ገጣሚው ጀገነ!
ሰሎሞን ተሠማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)
በውቀቱ ሥዩም ገጣሚ ነው፡፡ የወግ ፀኃፊም ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ተከታታይ ታሪክ ቀመስ ክርክሮችን በፍትህ ጋዜጣ ላይ መጻፍ ጀምሯል፡፡ በአጫጭር ግጥሞቹና ስንኞቹ እንዲሁም በራሱ ድምጽ እያነበበ በሲዲ በሚያሰራጫቸው ወጎቹ በህዝብ ይታወቃል፡፡ “ነዋሪ አልባ ጎጆዎች”ና “ስብስብ ግጥሞች” የሚባሉትን የግጥም መድብሎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ “መግባትና መውጣት” የተሰኘው የወጎች ስብስብ የሆነው ሲዲ የመጨረሻው ይመስለኛል፡፡ ላለፉት ጥቂት አመታት በ”አዲስ አድማስ”፣ በ”አዲስ ነገር”ና በ”ፍትህ” ጋዜጦች ላይ አምደኛ ሆኖ ጽፏል፡፡ በቀድሞዋ “ሮዝ”ና በአሁኗ “አዲስ ጉዳይ” ላይም ካለፍ-አገደም መጣጥፎቹን ለአንባቢያን አበርክቷል፡፡

የተወሰኑት ግጥሞቹ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉመዋል፡፡ “In Search of Fat”, “So Playful”, “Peace”, “A Flower Growing On Rubbish Tip”, “Hunger in the Desert”, and “Asking Forgiveness” የተሰኙት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከሁለት አመት በፊት በአንድ የእንግሊዝኛ ግጥሞች ስብስብ ውስጥ መታተማቸው ይታወሳል፡፡
በጣይቱ ሆቴል የገጣሚ በውቀቱን ወደ ሎንደን ኦሎምፒክ መሄድ አስመልክቶ፣ “እግሮቻቸውን ብቻ ሳይሆኑ ብዕሮቻችንም ወደ ኦሎምፒክ ይሮጣሉ......” በሚል መሪ ቃል ነበር ዝግጅቱ የተሰናዳው፡፡ በሽኝት ዝግጅቱም ላይ ገጣሚዎች፣ ሰዓሊያን፣ የመድረክና የስክሪን ተዋንያን፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም የጥበብ አፍቃሪዎች ተገኝተው ነበር፡፡ ዝግጅቱ ላይ አቅራቢዎች እየተነሱ ግጥሞቻቸውንና ጽሁፎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ረ/ት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ፣ ገጣሚ ጌትነት እንየውና ምስራቅ ጀምበሩና ሌሎችም ግጥሞቻቸውን አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም፣ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ቆየት ያለ ገጠመኙን ለታዳሚው አቅርቧል፡፡ ድምፃዊት ሙኒት በጆርጋ ታጅባ ጣዕመ ዜማዎቿን ለዝግጅቱ ታዳሚዎች አቅርባለች፡፡
ተጋባዥ እንግዶች የፕሮግራሙን መጀመር ካበሰሩ በኋላ ከሁለት የግጥም አቅራቢዎች ቀጥሎ፣ በዝግጅቱ ላይ እንዲናገር የገጣሚ በውቀቱ ሥዩም ተራ ደረሰ፡፡ ባቀረበው አጭር የመግቢያ ንግግር ላይም፣ “የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ሰው፣ እኔን መንግስት ከኋላ ሆኖ የደገፈኝ ማስመሰላቸው አግባብ አይደለም፡፡ እኔን የረዳኝ አካል የለም፡፡ ፓስፖርት ለማውጣት መሞከሬም ቢሆን የዜግነት መብቴ ነው፡፡ ወደ ኢምግሬሽን ሄጄ ፓስፖርት ለማግኘት ሦስት ወራት ሊፈጅብኝ የነበረውን ጉዳይ፣ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዳገኝ የተባበረኝን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ላንመሰግን እወዳለሁ፡፡ መመስገንም ካለበትም ምስጋናው የሚገባው ለተባሉት ባለሥልጣን ሳይሆን ለደራሲያን ማህበር ነው!” ሲል ተናግሯል፡፡ ከዚያም ወጉን ማንበብ ጀመረ፡፡ አድማጮቹም በሳቅና በአድናቆት ጭብጨባ አጅበውት ነበር፡፡
ከደቂቃዎች በኋላም ተመልሶ መድረኩን የያዘው በውቀቱ አሁንም ሌላኛውን ተናጋሪ ጎነጥ በማድረግ ነበር የጀመረው፡፡ ተናጋሪው፣ “በውቀቱን በ1991 ዓ.ም. በባህር ዳር ሙሉዓለም አዳራሽ አንድ ስለ ጥቁር ደም የሚያወሳ ተውኔት ጽፎ በነበረበት ወቅት በጣም ተደንቄ ነበርና አድናቆቴን ለመግለፅ ያህል አዲስ ያለበስኩት ጃኬቴን ደብረማርቆስ ላይ ሸልሜው ነበር፤” አሉ፡፡ ዝግጅቱ “ኪነ ጥበብ ለሰላም” የተሰኘ የባህልና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ነበር፡፡ እኔም ከባህል ሚኒስቴር ለዳኝነት ሥራ ሄጄ ታድሜ ነበር በውቀቱን ያወቅኩት፤” ሲሊ ትውስታቸውን ለታዳሚው አካፈሉ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ መድረኩን የተረከበው በውቀቱም ንግግሩን እንዲህ ብሎ ጀመረ፤ “ተናጋሪው እንዳሉት ያኔ ጃኬት ሰጥተውኝ ነበር፡፡ ወዳጄ እንደሚያውቁት ሎንዶን የሚያንዘፈዝፍ ብርድ አለና ምናለ ታዲያ ዛሬስ የካፖርት እርጥባን ቢሸልሙኝ!” ሲል ታዳሚውን አስፈግጎታል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ዶ/ር ዳኛቸው የበውቀቱን ሦስት ግጥሞች መርጦ ከፍልስፍናና ከስነውበት አንፃር ለመተንተን ሞከረ፡፡ ቤኔዲቶ ክሮቼ ስለ ስነ-ውበት፣ በተለይም ስለ ስነ-ግጥም ያወሳውን በመጥቀስ ነበር የጀመረው፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው እንዲህ ሲል ወደ ዋናው ሃሳቡ ገባ፤“ፈላስፈው ስለ እውነት መዋቅርና ምንነት ለመግለጽ ይተጋል፡፡ ገጣሚው ግን ስለ ውበት መዋቅር ለመግለጽ ይጨነቃል፡፡ ለፈላስፋው የእውነትን ብያኔ መግለጽ ዋነኛ ተግባሩ ነው፡፡ ለገጣሚው ግን ዋነኛ ተግባሩ የታመቀ የውበት ስሜትን ሁለንተናዊ መልክና ቅርጽ መስጠት ነው፡፡ የገጣሚው ተግባር የሰውን አኗኗር መፈከር ነው፡፡ ”መፈከር” ስልም መተርጎም ማለቴ ነው፡፡ የሰውን አኗኗር አጢኖ እንዲሰማንና እንዲታየን አድርጎ ይገልጽልናል፡፡ ገጣሚው የሰውን ሕይወት ሐሣሢ ነው፡፡ ፈላጊ ነው፡፡ ገጣሚው ተንባይም ነው፡፡ በግሪክኛ ቋንቋ (Prophecy and Poesy) የተቀራረቡ ዓይነት ናቸው፡፡ ገጣሚው የአንባቢውን ስሜት ሊያቅፍ ይተጋል ወይም ይጣጣራል፡፡ በተጨማሪም ገጣሚው ጀግና ሳይሆን ስለ ጀግንነት የሚያትት ነው፡፡ የግድ አርበኛ መሆንም የለብም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደማየው ከሆነ ግን ገጣሚ በውቀቱ ወደመጀገኑ እየተጠጋ ነው። ለምን እንደሆነም በየራሳችሁ ግምት ድረሱበት። ገጣሚ ትልቅ ጓደኛም ላይሆን ይችላል፤ ግና ስለ ጓደኝነትና ስለ ወዳጅነት ይጠበባል፡፡”
ከላይ በዶ/ር ዳኛቸው የተጠቀሰው ሊቅ ስለ ገጣሚው ምንትነት ተጨማሪ ሃተታዎችም አሉት፡፡ “ገጣሚው ወይም ሰዓሊው ስለቅርፅ እውቀት ካጠረው ሁሉም ነገር አብሮ ያጥረዋል፡፡ ምክንያቱም ገጣሚው ወይም ሰዓሊው ራሱን አጉድሏልና ነው፡፡ የግጥምነት ይዘት ያላቸው የገጣሚው ገለፃዎች ነፍስ የሚኖራቸው፣ ቅርጽ ያላቸው ከሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ጥበባዊ ስራ እውነትን የፈለገውን ያህል ቢይዝ እንደ ኪናዊ ስራ ልንረዳው ያዳግተናል፡፡ በአንፃሩ፣ እንደ ምሁራዊ ሃቲት ሊወሰድ ይችላል፡፡ በዚህም አተያይ መሰረት የአንድ ኪነታዊ ስራ “ይዘት” ከኪናዊ ስራው “ሃሳብ” ጋር በእጅጉ እኩል ነው፡፡ ምክንየቱም ኪናዊ ስራ ይዘትን ብቻ መያዝ አይገባውምና ነው፡፡ አንድ ስሜትን ቆንጥጦ የሚይዝ ሃሳብም መያዝ ይገባዋል፡፡
“በተመሳሳይ ሁናቴም” ይላል ቤኔዲቶ ክሮቼ፣ “በግጥምና በዝርው ፅሁፍ መካከል ያለው ልዩነት ሊገለፅ የሚያዳግት ሁለትነት ነው፡፡ እርሱም ጥበብንና ሳይንስን ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ የነዚህ ሁለት የስነ-ፅሁፍ ዘውጎች ልዩነት ውጫዊ እንጂ ውስጣዊ አለመሆኑን በጥንታዊያኑ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ውስጥ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም - ምጣኔ፣ ምት፣ የቅርፅ ወይም የ“ቅጥ” አጠቃቀም ነፃነቱ የተገደበ መሆኑና አለመሆኑ ሁሉ የውስጣዊ ልዩነታቸው መገለጫ ነው፡፡ በዋናነት ግጥም ስሜት አዘል ቋንቋ ይጠቀማል፡፡ ስድ ንባብ (ዝርው) ግን አዕምሮአዊ ቋንቋ የታይበታል፡፡ ነገር ግን አዕምሮ በስሜታዊነት ከተሸበበ፣ ተጨባጭነትንና ነባራዊነትን ስለሚሻር፣ ዝርው ጽሁፍም ግጥማዊ መልክ ይይዛል፡፡” (Croce- Aesthetics as Science of Expression and General Linguistics, 2003:20 ይመልከቱ፡፡)
ዶ/ር ዳኛቸው ቀጠለ፡፡ “በዚህም አተያይ መሰረት የመረጥኳቸውን ሦስት የበውቀቱ ግጥሞች ለመተንተን እሞክራለሁ፡፡ መጀመሪያ የመረጥኩት ግጥም ስለ ምስኪኑ ጎልያድ የሚያትተውን ነው፡፡ እንደምታውቁት በመጽኃፍ ቅዱስና በአዋቂዎችም አንደበት ስንሰማው የኖርነው ስለ ጥሩር የለበሰው፣ በከፍተኛ ሁናቴ የጦር ትጥቅና ጀሌ ስላለው፣ ስለ ጉልበተኛውና ጨካኙ ጎሊያድ ነው፡፡ ተያይዞም፣ ስለ ሚስኪኑ ዳዊትና ስለ ወንጭፉ እንዲሁም ስለ ወረወረው ጠጠር ተደጋግሞ ሰምተናል፡፡ ሆኖም ግን ገጣሚው በውቀቱ ሥዩም መጣና ያላየነውን ምስኪኑን ጎሊያድ ሊያሳየን ሞከረ፡፡ እግዜር ከዳዊት ጋር ነበረና፣ ባለወንጭፉ ዳዊት በወረወረው ትንሽዬ ጠጠር ጎሊያድ ወደቀ፡፡ ማንም ላላዘነለት ለዚያ ጦረኛና የጦር መሪ ጎሊያድ ውዳሴውንና አድናቆቱን በተዋበ ቋንቋ ሊገልጽ ችሏል፡፡ በተለይም፣ በበጎ ጎኑ የማይወሳውን ጎሊያድ ገጣሚው በራሱ ቃላት ዳግም ልደት ሊሰጠው ጥሯል፡፡
በማስከተልም፣ በረሃ ላይ እግሮቿን አሸዋ ውስጥ የደበቀችው ግመል ትበላለች አታበላም እያሉ ስለሚከራከሩት የተራቡት ሰዎችና በውቀቱ እንዴት አድርጎ ቃላቱን የተለየና ማራኪ ትርጉም ለያስተፋቸው እንደሞከረ አቀርባለሁ፡፡ በዚህ ግጥም ውስጥ ሁለት አከራካሪ ቀኖናዎች አሉ፡፡ አነርሱም ከቅዱሱ መጽሀፍ የተወሰዱ ናቸው፡፡ “የሚያመሰኳ ከሆነ ብላው፤” የሚለው አስተምህሮትና፤ “ሸኮናው ድፍን የሆነውን ማንኛውንም እንሰሳ አትብላ” የሚለው ትዕዛዝ ነው፡፡ በዚያ አውላላ በረሃ ላይ እጅግ የተራቡት ሰዎች ትዕዛዙን ጠብቀው መመገብ አለባቸው፡፡ በዚያ ላይ ፊት ለፊታቸው ያለችው ግመል እያመሰኳች ነው፡፡ ሆኖም፣ አሸዋው ውስጥ የተደበቀውን ሸኮናዋን አይተው ሳያረጋግጡ ሊያርዋት አይችሉም፡፡ በመሆኑም፣ ሸኮናዋን ለማየት ፍተሻ ጀመሩ፡፡ የግመሏን እግርም አሸዋው እያሰመጠውና ለማየት እያዳገታቸው በጣም ደከሙ፡፡ ስለዚህም፣ ወደ በመጀመሪያው ሃሳባቸው ላይ ፀንተው የግመሏን እግር ባናየውም እኮ ማመንዠጓን አይተናልና፣ በቃ ትበላለች ሲሉ አረዷት፡፡
በመጨረሻም ልተንነው የምፈልገው ግጥም “የባየተዋር ገድል” የሚለውን ነው፡፡ ስለ ዝምታና የገደል ማሚቶ በተመለከተ ጉደኛ ምናባዊ አቅም ያለው ግጥም ነው፡፡ መቼም፣ መስታወት ፊት ብቻውን የቆመ ሰው የገዛ መልኩን ማየቱ የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ግጥም ትልቅ ምናባዊ ኃይል (imaginative power) እንዲኖረው ያደረገው ከዝምታው ውሰጥ የወጣው የገደል ማሚቶ ነው፡፡ ግጥሙ፣ ለካስ እንደዚህም ማሰብና ማሰላሰል ይቻላልና የሚያሰኝ ጉልበት አለው፡፡
አሁን ደግሞ በዝግጅቱ ላይ ስለታዘብኳችና ግር ስላሉኝ አንዳንድ ነገሮች ልጥቀስ፡፡ ከላይ እንደ ገለጽኩት የመሸኛ ግጅቱ መልካም ነበረ፡፡ አዘጋጆቹ በሙሉ፣ በተለይም የእሸት ቤተመፅሀፍ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ሁለት ነገሮች ግርታን ፈጥረውብኛል፡፡ የመጀመሪያው፣ አዳራሹ ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ የነበረው መፈክር ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል፤ “እግሮቸችን ብቻ ሳይሆኑ ብዕሮቻችንም ወደ ኦሎምፒክ ይሮጣሉ......” ይላል፡፡ ሁለት መልዕክቶችን የያዘ መፈክር ነው፡፡ “የአትሌቶቸችን እግሮች ብቻ ሳይሆኑ የፀሀፊዎቻችንም ብዕሮች ወደ ሎንዶን ይሄዳሉ፤” የሚል ነው - እማሬያዊ ትርጉሙ፡፡ ፍካሬያዊ ትርጉሙም፣ “እግሮቻችን ብቻ ሳይሆኑ ብዕሮቻችንም በኦሎምፒኩ ውድድር ላይ ወርቅ ያመጣሉና አትስጉ” የሚል ሳይሆን ይቀራል? (ምናልባትም፣ ሌላው የመፈክሩ መልዕክት፣ ለታዳሚው በሞላ፣ “በአትሌተክሱ ወርቅ ባናገኝም ምንም ማለት ላይሆን ይችላል፣ በብዕራችን ባገኘነው ወርቅ ተደሰቱ” የሚል እንደሆነ እገምታለሁ፡፡
እዚህ ላይ ያልገባኝ ነገር ምን መሰላችሁ፤ “ብዕሮቻችን” የምትለው ቃል ናት፡፡ እስከማውቀው ድረስ እንድ ብዕር ብቻ ነው የተመረጠው፡፡ እናም ከወዴት መጥቶ “ብዕሮቻችን” እንደተባለ አልገባኝም፡፡ ምናልባት “በዘር ሃረጉ ኢትዮጵያዊ፣ በዜግነቱም እንግሊዛዊ የሆነውን የለምን ሢሣይን ብዕር ጨምሮ ይሆን እንዴ?” ብያለሁ፡፡
ሁለተኛው ግር ያሰኘኝ ጉዳይ፣ ገጣሚ በውቀቱ ነጭ ጥልፍና ጥበብ ያለው ጥብቆና ሱሪ ለብሶ የተነሳው ፎቶግራፍ ላይ ታዳሚውን ፈርም መባሉ ነው፡፡ እስከማውቀው ድረስ ይህንን መሰሉ የፊርማ ማስታወሻ ፎቶ የሚዘጋጀው የሰርግ ዕለት ነው፡፡ ታዲያ ምነው የሽኝት ዝግጅት ነው በለው ጠርተው ሙሽራይቱ የሌለችበት ፎቶ ላይ ፈርሙ መባሉ? ምናለበት አንድ ቆመጥ የሚያክል ብዕር ገጣሚ በውቀቱን አስታቅፈው ሙሽራይቱ ይህቺ ናት ቢሉን ኖሮ!..... ያሰኛል፡፡
(ይህ መጣጥፍ በአዲስ ጉዳይ መፅሔት ሰኔ 23 ቀን 2004 ዓ.ም ዕትም ላይ ወጥቶ
ነበር፡፡)
ምላሽ ይስጡሰርዝGreat post and success for you..
Kontraktor Pameran
Jasa Pembuatan Booth Pameran
Kontraktor Booth Pameran
Jasa Pembuatan Booth
Jasa Dekorasi Booth Pameran
Great post and success for you..
ምላሽ ይስጡሰርዝKontraktor Pameran
Jasa Pembuatan Booth Pameran
Kontraktor Booth Pameran
Jasa Pembuatan Booth
Jasa Dekorasi Booth Pameran
Great post and success for you..
ምላሽ ይስጡሰርዝKontraktor Pameran
Kontraktor Booth Pameran
Kontraktor Booth Pameran
Jasa Pembuatan Booth