደቂቃ 23 ሴኮንድ ሮጦታል ነው፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት በሄልሲንኪው ኦሎምፒክ ዛልቶክ በተባለው የቼኮዝሎቫኪያው ሯጭ ተይዞ የነበረውን 2፡23፡03 የኦሎምፒክ ሬኮርድ አሻሽሎታል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን፣ ወታደር ዋቅጂራ 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ገደማ ስለገባ ከአበበ ቢቂላም የተሻለ ሰዓት ነበረው (ሮማን የወረረ ጀግና፣ ገፅ 120)፡፡ ያም ሆኖ፣ ሻለቃ ኒስካኔን አበበን ወደሮም ይዞት ቢሄድ ይወድ ነበር፡፡ ሆኖም፣ “በዕድሜው ከሌሎቹ ይልቅ ልጅ ነውና ለቀጣዩ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሊሳተፍ” ስለሚችል፣ በዚህኛው ውድድር ሠላሳ ሰባት ዓመት የሞላቸው ዋቅጂራና ዋሚ ቢራቱ ቢሄዱ የተሻለ እንደሆነ ከረዳት አሰልጣኙ ፍቅሩ ኪዳኔ ጋር ወሰኑ፡፡ 


አሰልጣኙ ኒስካኔንና አትሌቶቹ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰው ወደአውሮፕላኑ ሊገቡ በሰልፍ እየተጠባበቁ ሳለ፣ አንድ ጂፕ አቶ ይድነቃቸው ተሠማንና ረ/አሰልጣኙን ፍቅሩ ኪዳኔን አሳፍራ እየከነፈች መጣች፡፡ ኒስካኔን አጠገብም ደርሳ ቆመች፡፡ ይድነቃቸውና ፍቅሩ ተደናግጠዋል፡፡ ሻለቃ ኒስካኔን ጥሩ ዜና ይዘው እንዳልመጡ ገምቷል፡፡ “ምን ሊሆን ይችላል?” እያለ ሲያውጠነጥን ጥቂት ሴኮንዶችን ፈጀ፡፡ ያንን ቅፅበት የራምባሊ መጽሐፍ እንዲህ ሲል ተርኮታል፤


“ሻለቃ! ችግር አጋጥሞናል፡፡” አለ ይድነቃቸው፡፡
“እንዴት?” ሲል ጠየቀ ሻለቃ ኔስካኔን፡፡
“ዋሚን አደጋ አጋጠመው፡፡ ቁርጭምጭሚቱ ተሰብሯል፡፡”
“ቁርጭምጭሚቱ?!” ኒስካኔን ሊያምን አይችልም፡፡ “እንዴት?” ይድነቃቸውና ፍቅሩ ጥያቄውን ማን እንደሚመልስ የሚመካከሩ ይመስል ተያዩ፡፡
“እግር ኳስ ሲጫወት ነበር፣” አለ ይድነቃቸው፡፡
“እግር ኳስ?!”
“አዎን፤ ሆስፒታል ነው ያለው፡፡ ራጅ ተነስቷል፡፡ ግን......” ፍቅሩ ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡ “ዶክተሩ ቁርጭምጭሚቱ ቶሎ የመዳን ዕድል እንደሌለው ነግሮናል፡፡”
ኒስካኔን በመጀመሪያ አውሮፕላኑን፣ ቀጥሎ አዳዲስ ጃኬቶቻቸውን እንደለበሱ በተስፋ የሚጠባበቁትን ሯጮች ከተመለከተ በኋላ፤ “አበበን በፍጥነት አምጡልኝ፡፡ ከኛ ጋር ይዘነው እንሄዳለን፣” ሲል አዘዘ (ሮማን የወረረ ጀግና፣ ገፅ 120-1)፡፡    


አበበ ቢቂላ ማነው? ከየት ተነስቶ ለኦሊምፒክ የማራቶን ጀግናነት በቃ? እሰቲ ጥቂት እንበል! ሻምበል አበበ ቢቂላ ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም (በዚያን ጊዜው አጠራር) በሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ በደብረ ብርሃን አውራጃ፣ በዋዩ ወረዳ (ያሁኗ ደነባ ከተማ አቅራቢያ) በጂቶ ቀበሌ ተወለደ፡፡ አባቱ አቶ ቢቂላ ደምሴ የተባሉ ሲሆኑ፣ በአምስቱ ዓመት የኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት ወቅት አርበኛ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ በንጉሠ ነገሥቱም ዘንድ በአርበኝነታቸውም የታወቁ ነበሩ (ሮማን የወረረ ጀግና፣ ገፅ 23)፡፡ እናቱ ደግሞ ወ/ሮ ውድነሽ በነበሩ የሚባሉ የጅሩ ሴት ናቸው፡፡ እናቱንና አባቱን ሲረዳ ካደገ በኋላ፣ ለአገሩና ለንጉሠ ነገሥቱ በወታደርነት ሞያ ለማገልገል በመጀመሪያ በአስራ አምስት ዓመቱ መጣ፡፡ እድሜው ለጋ ስለነበረ አንቀጥርህም አሉት፡፡ ወደጂቶ ተመልሶ አምስት አመታት በግብርና ሞያ ቆየ፡፡ በድጋሚ ወደአዲስ አበባ መጥቶ ሚያዝያ 14 ቀን 1945 ዓ.ም በክብር ዘበኛ ሠራዊት ውስጥ ተቀጠረ (አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 16 ቀን 1966 ዓ.ም)፡፡ 


አበበና የክብር ዘበኛ ሠራዊት አባላት በሳምንት ሁለት ቀን፣ በአካል ብቃት አሠልጣኙ ሻለቃ ኒሽካኔን አማካኝነት ስፖርት የመስራት ግዴታ ነበረባቸው፡፡ በ1948 መባቻ ላይ ከሜልቦርን ኦሎምፒክ ተሳትፈው የሚመለሱትን የክብር ዘበኛ አትሌቶች (እነማሞ ወልዴና ዋሚ ቢራቱ፣ እነንጉሴ ሮባና ሌሎችም ወደአዲስ አበባ ከገቡ በኋላ፣ በቀጥታ እነአበበ ቢቂላ ስፖርታዊ ልምምድ ወደሚያድረጉበት ጃንሜዳ መጥተው አቀባበል ሲደረግላቸው ይመለከት ነበር፡፡ አትሌቶቹ ጀርባ ላይ በእንግሊዝኛ የተጻፈውን “ETHIOPIA” የሚለው ጽሑፍ ስላልገባው ጠይቆ ተረዳ፡፡ የሥራ ጓደኞቹም፣ “በእንግሊዝኛ ቋንቋ “ኢትዮጵያ” ነው የሚለው፡፡ እነዚህ አባሎቻችን፣ ኢትዮጵያን በዓለም የስፖርት አደባባይ የወከሉ ጀግኖች ናቸው፤” ሲሉ አስረዱት፡፡ አበበ የመንፈስ ቅናት ያዘው፡፡ “እኔም እንደነሱ ጀግና እሆናለሁ!” ሲል ዛተ፡፡ ባልደረቦቹ ሳቁበት፤ አፌዙበት፡፡ እስከዚያን ዕለት ድረስ እንደቀልድ የሚያዘወትረው ስፖርት ይሄንን ያህል ብሔራዊ ክብርን የሚያጎናፅፍ ስለመሆኑ ፈፅሞ አያውቅ ነበር፡፡ ያን ዕለት ታዲያ፣ የአበበ መንፈስ ተነቃቃ (የማራቶን ጀግኖች አበበና ማሞ፣ ገጽ 20)፡፡


አበበ የሃያ አምስተኛ ዓመት ልደት ዘመኑ ላይ፣ ማለትም 1949 ዓ.ም በሳዛኝና በአስደሳች ሁናቴ ነበር የወጣው፡፡ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ አባቱን እስከወዲያኛው ተሰናበተ፡፡ ሀዘኑ ጥልቅ ነበር፡፡ በብዙ መልኩም በአበበ ሰብዕና ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ ታማኝነትን፣ አክብሮትን፣ እልክንና ወኔን ያሰረፁበት አቶ ቢቂላ ደምሴ ናቸው፡፡ ከሁሉ በላይ ፍቅርን የድል አድራጊነት መንፈስን በሰራ አካላቱ የዘሩበት አባቱ ናቸው (የማራቶን ጀግኖች አበበና ማሞ፣ ገጽ 71)፡፡ በሌላ በኩል፣ በዚሁ ዓመት “ብቸኝነት ደህና ሁኝ!” ብሎ የትዳር ጓደኛውን ወ/ሮ የውብዳር ወልደ ጊዮርጊስን አገባ፡፡ ትዳራቸውም ስድስት ልጆች ያፈራ ሲሆን፣ ሦስት ወንዶችንና አንዲት ሴት ልጁንም በአጸደ ሕይወት ኖሩ በሥሥትና በሥርዓት አሳድገዋል (የማራቶን ጀግኖች አበበና ማሞ፣ ገጽ 15)፡፡ 
**************************************


ጳግሜ 5 ቀን 1952 ዓ.ም. ለአበበ ቢቂላ የአዲስ አመት ዋዜማ ብቻ አልነበረም፡፡ የአዲስ ድል፣ የአዲስ ክብረ-ወሰንና የአዲስ ታሪክ ሠሪነትም ጅማሮ ዕለት ነበር፡፡ በባዶ እግሩ 42 ኪ/ሜትር ከ195 ሜትሩን ሮጦ የኦሎመፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ተቀዳጀ፡፡ ከአበበ ቢቂላም በፊት ሆነ በኋላ በባዶ እግሩ ሮጦ በዘመናዊ ኦሎምፒክ ያሸነፈ የለም፡፡ ኧረ! የደፈረም የለ፡፡ 


አበበ ቢቂላ፣ አዲስ አበባ በድል አድራጊነት ሲመለስ ስለተደረገለት አቀባበልና ከጋዜጠኞች ጋር ያደረገውን ቃለ-ምልልስ ሙሉ ቃል አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲህ ነበር የዘገበው፡፡


አንዲት የሰማኒያ አመት አዛውንት መጥተው የአበበ ቢቂላን እጅና ጉንጭ እየሳሙ፣ “እድሜህን ያርዝመው፡፡ የእናትህ ልጅ፣ የሚስትህ ባል፣ የልጅህ አባት ያድርግህ፡፡” እያሉ መረቁት፡፡ ልብ ከሚነካው ከዚህ ትዕይንት በኋላ ጋዜጠኞች ቀርበው፣ ለአበበ ቢቂላ ጥያቄዎችን አቀረቡለት፡፡ ጥያቄዎቹንና መልሶቹን እነሆኝ ብለናል፡፡
ጥያቄ፤ በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ድርጅት ውስጥ መቼ ተቀጠርክ?
አበበ፤ በሚያዝያ 14 ቀን 1945 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ድርጅት ገባሁ፡፡
ጥያቄ፤ የክብር ዘበኛ ባልደረባ ከመሆንህ በፊት ስራህ ምን ነበረ?
አበበ፤ በጅሩ ወረዳ ልዩ ስሙ ሙጢ ከተባለ ወረዳ በግብርና ሙያ ላይ ነበርኩኝ፡፡  
ጥያቄ፤ የዛሬ አራት አመት የማራቶን ውድድር ተካፋይ መሆን ትፈልጋለህን?
አበበ፤ አዎን እርምጃዬን በዚሁ ዓይነት በመቀጠል ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ለምኮራባት እናት ሃገሬ    ለኢትዮጵያ ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማስገኘት አጣጣራለሁ፡፡
ጥያቄ፤ ይህንን የመሳሰሉት ድል አድራጊነቶች ከኢትዮጵያችን እጅ እንዳይወጡ የክብር ዘበኛ መስሪያ ቤትና የንጉሠ ነገሥቱ መንግስት ምን ቢያደርግ ይሻል ይመስልሃል?
አበበ፤ ምንም እንኳን ይህ ውድድር ጥንካሬንና ጉልበትን የሚጠይቅ ቢሆንም፣ እኔም ራሴ ወደዚህ ውድድር መግባት የሚፈልጉትን ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቼን ሮም ባገኘሁት ልምምድ መሰረት ለማስተማርና ይህ ድል ከኢትዮጵያዊያን እጅ እንዳይወሰድ ለማድረግ እጥራለሁ፡፡
ጥያቄ፤ ለመሆኑ ሩጫውን ድል ለማድረግ ምኞት ነበረህን?
አበበ፤ የአንደኝነት እንኳን ቢቀር የሁለተኝነትንና የሦስተኝነትን አሸናፊነት ለመውሰድ እሮጥ ነበር፡፡ በዚሁ ጊዜ አርባውን ኪሎ ሜትር ለመሮጤ ምልክት አሳዩኝ፡፡ ከፊቴም ቀጥ ያለ ፈታኝ አቀበት ነበረ፡፡ በዚህ ግዜ ነበር የሁለተኝነት ምኞቴ የተለወጠው፡፡ ተፎካካሪዬ የነበረውን ሩዋጭ አስቀድሜም ቀድሜው ነበርና አንደኝነቴን ለማረጋገጥ፣ ከበፊት የበለጠ በኃይል እሮጥ ጀመርኩ፡፡ ተፎካካሪዬን የሞሮኮውን ተወላጅ ራዲን በአንድ መቶ አንድ ያርድ (92.3544 ሜትር) ያህል ቀደምኩት፡፡
ጥያቄ፤ በውድድሩ አሸናፊነት ካገኘህ በኋላ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦልሃልን?
አበበ፤ አዎን፣ ቀርቦልኝ መልሻለሁ፡፡
ጥያቄ፤ የአዲስ አበባ ነዋሪ-ህዝብ ታላቅ አቀባበል አድርጎልሃል፡፡ ሮም ሳለህ ይኼን ያህል አቀባበል ይደረግልኝ ይሆናል ብለህ ገምተህ ነበርን?
አበበ፤ ይህን ያህል ደምቆና ተሟሙቆ ይቆየኛል ብዬ አልገመትኩም እንጂ መጠነኛ አቀባበል እንደሚደረግልኝ ተስፋ ነበረኝ፡፡
ጥያቄ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ፊት ቀርበሃል፡፡ በዚህም ተግባርህ እንድትበረታታ ማበረታቻ መሪ ቃል ተሰጠቶሃል፡፡ ለወደፊቱስ በዚህ በሮማ ብቻ ነው ወይስ በሌሎቹም የስፖርት ተግባሮች ትቀጥላለህ?
አበበ፤ እስፖርት የተባለውን ሁሉ በበለጠ ለመስራት በጣም አጣጣራለሁ፡፡ በዚህና በሌሎቹም የእስፖርት ተግባሮች እቀጥላለሁ፡፡
ጥያቄ፤ ስለተደረገልህ አቀባበል ምን ይሰማሃል፡፡
አበበ፤ የተገኘው ድል የሁሉም ነው፡፡ የመላው ኢትዮጵያውያን ፀሎትና እድል ተከትሎኝ የተፈለገውን ድል አገኘሁ፡፡ ደስታውም የሁላችንም ነው፡፡ ያላሰብኩትና ያልገመትኩት ደስታ በላዬ ላይ አርፏል፡፡
ጥያቄ፤ እግዜር ይስጥልን፡፡ ጥያቄያችንን ፈፀምን፡፡
አበበ፤ እኔም፣ እግዜር ይስጥልኝ፡፡ (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ መስከረም 6 ቀን 1953 ዓ.ም. ገፅ 3)


በዕለቱ የነበረውን የቤተ መንግሥት ስነ-ሥርዓት ፖል ራምባሊ እንዲህ ሲል ተርኮታል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ገነተ ልዑል ቤተ-መንግስት መግቢያ በረንዳ ላይ ዙፋናቸው ከፍ ብሎ ጠቀምጠዋል፡፡ የገረረችው ፀሐይ ወጥታለች፡፡ ራሶችና የክብር እንግዶች ፀሐይ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ዝግጅቱ እንደተጀመረም ንጉሡ በቅድሚያ ወደሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን ተጠግተው “ሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን የክብር ዘበኛ የስፖርት ኃላፊና የትምህርትና ስነ-ጥበብ ሚኒስቴር የስፖርት ዳይሬክተር በመሆን ወጣቶች አካላዊ ጥንካሬ እንዲላበሱ ላደረከው ከፍተኛ አገልግሎትና ላበረከትከው ቅን አገልግሎት ይህን ሜዳሊያ ስንሸልምህ ክብር ይሰማናል፡፡” ከዚያም፣ የኒሻን ሽልማቱን አጠለቁለት፡፡ 


ወደአበበም ቀረብ ብለው፣ “ወታደር አበበ ቢቂላ ለተቀዳጀኸው ታላቅ ድልና ለአገራችንና ለመላው አፍሪካም ላጎናፀፍከው ክብርና ተጋድሎህ ይህን አበርክተንልሃል፡፡” ንጉሡ ሜዳሊያውን ከሳህኑ ላይ አንስተው አበበ አንገት ላይ ካጠለቁ በኋላ ሁለቴ ወደ ኋላቸው ተራመዱና ወታደራዊ ሰላምታ ሰጡት፡፡....ስነ-ሥርዓቱም የተጠናቀቀ መሰለ፡፡ ንጉሡ ግን ከሄዱበት ሃሳብ ድንገት መለስ ብለው የኦሎምፒኩን ጀግና ትኩር ብለው አዩት፡፡ ከዚያም ከደማቅ ሰማያዊ እጀ-ጠባባቸው ኪስ አንድ የሥጦታ መያዣ አውጥተው በድጋሚ ተጠጉት፡፡ “የአስር አለቃ አበበ አገርህንና መላውን አፍሪካ አኩርተሃል፡፡.....በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ይህን ስጦታ ከንጉሠ ነገሥቱ ግምጃ ቤት አበርክተንልሃል፡፡” ካሉት በኋላ በድጋሚ ወታደራዊ ሰላምታ ሰጡት፡፡ አበበም እጆቹ እየተንቀጠቀጡ አጸፋውን መለሰ፡፡.....ንጉሡ የሰጡትን የስጦታ መያዣ እንደከፈተውም አንድ ትልቅ ባለአልማዝ ፈርጥ የወርቅ ቀለበት በማየቱ ደነገጠ፡፡” (ሮማን የወረረ ጀግና፣ ገፅ 153-4)፡፡


ይህን የአልማዝ ፈርጥ ያለው የወርቅ ቀለበት ከፍቶ ሲመለከት የተሰማውን ድንጋጤ መቼም አይረሳው፡፡ አልማዝ በእጁ ሲይዝ ለመጀመሪያ ጊዜው ነበር፡፡ የግርማዊነታቸው ስጦታም በመሆኑ እጅግ አስገርሞታል፡፡ ቀለበቱ ላይም “Rome 1960” የሚል ጽሑፍና የግርማዊ ንጉሠ ነገሥቱ ፊርማ ነበረው፡፡ በ1953ቱ የታኅሣሥ ግርግር ወቅትም አበበ ቢቂላ “ከነብርጋዴር ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ ጋር በዓመጹ ተሳትፈሃል” ተብሎ ዘብጥያ በወረደበት ጊዜ ሸሽጎ አስቀምጦት ነበር፡፡
በአበበ እስርና እንግልት ምክንያት ዓለም ዓቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የአሜሪካን የወቅቱ ፕሬዚዴንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ፣ የእንግሊዟ ንግስሥት ኤልሳቤጥ፣ የፈረንሳዩ ፕ/ት ዶጎል፣ የዩጎዝላቪያው ፕ/ት ቲቶ፣ እንዲሁም ታላላቅ ሰዎች ጭምር ከፍተኛ ጉትጎታ አድርገው ነበር፡፡ ንጉሡ አበበን እንዲምሩትና በማራቶን ድሎቹ ገፍቶበት በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ሊያዩት የሚፈልጉ ሁሉ ተማጽኖአቸውን ለንጉሡ አቀረቡ፡፡ በጦር ፍርድ ቤቱ ከአበበ ጋር በእስር እንዲማቅቁ ተፈርዶባቸው የነበሩት 89 ባልደረቦቹ ምህረት ተደረገላቸው (አዲስ ዘመን፣ ሚያዝያ 4 ቀን 1953፣ ገጽ 1)፡፡ 


የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የነበረውን የምረት ስነ-ሥርዓት እንዲህ ሲል ዘግቦታል፡፡ “የክብር ዘበኛ የበላይና ዝቅተኛ መኮንኖች መካከል፣ ጥፋተኛ ያለመሆናቸው እየተመረመረና እየተጣራ ከጥፋት ውጭ ሆነው የተገኙ ሰማንያ ዘጠኝ የሆኑ የክብር ዘቡ ባልደረቦች “ታላቅ ንጉሠ ነገሥታዊ ምህረት ተደረገላቸው፡፡” በክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ ብ/ር ጄኔራል ደበበ ኃይለ ማርያም አቅራቢነት - ገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥትም ቀርበው ስለተደረገላቸው ምህረት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትን እጅ ነሥተዋል” (አዲስ ዘመን፣ ሚያዝያ 4 ቀን 1953፣ ገጽ 1)፡፡ 


ምሕረት ሲደረግላቸው አበበ በጣም ከስቶና ውስጥ እግሩም በድብደባ የተነሳ ተተልትሎ፣ ቆስሎም ነበር (ሮማን የወረረ ጀግና፣ ገፅ 176-8)፡፡  ሊጠይቀው የሄደው ሻለቃ ኒስካኔን የአበበን ውስጥ እግሮች አያቸው፡፡ በድብደባው ሰበብ ፈነዳድተዋል፡፡ ትከሻውንም ይዞ ጨመቅ አደረገው፡፡ አበበ አጥንቱ ወትቷል፤ ጡንቻዎቹ ተልፈስፍሰዋል፡፡ አሰልጣኙም “ግን ለምን? ለምን እንደዚህ አደረጉ?!” ሲል ተንገበገበ፡፡ አበበም መለሰ፣ “ብዙ ጊዜ በኛ ሰዎች ላይ ሰይጣናዊ ቅናት አለ፡፡ የራሳችንን አጥብቀን መያዝ እንተውና የሰውን በቅናት ስንከተል የያዝነውና ያሰብነው ይላላል፤” (የማራቶን ጀግኖች አበበና ማሞ፣ ገጽ 84) ስለዚህም አበበ የምቀኝነትን ምንነት በወል ተረድቶታል፡፡ ኒስካኔንም፣  “ወደቀድሞ አቋምህ እናመጣሃለን፡፡ በቂ ልምምድም ትጀምራለህ” አለው፡፡.......አበበ የአልማዝ ፈርጥ ያለውን ቀለበቱን ከደበቀበት አውጥቶ ሳም ካደረገ በኋላ ጣቱ ላይ አጠለቀው፡፡ የድል አድራጊነቱ ልዩ ማሳታወሻ ነው፡፡ መብረቅ የሆነውን የምቀኞች ተንኮል የሚከላከልለት ያህል ነበር የተሠማው፡፡ (ስለዚህ ተዓምረኛ ቀለበትና ስለአበበ ቢቂላ የቶኪዮና የሜክሲኮ ኦሎምፒክ ድሎችና ተሳትፎዎች ሳምንት በክፍል ሁለት እንመለስበታልን፡፡ ቸር እንሰንብት!)       

(ይህ መጥፍ በአዲስ ጉዳይ መፅሔት ሐምሌ 22 ቀን 2004 ዓ.ም ቁጥር 124 ዕትም ላይ ወጥቶ ነበር፡፡)

አስተያየቶች

አስተያየት ይለጥፉ

Thanks a lot for your comments.