ሻምበል አበበ ቢቂላ፤
የኢትዮጵያ አልማዝ፣ የአፍሪቃ እንቁ! (ክፍል 2)

በሰሎሞን ተሠማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)

“በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ዋናው ጉዳይ ተሳትፎ ነው፡፡ አሸናፊነት ከትጋት፣ ከልምድና ከወኔ የሚመጣ ነው፡፡” ይህንን ቃል በተደጋጋሚ የሚናገረው ስዊድናዊው የአበበ ቢቂላ አሰልጣኝ ሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን ነበር፡፡
ከቶኪዮ የኦሎምፒክ መንደር ሮይተርስ ጥቅምት 11 ቀን 1957 እንደዘገበው ከሆነ፣ የማራቶን ሩጫ ለመወዳደር ልብስ መለዋወጫ ክፍል ውስጥ ባለአልማዝ ፈርጥ የወርቅ ቀለበቱን እንዳጣ ተናግሯል፡፡ ሮይተርስ፣ አበበ ቢቂላ የጣት ቀለበቱን ያገኘው በ1953 ዓ.ም በሮም ኦሎምፒክ የማራቶን ሩጫ ድል አድርጎ እንደተመለሰ፣ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የሰጡት እንደነበረ አትቷል፡፡ በቀለበቱ ላይም “Rome 1960” የሚል ጽሑፍና የንጉሡ ፊርማም ይገኝበት እንደነበር ወሬው አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም፣ በቀለበቱ መጥፋት የተነሳ አበበ በጣም ያዘነ መሆኑን ሮይተርስ ገልጧል (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ጥቅምት 14 ቀን 1957 ዓ.ም፣ ገጽ 1)፡፡
ስለዚሁ የአበበ ቢቂላ ቀለበት ጉዳይ በተመለከተ ኅዳር  18 ቀን 1957 ዓ.ም የወጣው “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ እንዲህ ሲል አትቶታል፡፡ “ይህንን የአልማዝ ፈርጥ ያለው የወርቅ ቀለበት፣ አንዲት ጃፓናዊት ሴትዮ ያገኘችው መሆኗንና ሴትዮዋም የቀለበቱን ዝና ባለማወቅ ለልጅ ልጀዋ ሰጥታት የነበረ ሲሆን፣ የልጅ ልጅቷ ግን ስለዚህ ቀለበት መጥፋት ጉዳይ በጋዜጣ ላይ አንብባ ስለነበር አያቷ የሰጠቻትን ይህንን ቀለበት ይዛ “ሜኒቺ ሺምቡን” ለተባለው ለዚሁ ጋዜጣ ጽሕፈት ቤት ወስዳ ያስረከበች” መሆኗ ተገልጧል (ገጽ 1)፡፡ አበበ በቀጣዩ ግንቦት ወር ለኢንተርናሽናል ውድድር ወደጃፓን  በሚሄድበት ወቅት ቀለበቱን እንደሚረከብ አዲስ ዘመን ዘግቧል፡፡
******************************          
አበበ ቢቂላ፣ መንፈሰ-ጠንካራና እልኸኛ ከመሆኑም በላይ፣ በብዙ አገሮችና የኦሎምፒክ ውድድሮች በመሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካም ያመጣ የሩጫ ባለሙያ ነው፡፡ የሩጫ ጀግና ነው - አበበ፡፡ አበበ ቢቂላ፣ የሚከተሉትን ድሎች በጀግንነትና በእልህ ያገኘ ሯጭ ነው፡፡ 
አንደኛ፤ በ1951 ዓ.ም. ክረምት ላይ በተደረገ የግርማዊ ጃንሆይ የጦር ሰራዊት የስፖርት ውድድር በዓል ላይ በማራቶን ተፎካክሮ አንደኛ ሆነ፡፡ ይህ ድል ለአበበ ቢቂላ ብቻ ሳይሆን ለአሰልጣኙ ለሻለቃ ኦኒ ስካኔንም ታላቅ ተስፋን የፈጠረ ነበር፡፡ አበበ ውድድሩን ያለጫማ 2፡16 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ ገደማ ነበር ያጠናቀቀው፡፡ ቀደምቶቹን ሯጮች እነዋሚ ቢራቱን፣ እነባሻዬንና እነማሞ ወልዴን ሳይቀር በረጅም ርቀት ነበር ጥሏቸው የገባው፡፡ ይህ ውድድር “ለአበበ ቢቂላ ድሎች ሁሉ” የመሰረት ድንጊያ ነው፡፡   
ሻምበል አበበ ቢቂላ ጳግሜ 5 ቀን በ1952 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በሮም ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ያገኘውን የማራቶን ድል በመቀጠል በርካታ የማራቶን፣ የግማሽ ማራቶንና የተለያዩ የረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ በመካፈል ጀግንነቱን አረጋግጧል፡፡ ሻምበል አበበ ቢቂላ ከሮም ኦሎምፒክ ቀጥሎ የሚከተሉትን ድሎች የተቀዳጀ ሲሆን ዓመተ-ምህረታቸውን መሰረት አድርገን እናቀርብላችኋለን፡፡
1ኛ. በ1953 ዓ.ም. አቴንስ ላዩ በተደረገው የማራቶን ውድድር 2፡21፡36 ሰዓት በመግባት አንደኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል፡፡ 
2ኛ. አሁንም በ1953 ዓ.ም. አቴንስ ላይ በተደረገ የማራቶን ውድድር በመካፈል 2፡23፡46.6 ሰዓት በመግባት አንደኛ ሆኖ ስለፈፀመ የተዘጋጀለትን ልዩ ሽልማት ተቀብሏል፡፡ 
3ኛ. በዚሁ በ1953 ዓ.ም. ለ4ኛ ጊዜ በተዘጋጀው የኮሎኝ ማራቶን ላይ ተወዳድሮ 2፡20፡12 ሰዓት በመግባት አንደኛ ሆኖ ሲፈፅም አከታትሎ በአንድ አመት ግዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ ከማሸነፉም በላይ “ማራቶን ርስቴ ነው” ያለ ነበር የሚመስለው (የማራቶን ጀግኖች፣ ገጽ 78)፡፡
4ኛ. በ1954 ዓ.ም. በርሊን ላይ በተደረገው የ10 ሺህ ሜትር አገር አቋራጭ ውድድር ላይ 20 ደቂቃ ከ004 ሴኮንድ በመግባት 2ኛ ሆኖ ስለፈጸመ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ 
5ኛ. በ1954 ዓ.ም ሜልሜ ከተማ ላይ በተደረገው የግማሽ ማራቶን ሩጫ ተካፍሎ ልክ 1፡00 ሰዓት በመግባት አንደኛ ሆኗል፡፡
6ኛ. በዚያው በ1954 ዓ.ም ለአምስተኛ ጊዜ ስውድን ላይ በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ተካፍሎ 1፡00፡26 በፈጀ ሰዓት በመግባት አንደኛ ሆኖ የአሸናፊነቱን ዋንጫ ተረክቧል፡፡ 
7ኛ. በዚያው በ1954 ዓ.ም ለ3ኛ ጊዜ በኩፐንሃገን ላበተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር 1፡09፡08 በመግባት አንደኛ ከመሆም በላይ የቦታውንም ክብረ-ወሰን ሰብሯል፡፡ 
8ኛ. በዚያው በ1954 ዓ.ም ለ6ኛ ጊዜ በዴንማርክ በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር 1፡08፡02 ሰዓት በመግባት አንደኛ ሆኗል፡፡
9ኛ. በ1954 ዓ.ም ለ7ኛ ጊዜ ቼኮዝሎቫኪያ ላይ በተደረገ የማራቶን ውድድር 2፡23፡4 ሰዓት በመግባት አንደኛ ሲሆን፤ በስድስት ኪሎ ሜትር ሩጫም ተወዳድሮ ስድስተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
10ኛ. በ1954 ዓ.ም. ኦሳካ ላይ በተደረገ ማራቶን ተወዳድሮ 2፡29፡27 ሰዓት በመግባት በአንደኛ ከመሆኑም በላይ አከታትሎ በሦስት የግማሽ ማራቶን እና በሁለት የማራቶን ውድድሮች ላይ በመካፈል ያሸነፈ አንድም አትሌት አልተገኘም፡፡
11ኛ. በዚሁ በ1954 ዓ.ም. ብራዚል ላይ በተደረገ የሰባት ሺ አራት መቶ ሜትር ውድድር ላይ ተካፍሎ 21፡29 ደቂቃ በመግባት በ2ኛነት አሸናፊነቱን አስመስክሯል፡፡
12ኛ. በ1955 ዓ.ም. ጃፓን ላይ በተደረገው የማራቶን ውድድር 2፡19፡06 ሰዓት በመግባት አንደኛ ሆኖ ፈጽሟል፡፡
13ኛ. በዚሁ በ1955 ዓ.ም በስዊድ ስቶኮልም ከተማ በተደረገ የወዳጅነት የማራቶን ውድድር ላይ  አንደኛ ሆኖ አሸንፏል (የፈጀበትን ሰዓት አላገኘነውም)፡፡
14ኛ፤ በ1955 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ ቦስቶን ላይ በተደረገ የማራቶን ውድድር ተካፍሎ ሲመራ ቆይቶ በደረሰበት የጡንቻ መሸማቀቅ የተነሳ 2፡24፡23 ሰዓት በመግባት አምስተኛ ሆኖ ውድድሩን ፈጽሟል፡፡
15ኛ. ከሦስት ቀናት በኋላ በዚያው ቦስተን ላይ በተደረገ የግማሽ ማራቶን ውድድር 1 ሰዓት ከ22 ደቂቃ በመግባት ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
16ኛ. በ1955 ዓ.ም ስፔን ላይ በተደረገ የአስራ ሁለት ሺህ ሜትር ሩጫ ላይ ተወዳድሮ 36 ደቂቃ ከ02 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡
17ኛ. በ1956 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ ሳስቶፓስቲያን ላይ በተደረገ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ላይ ሰባተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽሟል (የፈጀበትን ሰዓት አላገኘነውም)፡፡  
  
18ኛ. በ1957 ዓ.ም. በቶኪዮ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች የማራቶን ውድድር ላይ 2፡12፡11.2 በመግባት  የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያውን ለሁለተኛ ጊዜ አጥልቋል፡፡ (ይህን ውድድር ለየት የሚያደርጉት ሁለት ዘገባዎች አሉ፡፡ አንደኛው፣ ለቶኪዮ የኦሎምፒክ ማራቶን ውድድር ሠላሳ ስድስት ቀን ሲቀረው አበበ የትርፍ አንጀት ለማስወጣት የቀዶ ጥገና አካሂዶ ነበር፡፡ ሆስፒታል በገባ በሳምንቱ ልምምድ ጀመረ፡፡ ሁለተኛ፣ አበበ ጃፓን ሄዶ ንጉሠ ነገሥቱ የሮም ኦሎምፒክን አሸንፎ በተመለሰበት ወቅት የሸለሙትን ቀለበት ከመለባበሻ ክፍሉ ውስጥ ጠፋበት (ተሰረቀ)፡፡ በዚህም ከፍ ያለ ጫና ነበረበት፡፡ የሆነው ሆኖ አበበ እንደገና ቶኪዮ ላይ በኦሎምፒክ መድረክ በማራቶን የድል አክሊል ተቀዳጅቶ እንደስሙ “አበበ”፡፡) 
19ኛ፤ እንደገና በ1957 ዓ.ም በዚያው በጃፓን፣ ማንቺኒ ከተማ በተደረገለት የወዳጅነት ጥሪ መሰረት ተወዳድሮ 2፡29፡27 ሰዓት በመግባት የአንደኝነትን የድል አክሊል ደገመ፡፡
20ኛ. በ1958 ዓ.ም በስፔን ዛሮዚ ከተማ በተደረገ የማራቶን ውድድር ላይ 2፡20፡28 ሰዓት በመግባት ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቋል፡፡ 
21ኛ. በ1959 ዓ.ም በደቡብ ኪሪያ ዋና ከተማ ሴውል ማራቶን ላይ ተወዳድሮ 2፡22፡06 ሰዓት በመግባት የወርቅ ሜደሊያውን አጥልቋል፡፡
22ኛ. በ1961 ዓ.ም ሜክሲኮ ላይ በተደረገው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ ተካፍሎ እስከ አስራ አምስተኛው ኪሎ ሜትር ሲመራ ቆይቶ እግሩ ላይ በደረሰበት የሥር መዞር (መታወክ) የተነሳ አቋርጧል፡፡  (ምንጮች- አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ሐምሌ 24 ቀን 1958 ዓ.ም፣ ገጽ 6 እና የማራቶን ጀግኖች አበበና ማሞ፣ ገጽ 78-97፡፡)
ሻምበል አበበ ቢቂላ ለማራቶንና ለግማሽ ማራቶን የተፈጠረ ሯጭ ነው፡፡ አበበ ቢቂላን ከሌሎች የኢትዮጵያ አትሌቶች ሁሉ ለየት የሚያደርጉት ድሎቹን አከታትሎና ደጋግሞ መፈጸሙ ነው፡፡ በሁለት የወዳጀነት ማራቶኖች አንደኛ ሆኖ ያሸነፈ ሲሆን፣ በአስራ አንድ የኢንተርናሽናል ማራቶን ውድድሮች ላይ አንደኛ ሆኖ ከማጠናቀቁም በላይ፣ ሁለት የኦሎምፒክ ክብረ-ወሰኖችንና ሦስት የቦታ ክብረ-ወሰኖችን ሰብሮ የነበረ ሯጭ ነው፡፡ በቦስተን የኢንተርናሽናል ማራቶን ውድድር ላይ ተካፍሎ አምስተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ በአምስት የኢንተርናሽናል ግማሽ ማራቶን ውድድሮች ላይ ተካፍሎ በሁሉም ላይ አንደኛ ሆኖ ፈጽሟል፡፡ ከሰባት ሺህ እስከ አስር ሺህ ሜትር ርቀት ድረስ ያሉትን ውድድሮች ላይ አንደኝነት አይቀናውም ነበር፡፡
 በነዚህ ድሎቹ ምክንያት Daily Times የተባለው የናይጄሪያው ጋዜጣ “የአፍሪካ ዕንቁ” ብሎታል (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ታኅሣሥ 24 ቀን 1957 ዓ.ም፣ ገጽ 1)፡፡ ቢቢሲ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ አበበ ቢቂላን “የዓመቱ ታላቅ ስፖርተኛ” ከማለቱም ሌላ “የኢትዮጵያ አልማዝ” ነው ሲል ሰይሞታል፡፡ ከብሪታንያ ሕዝብና ከንግስት ኤልሳቤጥ የተላከለትን በብር የተሰራ የቪዲዮ ካሜራ ከጃንሆይ እጅ ተቀብሏል (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ታኅሣሥ 22 ቀን 1957 ዓ.ም፣ ገጽ 1)፡፡  በተጨማሪም፣ አበበ ቢቂላ ለኮሎምበስ የስፖርት ሽልማት የተመረጠ ሲሆን፣ ይህ ሽልማት የክርስቶፈር ኮሎምበስን መርከብ ቅርጽ ያለው ከወርቅና ብር ማዕድናት የተሰራ ነው፡፡ ሽልማቱን የካቲት 22 ቀን 1959 ዓ.ም ተሸልሞ ከተመለሰ በኋላ ቤተ-መንግሥት ድረስ ተጠርቶ “ሽልማቱን ለግርማዊ ጃንሆይ  አሳይቷል” (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የካቲት 30 ቀን 1959 ዓ.ም፣ ገጽ 1)፡፡
*****************************
የሜክሲኮ ኦሎምፒክ ዋዜማ ሐምሌ 1960 ዓ.ም አበበ ወደምዕራብ ጀርመን ለሕክምና የሄደው፡፡ ለሁለት ወራት ያህል ከፍተኛ የሆነ የእግር ጉልበት ምርመራና ሕክምና ሲያደርግ ነበር የቆየው፡፡ መስከረም 15 ቀን 1961 ዓ.ም ኤፒ (Associate Press) ከሜክሲኮ ባስተላለፈው ዜና “አበበ ቢቂላ ለሦስተኛ ጊዜ ባለድል የመሆኑን ተስፋ ሰጠ፡፡ የረጅም ርቀት ሯጭ የመቶ አለቃ አበበ ቢቂላ ወደሜክሲኮ ከተማ ሃያ (20) ኪ.ሜትር  ያህል ሮጦ ከገባ በኋላ ያኔውኑ ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃል፣ ሦስተኛውን የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳይ በአሸናፊነት እረከባለሁ” ማለቱን ዘግቧል፡፡ በጥቅምት 16 ቀን 1961 ዓ.ም፣ ኤ.ኤፍ.ፒ (AFP) ከሜክሲኮ ከተማ ባስተላለፈው ዜና፣ “አበበ ቢቂላ ለድሉ ያሰጋል” ሲል ተስፋውን ገልጦ ነበር፡፡ ከአስር ቀናትም በኋላ ኤ.ኤፍ.ፒ (AFP) “አበበ ቢቂላ ከሯጮች ሁሉ የተወደደና የተከበረ ነው፤” ሲል አሞግሶታል፡፡ መስከረም 29 ቀን 1961 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ “ከኦሎምፒክ መንደር” በሚለው ርእስ ስር፣ “የሜክሲኮው ማራቶን ድል የአበበ ቢቂላ ነው” ሲል የኢንተርናሽናል ክብረ-ወሰኖች ማህበር ፕሬዝደንት ሮቤርቶ ኮርቼታኒን ጠቅሶ ጽፏል፡፡ 
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በበኩሉ ጥቅምት 2 ቀን 1961 ዓ.ም ዕትሙ “የሁለት ጊዜ የማራቶን አሸናፊ የመቶ አለቃ አበበ እናትና ባለቤት ውጤቱን ለመስማት ጓጉተዋል፤” ሲል ነበር ያተመው፡፡ በዘገባው ስር አበበ ቢቂላ የእግር ሕመም ስሜት አለበት በመባሉ ብዙ ሰዎች መደናገጣቸውንም ጽፏል፡፡ ልብ የሚነካው ግን ጋዜጠኛው የ61 ዓመት እመቤት ከሆኑት እናቱ ወ/ሮ ውድነሽ በነበሩ ጋር ያደረገው ቃለ-ምልልስ ነው፡፡ የአበበ እናት፣ “ታምሞ ወደጀርመን አገር ሲሄድ ሕመሙ ለከፋ አደጋ ይዳርገዋል ብዬ እጅግ ሰግቼ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ታመመ ሲሉ ክፉኛ ደንግጫለሁ፡፡ ግን መቼም ቀን ከሌት በቀኝ እንዲያውለው ለኢትዮጵያ አምላክ ጸሎት እንዳደረስኩ ነው፤” በማለት የእናትነት ጥልቅ ስሜታቸውን ይፋ አድርገውታል፡፡ 
ወ/ሮ ውድነሽ እንደገጡት በአሁኑ ጊዜ ልጃቸው በዓይናቸው ላይ የሚሄደው በሁለት መልክ ነው፡፡ “አንደኛ በሔደበት ከፍተኛ ዓላማ ቅኝ ቢያውለው ብዬ ነው፡፡ ዳግመኛም ሕመሙ ለክፉ ይሰጠዋል በሚል የእናትነት አሳቢነት ነው፤” ብለዋል፡፡ በማስከተልም፣ ስለአበበ አብሮ አደግ ጠባይ አረጋዊቱ እመቤት እንደገለጡት፣ “አዋቂን ማክበር፣ በማንኛውም ነገር ጣልቃ አለመግባትንና የመንፈስ አለመረበሽ እንዲያው ከጥንት ከጠዋት የነበረው ቀና ባሕርይ ነው፤” ሲሉ አረጋግጠዋል (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ጥቅምት 2 ቀን 1961 ዓ.ም፣ ገጽ 8)፡፡ 
ጥቅምት 7 ቀን 1961 ዓ.ም የታተመው “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ እንዳተተው ከሆነ፣ “ማክሰኞ ዕለት (ማለትም ጥቅምት 5 ቀን 1961 ዓ.ም) የሃያ ኪሎ ሜትር ሩጫውን አጠናቆ መግባቱንና ጤንነቱም መልካም ሁኔታ ላይ መገኘቱን አበበ ቢቂላ ገልጧል” ሲል አስነብቧል፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ጥቅምት 11 ቀን 1961 ዓ.ም ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ውድድር በማራቶን ለሦስተኛ ጊዜ በመጋቢ ሃምሳ አለቃ (ያን ጊዜ) ማሞ ወልዴ አማካኝነት የወርቅ ሜዳሊያዋን ተቀዳጀች፡፡ ሮይተርስ፣ ማሞ ወልዴን “ብረት የሆነው ኢትዮጵያዊው ሰው” ሲል ነበር ያሞካሸው፡፡ የማሞ ወልዴ የ16 ዓመታት ባለቤት ወ/ሮ ዓይናለም ብሩ በበኩላቸው “ወንድ ብሆን ኖሮ ጥይት እተኩስ ነበር!” ሲሉ ደስታቸውን ገልጠዋል፡፡ .......
ከሜክሲኮ ኦሎምፒክ መልስ አበበ ቢቂላ አንድም የዓለም አቀፍ ውድድር አላደረገም ነበር፡፡ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ ሐረርና ዓለማያ (ኻሮማያ) ከተማዎች ለወራት ያህል በግብዣና በሽርሽር ነበር ያሳለፈው፡፡ በጥር ወር 1961 ዓ.ም ላይም አሰልጣኝ ለመሆን ወሰነ፡፡ ለሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን ስለአሳቡ ገለጠለት፡፡ ሻለቃ ኒስካኔን እንደዚያን እለትም ተደስቶ እንደማያውቅ የፖል ራምባኒ መጽሐፍ ይገልጻል፡፡ 
ማሰልጠን በጀመረ በሁለተኛ ወሩ፣ መጋቢት 14 ቀን 1961 ዓ.ም ቀትር ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስት ኪሎ ካምፓስ የአሁኖቹ የተማሪዎች መኖረያ ሕንታች የተሠሩበት ቦታ ላይ መሠረት ለመጣል ጉድጓድ ተቆፍሮ ነበር፡፡ ሦስት የፖሊስ ባልደረቦችን ተኩስና ዱላ የመሸሹ ተማሪዎች እየሮጡ የአበበን ቮልስ ላይ ሊወጡባት ተጠጓት፡፡ አበበ በፍጥነት መሪውን ጠመዘዘ፡፡ ሆኖም በስተቀኙ በከል የነበረውን ለግንባታ የተቆፈረ ጉድጓድ አላስተዋለውም ነበር፡፡ ነገሮች በፍጥነት ተከሰቱ፡፡ አበበና ንጉሴ ሮባ መኪናዋ ውስጥ እንዳሉ ብዙ ደም ፈሰሳቸው፡፡ የአበበ አከርሪ አጥንት (Spinal Cord) ተቀጨ፡፡ 
በንጉሠ ነገስቱ ጥብቅ ትዕዛዝ ዜናው ለሚዲያ ፍጆታ እንዳይውል ታሰረ፡፡ በመሆኑም፣ አደጋው ከደረሰበት ከሰባት ቀናት በኋላ መጋቢት 21 ቀን 1961 ዓ.ም የወጣው የ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣ “አበበ ቢቂላ ለሕክምና ወደ ሎንደን ሔደ” ካለ በኋላ፣ በክብር ዘበኛ ሆስፒታል ውስጥ ተኝቶ ያሳየናል፡፡ አበበ አይኖቹን የጨፈነ ሲሆን ግንባሩ ላይ ፕላስተር ተለጥፎበት ይተያል፡፡ ሎንዶን በሚገኘው የስቶክማን ዴቪል ሆስፒታል ሕክምናውን ለመከታተል በግርማዊነታቸው ትዕዛዝ እንደሔደ ያትታል፡፡

ከዚህ አደጋ በኋላ፣ ሻምበል አበበ ቢቂላ ዳግም በእግሮቹ አልሮጠም፡፡ ኧረ መሮጥ ቀርቶ አልተራመደባቸውም፡፡ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆኖ የሙኒክ አሎምፒክን በክብር እንግድነት ተካፍሏል፡፡ በአንድ የአካል ጉዳተኞች ኦሎምፒክ ውድድር ላይም ተሳትፎ የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችና አግኝቷል፡፡.......አደጋው በደረሰበት በአምስት ዓመት ከሰባት ወሩ፣ በክብር ዘበኛ ሆስፒታል ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም ልክ ከጠዋቱ 2፡45 ሰዓት ላይ ዐረፈ፡፡ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ-ክርስቲያን ንጉሠ ነገስቱ በተገኙበት በታላቅ ክብር ግብዓተ መሬቱ ተፈፀመ፡፡ 
እናቱ ወ/ሮ ውድነሽ በነበሩ እንዲህ ሲሉ ነበር ሙሾ ያወረዱት፡፡
      “ወርቅህ ሲያብለጨልጭ፣ ከሳጥንህ ላይ፣
አበባዬ ልጄ መርገፍህ ነወይ?!
አይዞህ አትደንግጥ፣ ስለሆንክ ብቸኛ
እኔም እመጣለሁ፣ ጠጋ ብለህ ተኛ!”  (የማራቶን ጀግኖች...፣ ገጽ 109-110) ለአበበ ቢቂላና ለሌሎችም ባለታሪኮች ሁሉ፣ ነፍስ ይማርልን!......





        

አስተያየቶች