ዘመን በርቆ፣ ዘመን ሲተካ
(ያረጀ ጥበብ፣ያፈጀ መላ….)
በሰሎሞን ተሰማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)

ስለዚህም፣ በዚህም ማጣጥፍ ስር ሦስት ርስ-በራሳቸው የተሳሰሩ፣ ግና በተናጠልም ተበታትነው
የሚገኙ “አሮጌ መላዎችንና ያፈጁ ጥበቦችን” እያነሳን እንሟገታለን፡፡
በበላ ልበልሃ የሙግት አካሄድ ዘይቤ እንጂ፣ በእንካ ሰላምቲያ ወይም ባልታረመው የ“ዴ-በለንዴ” አማርኛ ስልት እንዳታነቡኝ አደራ-አደራ
እላችኋለሁ፡፡ (ይህም ሆኖ ካልተገኘ፣… ከእንካ ሰላምታና ከአታካራ ውጭ በሆኑ ዘይቤዎች (በየራሳችሁ የንባብ ስልት) እንድትሞግቱኝ
በአክብሮት እጠይቅዎታለሁ፡፡)
*******************************************
‘ዘመን በርቆ፣ ዘመን ሲተካ፣’ ‘ሰው’ የሚባል ‘ታሪክ ሰሪ’ ፍጡር
አለ፡፡ ታሪክን ብቻ ሳይሆን ጥበብና መላንም አዕምሮው ያውጠነጥናል፡፡ ይጠበባል፡፡ ይህ ፈጣሪ “አሳምሮ የፈጠረው” የዘመናችን
ፍጡር ታዲያ፣ እንኳን ከዘመናት በፊት ሳይፃፍ ከቀረው ታሪክ ቀርቶ፣ ከተፃፈውም ጥበብና መላ አልማር ብሎ በአዙሪታዊ አዳዲስ መሰል ክስተቶች ታስሮ፣ ተሰነካክሎና
እግር-ተወርችም ተጠፍንጐ ይባዝናል፡፡ ብርሃኑን ከአማልዕክቱ ዘንድ ሰርቆ የሚያመጣለት ፕሮሚሲየቭ አጥቶ፣ የሚሰቀልለት ክርስቶስ
አርጎ፣ የሚቃጠልለት ቡረኖ ማርስ ጠፍቶ፣ መርዝ የሚጋትለት ሶክራቲስ ተሰውሮ - ይኼው “ሰው/ሕዝብ” የገዢዎቹ መጫወቻ፣ የአፋኝ
መንግስታቱ ማላገጫ ሆኗል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ወደ ዘመረላት “ደብተራ ግዕዛን” ወይም የነፃነት ድንኳን የሚያስገባው
በር ሁሉ በክፉዎችና በንፉጎች ተቆልፎበት፣ ፕሌቶ ወደ ገለጣት “ዩቶቢያ” ለመድረስ እየወደቀ-እየተነሳ ይጓዛል፡፡ ወደፊት ተስፋውን
ሰንቆ ይጓዛል፡፡ ወደ ነፃነት ምድር! ወደ ነፃነት አየር! ወደ ነፃነት ጠፈር!
መላ(ጥበብ) አንድ፡-
በግማሽ ልብ የመሆን (የወላውሌነት) አባዜ፣
ሄሶይድ የተባለው ግሪካዊ ገጣሚ “ከንቱዎች፣ አንድ ሙሉ ነገር ከግማሽ ነገር በምን ያህል እንደሚበልጥ
አያወቁም!” ሲል ተሳልቋል፡፡ አባባሉን አሁንም ድረስ፣ ልክ አንደ ዘጠኝ ወር ሙሉ እርጉዝ ፈጦ እመለከተዋለሁ፡፡ በውስጡም ሊወለድ
የሚችል “ልጅና እንግዴ ልጅ” አምቋል፡፡ ዋነኛው ቁም ነገር፣ ቀሪው ግማሽ ነገር በጣም አስፈላጊ ፋይዳ፣ ጥቅምና አገልግሎት
ያለው መሆኑ ነው፡፡ በምሳሌ ሳስረዳዎት፤ አንድ ሰው የተመኘውን ነገር ተፍጨርጭሮ ግማሹን ያህል ሲያገኘ፣ ቀሪውን ለመሙላትም ሲውተረተር
ቢታይ ሰውዬው ከስንፍናና ከወላውሌነት የራቀ ቆራጥ (ከነቱ ያልሆነ ሰው) መሆኑን ያሳያል፡፡ (እስቲ በሌላ መነጽር አይተን እንተርጉመው፡፡)
ከንቱዎቹ ያገኙትን ግማሽ ነገር ተሸክሞ ለረጅም ሂዜ መቆየትም አለመቻላቸው
ደግሞ ይበልጡን ያስቆጫል፡፡ ለምሳሌ፣ አንዲት ሰነፍ ሴት እንስራዋን አዝላ ውሃ ልትቀዳ ወደ ወንዝ ወረደች፡፡ እንስራዋን አውርዳ
ውሃ መቅዳት እንደ ጀመረችም፣ “ግማሽ እንስራ ውሃ ብቻ ቀድቼ ብሄድ ሊበቃኝ ይችላል’እኮ፡፡” ስትል አሰበች፡፡ በተጨማሪም፣ ከፊቷ
ያለውን አቀበታማ ዳገት አስታወሰችና ሃሞቷ ፈሰሰ፡፡ ስለዚህም፣ “ግማሽ እንስራ ውሃ ብቻ ብቀዳ ይበቃኛል” ብላ ወሰነች፡፡
ከዚያስ? ከዚያማ - ሴትዬዋ ግማሽ እንስራውን ውሃ ተሸክማ ጉዞዋን
እንደጀመረች፣ ግማሽ እንስራው ውሃ በተንቦጫረቀ ቁጥር ወገቧ ሲናጥ፣ የውሃው ሞገድ እንስራው
ውስጥ በተላጋ ቁጥር፣ ትንፋሿ ሲያጥር አቀበቱን እንደምንም ብላ (አይወጡት የለምና) ወጣች፡፡ ወዲያው ግን፣ ሌላ ሃሳብ ገስግሶ
መጣባት፡፡ ለካስ፣ “የጠላው ድፍድፍ ውሃ መሞላት አለበት፡፡ ኧረ! ጉድ፡፡ ለካስ የልጄም ሽንት ጨርቅ መታጠብ አለበት! ለካስ ጥጆቹም
ገና ውኃ አልጠጡም! ለካስ……” አዬ ጉድ! ቀጠለች፡፡
ሴትዮይቱ፣ ቀድሞ ድፍድፉን መሙላት እንደነበረባት ብታውቀው ኖሮ፣ ዳገቱን ለመውጣት የሚያስችላትን
ወኔ አሰባስባ፣ ተሸክማ ልትወጣው የምትችለውን ያህል እንስራ ወይም ገንቦ ገምታ ከቤቷ ወጥታ ቢሆን ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ልፋትና ድንጋጤ
ባልተፈጠረ ነበር፡፡ በዚህ ምሳሌ አስታከን፣ አንዱን ‘ግዙፍ መፍትሄ’ የሚያሻውን የኤሌክትሪክና የኃይል አቅርቦት እጥረት (የችግር
ድፍድፍ) እንመልከተው፡፡ በብርሃን ውስጥ ሆነን ልናስበው፣ ልናቅደው የሚንችለውን ችግር ይሄው በጨለማ ውስጥ ሆነን እንታሽበታል፡፡
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ውድ ዋጋ እየከፈሉበት ነው፡፡ ሃገራችን ለውስጥ ፍጆታዋና ለአጎራባቾቿ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችላትን
እቅድ ነድፋ ያጠናቀቀችው በ1958/9 ዓ.ም ላይ ነበር፡፡ (በ1992 ዓ.ም. ባሕርዳር በሚገኘው ቤዛዊት ቤተ-መንግስት ውስጥ ባጋጣሚ
ለስራ ጉዳይ ገብቼ ነበር ጥናቶቹንና መራሄ-ግብሩን ያነበብኩት፡፡) በፖለቲከኞቹ ወላውሌነትና በሕዝባችንም የንቃተ-ሕሊና ቀርነት
የተነሳ ይሄው ኢትዮጵያ በኃይል እጥረት ሳቢያ ሳይመሽ ጨለመባት፡፡ ከዚህም ችግር በማያዳግም ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችል መላና ጥበብ ኢትዮጵያ እየተከተለች
እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ብድሩንና ፈንዱን አፈላልጎ ያመጣል በሚል ስሌት ፕሮጅቸቶቹ ሁሉ ለሳሊኒ መሰጠታቸው ደግሞ ችግሩን ይበልጥ
ያወሳስበዋል፡፡
ዛሬ-ዛሬ ሳሊኒ የተባለው ጣሊያናው ኮንትራክተር ከመለስ ዜናዊ፣ ከአዜብ መስፍን፣ ከካሱ ኢላላ፣
ከአለማየሁ ተገኑ፣ ከምህረት ደበበና ከስመኘው በቀለ እንዲሁም ከሌሎች ግብረ-አበሮቹ ጋር ሆኖ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎቹን ግንባታ
በሙሉ በሞኖፖል ተቆጣጥሮታል፡፡ (ቦታው አይደለም እንጂ፣ ጠቅላዮቹ - መለስ ዜናዊና ሚስቱ፣ ሚኒስትሮቹ (አሽከሮቹ) ካሱ ኢላላና
አለማየሁ ተገኑ፣ እንዲሁም የወየኔ ጭፍራ ካድሬዎች ምህረት ደበበና ስመኘው በቀለ ምን ያህል ከኩባንያው ጋር የጥቅምና የሙስና ትስስር
እንዳላቸው ውስጥ አዋቂዎቹ መጋለጥ በቻሉ ነበር፡፡)
የኮሬንቲው ችግር ከመፈጠሩ በፊት ወያኔ ንፁህ የማቀጃና የመገንቢያ አመታት ነበሩት፡፡ ግና፣
የአገዛዙን ጥርስና ጥፍር ለማጠንከር፣ የቀንደኛ አመራሮቹን ብቃት ለመገንባትና በሃብትና በነዋይም ጭምር ለማደለብ ሲል ሃገራዊ አጀንዳዎችን
በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ጎን ገፈተራቸው፡፡ ሃገሪቱ የምትፈልገውን ትቶ፣ ወያኔ የሚፈልገውን እንደሚፈልገው ከወነ፡፡ በርካታ የመዘናጋትና
የመወላወል ጣጣዎች-ፈንጠጣ ሆኑ፡፡
በዓለማችን ላይ የተመዘገቡት ታላላቅ ክስተቶች የተገኙት በመጠበብና በጭንቀታማ ምርምሮች ነው፡፡
የአርኪሜደስ የመንሳፈፍ ህግም ሆነ የፋራዳይ አንፖል በጭንቀትና በመጠበብ ውስጥ የተወለዱ ናቸው፡፡ በጠራራ ፀሐይም ሆነ በድቅድቅ
ጨለማ ውስጥ ተቀምጦ የመፍትሔውን ጥበብ፣ የመውጫውን መላ መዘየድን ይጠይቃሉ፡፡ ሳይሰንፉ - ሳይቦዝኑ መጣር - መውተርተርን ይጠይቃሉ፡፡
በዚህም-በዚያም ብሎ የችግሩን ምንጭ፣ የችግሩን ስፋትና የሚያስከትለውን ጉዳት መገንዘብ ግድ ይላል፡፡ ያን ጊዜ የመፍትሔው ቁልፍ
በአጋጣሚ፣ በድንገቴ፣ ወይም በትጋት ማግኘት ይቻላል፡፡
ወደ መነሻ ነጥባችን እንመለስ፡፡ በሃገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ “ግማሽ” የሚባል ስምምነትም ሆነ ጥቅም ማስከበር የለም፡፡
ሁለት አብነቶችን እጠቅሳለሁ፡፡ አፄ ሚኒሊክ፣ ያንን ሁሉ መስዋዕትነት ያስከፈለ ጦርነት መርተው፣ ከመረብ ምላሽ ወዲያ ማዶ ያለውን
ታሪካዊ ግዛታችንን በገሚስ አስረክበው ተመለሱ፡፡ ያ በቀላሉ ታይቶ የነበረው “የመረብ ምላሽ” መዘዝ፣ የሰላሳ ዓመታት የእርስ በርስ
ጦርነትና እልቂት ማስከተሉ ሳያንስ - እንደማይሆን ሆኖ ተጠናቀቀ፡፡ የዛሬ አስራ ምናምን ዓመትም፣ ገሚስ ባድመን በጦር ሃይል ማስመለስ
ቢቻልም ቅሉ፣ (በገሚስ) ለኢትዬጵያ ሉዓላዊነት ጠር የሆነው የአስመራው
ኃይል ባለበት ተወው፡፡ የሶማሌያውን የሼክ/የኮሮኔል አውየስን
ኢስላሚክ ኮርት (የሸሪያ ፍርድ ቤቶች ህብረት) ከሞቃዲሾ አስለቀቅኩ ተበሎ ተፎከረና፣ “ወጣቶች ነን” የሚሉትን “አልሻ-እባቦች”
ተዋቸው፡፡ ኧረ ለምን ተብሎ ተመሳሳይ የሆኑ ታሪካዊ ክስተቶች ተፈፀሙ? ለምንስ፣ ክብራቸውን በወታደራዊ
የበላይነት የተነጠቁት የአስመራና የሶማሊያ ሃይሎች ይሄን ያህል አስቸጋሪ ሆኑ? ለምንስ አለባብሶ ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ሆነ?
መልሱ ቀላል ነው፡፡ ወላውሌነት ነው፡፡ የወታደራዊው ክንድ ድል በዲፕሎማሲያዊ መላና በጥበብ ካልታጀበ - (ገሚስ ሉዓላዊነትን የማስከብሩ
አዙሪት) - ዞሮ ዞሮ ግማሽ እንስራ ውሃ ተሸክሞ ዳገት እንደመውጣት ያለ ነው፡፡
ሰሞኑን በኢትዮጵየና የኤርትራ ድንበር አካባቢ የጦርነትና የግጭት ወሬዎች ይናፈሳሉ፡፡ የዓለም
አቀፍ መገናኛ ብዙኃኑም በአካባቢው ዝር እንዳይሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው፡፡ ከዘመዶቻችንና ጓደኞቻችንም ጋር እንዳንገናኝ
የስልክ መስመሮች አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ ነገሩ ሦስተኛ ሳምንቱን ወደ መያዙ ላይ ነው፡፡…ለመሆኑ የኤርትራ ጉዳይ፣ ዘመን በርቆም
- ዘመን ሲተካ፤ (ቢያንስ ለሦስት ተከታታይ ትውልዶች ያህል) ከድጡ ወደ ማጡ የሚጎትተን ለምንድን ነው? እውን ኢትዮጵያ ወደብ
ስለምትፈልግ ነውን? ወይስ ኤርትራ ለም መሬት ከኢትዮጵያ ግዛት ለመቁረስ ብላ፣ የኢንዱስትሪ ምርቶቿንና ሸቀጦቿምን በኢትዮጵያ ውስጥ
ያለሁለትዮሽ ንግድ ስምምነት ለማራገፍ ስለምትፈልግ ነውን? ወይስ፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሚደረገው የልዕለ ሃያልነት ሩጫ እሽቅድድም
ውስጥ በልጣ በመልክዓ-ምድራዊ የፖለቲካ አቀማመጧም “ምቹ ነኝ” ብላ ስላሰበች? አይመስለኝም፡፡ ጉዳዩ፣ ውሃ ቀጂዋ ሴትዮ እንዳደረገችው
ያለ፣ ድፍድፉን የመርሳት አባዜ ነው፡፡ ያልሞሉት
እንስራ እንደሚንቦጫቦጨው ሁሉ፤ ያላሰመሩትም ድንበር መቼም ቢሆን ይገፋል፡፡ ……ከሁለቱ
ሱዳኖችም ጋር ያለን ድንበር በቅጡ አልተያዘም፡፡ ዛሬ ወልቃይትና ፀገዴ፣ ነገ ደግሞ የደቡብ ምዕራብ መሬቶቻችን በሄክታር ሰላሳ
ብር ከመቸብቸብ አልፈው፣ ለአንደኛዋ ሱዳን ድርጎ እንደማይሰጡ ምንድነው ማረጋገጫው?!
መላ(ጥበብ)
ሁለት፡- ጠቢቡ ሰሎሞን እና የንግዱ ዘርፍ አዙሪት
ሀ. ይሄ ጥበበኛ ሰውዬው እንደበቅሎ ያሉ “ዲቃላ እውነታዎችን” በምሳሌነት ይናገራል፡፡ እንኳን
በሰሎሞን ዘመንና አሁንም ቢሆን “የንግዱን ዘርፍ አዙሪት” ብዙዎች የሚወስዱት በግለሰብ ደረጃ ነው (at the micro-
economics level)፡፡ እርግጥ ነው፣ ሰሎሞን ስለአንድ ግለሰብ የሚያወራ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ እንዲህ ሲል፤ “ለድሃ
ድህነቱ መጥፊያው ነው፡፡” ትልቅ ጥያቄ ነው የሚፈጥርብኝ፡፡ እንዴት አድርጎ፣ እንዴትስ ብሎ “ድህነት” ድሃውን
ያጠፋዋል? የሚለውን ጥያቄ ሳይሆን፤ “እንዴት መጥፍያው ሊሆን ቻለ?” እያልኩ ነው፡፡ (ምክንያቱም ለድሃው ሕዝብ ድህነት ርስቱ ነው፡፡
ኑሮው ነው፡፡) በመጀመሪያ “ድሃ” የሚባለው የሚበላው በቂ ምግብ፣ የሚለብሰው ንጹኅ ልብስ እና የሚጠለልበት ቤት የሌለው ብቻ ሳይሆን፤ ሙያዊ ክህሎት እና ስልጠናም
የሌለው ብለን እንበይነው፡፡ በመሆኑም፤አንድ ሰው ሳይበላ ሲቀር ይራባል፤ ሲርበውም ይዳከማል፡፡ ከደክመው ደግሞ፣ እንኳን አዲስ
ልብስ ሊገዛ የቆሸሸውንም ልብሱን አያጥበውም፡፡ ያልታጠበው ልብስም መንችኮ ይቀደዳል፡፡ ቀዳዳ ልብስ ደግም በስፌትና በጥፈት ተደርቶ
ተባይ ያመጣል፡፡ ተባዮቹንም ችሎ ስለማየቀምላቸው ተስቦ እና ወረርሺን ያመጡበታል፡፡ የዚህም ጊዜ፣ ሰውዬው የባሰ የምግብ አምሮቱም
ሆነ፣ የመዳን ተስፋው ጨርሶ ይሟሽሻል፡፡ ሰውዬውም፣ እንኳን ቤተሰቡን ሊመራ፣ ያሳደገውን ህብረተሰብ ሊያገለግል ቀርቶ እርሱ-ራሱም
በሌሎች እጅ ላይ ይወድቃል፡፡ ሰሎሞን “የድሃ መጥፍያ ድህነቱ ነው፡፡” ያለው ኃይለ-ቃል ምንኛ ትክክል
ነው፡፡
እስኪ ደግመን ጉዳዩን ከንግዱ ዘርፍ አዙሪት አንጻር እንመልከተው፡፡ በውስን የገንዘብ መጠን
የተቋቋመ አንድ የንግድ ድርጅት፤ እንደ ኢትዮጵያው ባለ ራሱን በስርዓትና በሕግ በማይመራ፣ ነፃነትና ፍትሃዊነት በጎደለው የንግድ
ሂደት ውስጥ ገባ እንበል፡፡ የንግዱ ዘርፍ ገዢ ሲያጣ፣ ደንብና መመሪያ ሲጎለው፣ የሚጠለልበትም ህግና ስርዓት ሲተጓጎልበት መቀዛቀዝ
ይገጥማቸዋል፡፡ የንግዱ ዘርፍም መቀዛቀዝ በርካታ ስራ-አጦችን ያበራክታል፡፡ ስራ-አጥነትም መልሶ የንግድ እንቅስቃሴውን እንደበረዶ
ክምር ያቀዘቅዘዋል፡፡ የድሃ መጥፊያው ድህነት በመሆኑም ያ ውሱን አቅምና ቤሳ-ቢስቲን ይዞ ወደ ገበያ የገባው ነጋዴ ስራ ፍትቶ፣
ታርዞና ተርቦ ይጠፋል፡፡
ስለድህነትና ስለንግድ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ስናነሳም ሰውዬውን፣ የሚበላውን አሳጥቶ፣ መጠለያውን
አስትቶ - ደካማና ልፍስፍስ ያደረገው “ድህነት ነው?” ወይስ ‘የኢኮኖሚው አለማደግ’ ነው ስራ-አጥነቱንና፣ የኑሮ ውድነቱ ያስከተለው?
ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ እነዚህ ሁለት ጥያቄዎች፣ አንዱ የሌላው ውጤትና ምክንያት መሆናቸውንም ማየት ይቻላል፡፡ በምሳሌ እንየው፡፡
ሰዎች፣ ስራ የማግኘት ዕድላቸው ያነሰና የተመናመነ መሆኑን ሲያውቁ፣ ወጪዎቻቸው በእጅጉ ይቀንሳሉ፡፡ የንግድ እንቅስቃስዎችም በዚሁ
የገዢዎች መጪያቸውን የመቀነስ ጣጣ የተነሳ “ዱካክ” ይይዛቸዋል፡፡ ይህ መቀዛቀዝም፣ የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያና
የነዳጅ ዋጋ ጭምርማሪዎች ሲታከሉበት፣ ዜጎች እንኳንም ሌላ የገቢ ምንጭ ሊፈጠሩ ቀርቶ፣ የስራ ዕድልም ሊያገኙ ቀርቶ፣ የያዙትንም
ስራ ዋስትና አጥተውበት “እቀነስ ይሆን? እባረርስ ይሆን?” እያሉ ስጋትና ጭንቀት ያናውጣቸዋል፡፡ (ዛሬ፣
የአሜሪካንና የአውሮፓ ኢኮኖሚዎች (ገበያዎች) በዚህ ዓይነት አዙሪት ውስጥ ገብተው ጓያ እንደበላ ሰው እየተሸመደመዱ ይገኛሉ፡፡
የእኛ ገበያና ገበያተኛም ቢሆን በአደገኛ ሪህና ቁርጥማት መሰቃየቱን ቀጥሏል፡፡)
ታዲያ በዚህ መሰሉ ማጥ ውስጥ ዘው ብሎ የገባው ኢኮኖሚ (ገበያ) እንዴት ብሎ ‹ድህነትን
ተረት› ሊያደርግ ይችላል? የሚል ነው ጥያቄው፡፡ ባለኝ የምጣኔ ሃብት እውቀት መሰረት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት አዋጆች
መታወጅ ይገባቸዋል፡፡ ድህነት ከስሩ ተነቅሎ እንዲወገድ ካስፈለገ፣ ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ ከገዢዎች አፈናና ጭቆና ነፃ መውጣት
አለበት፡፡ በተጨማሪም የኢንደስትሪ መር አብዮት በኢትዮጵያ ምድር ላይ መታወጅ፤ መለፈፍ፤ መሰበክም አለበት፡፡
የሰብዐዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ባክበርና በማስከበሩ በኩል ኢትዮጵያዊን አልታደልንም፡፡
የአምነስቲም ሆነ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ የሚያሳየው ኢትዮጵያ በሰገራው ጉድጓድ ወለል ላይ መሆኗን ነው፡፡ ቅዱስ
ያሬድ “ደብተራ ግዕዛን” (የነፃነት ድንኳን/ ሰማይ) የሆንሺው
ኢትዮጵያ ሆይ እያለ የዘመረላት ኢትዮጵያ የዘር መድሎና የጭቆና አፀድ እየሆነች ነው፡፡ ድህነት ተረት እንዲሆን የዜጎች
ነፃነት ሙሉ ለሙሉ የታወጀባት አገር፣ ነፃነት የተዘመረባት አፈር ትሁን-ኢትዮጵያ! አገዛዝ ይብቃ! አፈናና ጭቆና ይወገዱ፡፡ ያኔ
ታዲያ ድህነት……… (የዚያ ዘመን ሰው ነኝ እኔ! አምናለሁ፡፡ ይሆናል፡፡)
የኢኮኖሚው ዘመቻ በከባድ እና በመካከለኛ ኢንደስትሪዎች ግንባታ ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ለምን?
ቢሉ፤ ኢትዮጵያ ለከባድ ኢንደስትሪዎች የምትበጅተው ወጪ እንደልብ የሌላት ደሃ ሃገር ናት፡፡ (የአደጋ መከላከልና ዝገጁነት ኮሚሽን
እንደሚነግረን ከሆነማ ሚሊዮኖች የሚሆኑት ህዝቦቿ በአስከፊ
የምግብ እርዳታ ጥሪ ላይ ናቸው፡፡ ‹የደሃ መጥፍያው ድህነቱ ነው!› ብለናልና፣
ኢትዮጵያን በአንድ ደሃ ግለሰብ ብንመስላት የምግብ፣ የልብስ እና የመጠለያ እንዲሁም የኃይል ምንጭ እጥረቶች አሉባት፡፡
ስለዚህ፣ ዘመን በርቆ ዘመን ሲተካ እየደከመች፣ ከዘመን ዘመንም እየሰለለች፣ ህመሟ እየፀናባት እንዳትሄድ፣ የገዛ ህዝቧን ሆድ እንኳ
መሙላት ካልቻለው የግብርና መር የኢኮኖሚ ስርዓት በብዙ እጥፍ ዋጋና ፋይዳ
ወዳለው ኢንደስትሪያላዊ አብዮት መሄድ ያስፈልጋል፡፡
አነስተኛና ጥቃቅን፣ ኮብል ስቶንና በማህበርና በሊግ ወጣቱንና ሴቶችን በማደራጀት ስንዝር መጓዝ
አይቻልም፡፡ የትም አያደርሰንም፡፡ ሃያ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑትን የትግራይ፣ የአማራና የደቡብ ኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በነፃ ለአርባ
ቀናት እርከን በማሰራትና በቀን ከሰላሳ እስከ አርባ ብር (30-40) በመቆንደድ የወረዳ ካቢኔ አባላቱን ኪስ ከማጠርቃት በስተቀር
ከድህነት አይገላግልም፡፡ ሰሞኑን የትግራይ፣ የአማራና የደቡብ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የሚያሰዩት የነፃ ሕዝብ መገለጫዎች አይደሉም፡፡
የሚሊሻ መንግስት (Police-Stateship) እየመጣ እንደሆነ ያሳብቃል፡፡
ሀገረ-ቻይናን እንደ በጎ መዴል (ማሳያ) መውሰዱ አይረባም፡፡ ኢትዮጵያ የነፃነት ድንኳን
(ምድር) ናት፡፡ (ቃል ነው፡፡ ትንቢት ነው፡፡ “ትንቢት ይቀድም ወዘነገር!” እንዲል፡፡) በ18ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምረው
እያደጉ የመጡት የአውሮፓና የአሜሪካንም እድገት መሰረቱ ኢንደስተሪያላዊ አብዮት ነው፡፡ ያን ጊዜም ነው ድህነት ተረት የሚሆነው፡፡
በመንግስት ቁጥጥር ስር ባሉት መገናኛ ብዙኃን ላይ የባጥ-የቆጡን በመደስኮር፣ ወይም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ፕሮቶኮል በማሳመር
ኢትዮጵያ ድህነትን ተረት አይሆንም፡፡ መጀመሪያ ነፃነት! ቀጥሎም ነፃነት! ከዚያ በኋላ ኢንደስትሪያላዊ አብዮት መታወጅ አለበት፡፡
ለ. “ፈጥኖ የሰጠ ደግሞ ይሰጣል!” ይባላል፡፡ አባባሉ ከመጽሐፈ ምሳሌ ከተዋስነው የሰሎሞን ጥቅስ ጋር የሚመሳሰል
ነው፡፡ ሁለቱም፣ በግለሰብ ደረጃ ስለተቸገረ ድሃና እርዳታ ፈላጊ ሰው ይጨነቃሉ፡፡ አስቸኳይ ትኩረትና እርዳታ ስለሚያስፈልገው ችግረኛ
ሰው የተባሉ ቢመስሉም፤ በጅምላው በበርካታ ችግሮች እግር ተወርች ስለተቀፈደደች አገርም እንድናስብ ያደርጉናል፡፡ አሁኑኑ፣ የስራአጥነትን፣
በአስር ወይም አስራ-ምናምን አጥፍ እየፈለፈለ ያለ ኢኮኖሚ፣ የንግድ መቀዛቀዙን በአስራ ሁለት ወይም በአስራ አምስት እጥፍ እየጨመረ
ቢሄድ አያስደንቅም፡፡ ከዚህ ሁሉ ስጋትና ፍርሀት ለመውጣት - ዛሬውኑ ፣ አሁኑኑ የኢንዱስትሪ -መር አብዮት ይታወጅ፡፡ (ብዙ-ብዙ
የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተር ተብዬዎች ከባለስልጣናቱ ጋር ሳይሞዳሞዱ ሰባራ ሳንቲም እንኳን ማፍሰስ እንደማይፈቀድላቸው
አያወቅኩ ነው የኢንደስትሪ-መር አብዮት ይታወጅ የምለው፡፡ ማለቴ መጀመሪያ ነፃነት ይከበርና!)
ለምሳሌ፣ የሲንጋፖርም ሆነ የቻይና፤ የህንድም ሆነ የብራዚል ኢኮኖሚ ኢንደስተሪያላዊ መሆን
ሲጀምር ነው- ህዝቦቻቸው ከስራ-አጥነት አዙሪት መውጣት የጀመሩት፡፡ ሀገሮቹም ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ በሽታዎቻቸው መዳን የቻሉት፡፡
ኢትዮጵያም ከያዛት ልክፈት እንድትድን፤ ስራ-አጦች ስራ እንዲያገኙ፤ የግብርናውን ዘርፍ ጥለው ወደ ከተሞችና ወደ አረብ አገራት
እየተሰደዱ ያሉትም ሆኑ ከተሜዎቹ፣ ኢንደስተሪዎች ውስጥ ገብተው ምርታማ እንዲሆኑ፤ የተሻለ ገቢም ማግኘት ችለው፣ ከገቢያቸውም እንዲቆጥቡና
ደፍረው - የንግዱን ዘርፍ እንቅስቃሴ የተጠየቁትን ዋጋ በመክፈል እንዲያነሳሱት - ኢንደስትሪ-መር አብዮት ያስፈልጋል፡፡ ያንጊዜም፣
ይኼኛውም ትውልድ የራሱን “የአድዋ ድል” ይቀዳጃል፡፡
መላ(ጥበብ) ሦስት፡-
የመዘናጋት አባዜና-አስከፊው ፈተና
መቼ ተዘናጋን? ለምን ተዘናጋን? እንዴትስ ተዘናጋን? … ለመሰረተ ልማት ግንባታ ከመደበኛው
በጀት ላይ የምናወጣው መንግስታዊ ወጪ ከፍ ሲል፣ የንግዱ እንቅስቃሴ ይቀዛቀዛል፡፡ (የዚህ ጊዜ ምእራባዊያኑ ድጎማ (Bail-out
ወይም Osterity) የሚሉት ‘መልከ-ጥፉን፣ በስም ይደግፉ’) ኪሳራ ይከተላል፡፡ ወይም ደግሞ፣ የንግዱ እንቅስቃሴው ሲነቃቃና
የመንግስት የቋሚ መሰረተ ልማቶች ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ሲቀንስ፣ የንግዱ አዙሪት ሊያስከትል የሚችለው ክፉ አዚም ይቀንሳል፡፡ የንግዱን
መስክ እንደ ጥንጣን የሚበላው ሙስናም ሆነ በዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ቀንሱ እየተባልን የምንጨቀጨቅበት የመደበኛ ወጪ ርዕስ ቀርቶ
ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ኢኮኖሚ ይኖራል፡፡
እዚህ ላይ የመዘንጋትን አባዜ በማጣቀሻ ላስረዳ፡፡ “የክደት ቁልቁለት” በተባለው መጽሐፋቸው
ውስጥ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም እንደገለፁት፤ ቀድሞም በጀኔራል ናፔር ዘመቻ ወቅት-መቅደላ ላይ፣ በኋላም በደርቡሽ ጦርነት ወቅት-መተማ
ላይ፣ ከዚያም በአድዋ ጦርነት ወቅት-አድዋ ላይ፣ በሦስቱም ፀረ-ወረራ ታጋድሎዎች ወቅትና በ1983ዓ.ም ጭምር የኢትዬጵያዊያን የመዘናጋት
አባዜ በጉልህ ተረጋግጧል፡፡ እንግሊዝ-መድፉን በዝሆንና በፈረስ ሲጭን፣ ደርቡሽም-ግመሎችን ሲጠቀም፣ ጣሊያንም-የመርከቦቹን መልህቅ
ምፅዋና አሰብ ላይ በ1888 ዓ.ም ሲጥል፣ በ1928ዓ.ም ደግሞ ንስር አሞራ የመሰሉ የጦር አውሮፕላኖቹን ይዞ ባህር አቋርጦ ሲመጣ፤
ዝንጉው የኢትዬጵያ ጦር በመቅደላም፣ በመተማም፣ በአድዋም ጊዜም ሆነ በአምስቱ አመት የፀለ-ወረራ ዘመን ያንኑ አህያ የተባለ
ፍጡር ሲጭን፣ አህያ ሲነዳ፣ አህያም ላይ ቀለቡንና ቁስለኛውን ሲጭን ታይቷል፡፡ የመዘናጋት አባዜው አሁንም ድረስ ከአዲስ
አባባ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በጉልህ ይታያል፡፡ ገበሬዎቻችን በብዙ ሚሊዮን መዋዕለ-ንዋይ በተሰሩት መንገዶች ላይ አህዮቹን
ከነመጫኛዎቻቸው ይነዳሉ፡፡ የነደስትሪ-መሩ አብዮት መጥቶ የገበሬዎቻችን የጭነት መገልገያዎች በዘመናዊ የኢንደስተሪ ውጤቶች እስከሚተካቸው
ድረስ ናፍቆኛል፡፡ (የዚያ ሰው የበለን! - አሜን!)
ዝንጉነትን በተመለከተ ባህሪው የሰው ሳይሆን የአህያ ነው፡፡ አህያ ደንገዝገዝ
ሲል ግጦሽ በአፍላ ወኔ ትጀምራለች፡፡ ቀኑን አመድ ላይና ጥላ ስር ስትንከባለልና ስትተኛ ውላ ሲመሽ ግጦሽ ያሰኛታል፡፡ ጠገብ
ስትል “ቀበተተኝ ልጩህ” እያለች ታስብና፣ ምናልባትም አምልጧት ትጮሃለች፡፡
ተረቱ የልጆች ቢሆንም አንድምታውን ተጠቅመናል፡፡ ኢንዱስትሪ መር የሆነ አብዬት ሳይታወጅ ቀርቶ ብንዘናጋ ፣ አያ ግሎባላይዜሽን
ደርሶ እንዳይሰለቅጠን ያሰጋል፡፡ እኛም በድህነት ፋንታ ታሪክ እንሆናለን ፡፡
ምላሽ ይስጡሰርዝGreat post and success for you..
Kontraktor Pameran
Kontraktor Booth Pameran
Kontraktor Booth Pameran
Jasa Pembuatan Booth
Great post and success for you..
ምላሽ ይስጡሰርዝKontraktor Pameran
Kontraktor Booth Pameran
Jasa Pembuatan Booth
Jasa Dekorasi Booth Pameran
Great post and success for you..
ምላሽ ይስጡሰርዝKontraktor Pameran
Kontraktor Booth Pameran
Jasa Pembuatan Booth
Jasa Dekorasi Booth Pameran