15ቱ የዓለማችን ታላላቅ ቀናት

(አድዋ ናት አንድዋ!)

            (በሰሎሞን ተሰማ ጂ. /ከአ.አ)      semnaworeq.blogspot.com


የዓለምን ታሪክ ስናስብ፣የአንዳንድ ሰዎች ታሪክና አስተዋጽኦ የላቀና የደመቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡የፈጠራ ስራዎቻቸው፣ የፈለሰፏቸው ግኝቶች፣ ያሰረጿቸው አስተሳሰቦችና አስተምህሮቶች ሳይቀሩ ከፍ ያለ ዋጋ አላቸው፡፡ አንዳዶቹማ የረገጧቸው ቦታዎች ሳይቀሩ የተለዩና እፁብ ድንቅ ተፅዕኖን አስፍነዋል፡፡ እንኳን ሰዎቹ፣ ቦታዎቹም ቀላል የማይባሉ ተጓዦችና ጎብኝዎችንም አፍርተዋል፡፡ እነእየሩሳሌምና መካ-መዲናማ ተሳላሚም አጉርፈዋል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ቦታዎች የተቀበሩተን ቅዱሳንና ነቢያት መካነ-መቃብር ለማየትና ለመፀለይ የማይሄድ ማን አለ?
መቼም፣ በሺህዎች ከሚቆጠሩት የታሪክና የሥነ-ጽሑፍ ጥራዞች ውስጥ፣ 15ቱን መርጦ ልዩ ትርጉምና ፋይዳ ያላቸው ታላላቅ ቀናት “ናቸው” ለማለት ብርቱ ፈተና አለው፡፡ የቀናቱን ትክክለኛ ወርና ዘመን ለማወቅ መሞከሩም ምን ያህል አድካሚ መሰላችሁ፡፡  
እንደውቅያኖስ ጥልቅ ከሆነው የዓለማችን ታሪክ ውስጥ 15ቱን ታላላቅ ታሪካዊ ቀናት ለመምረጥ ተሞክሯል፡፡ የዓለምን አቅጣጫ ከቀየሱት ፈጠራዎች መካከል የጥይት አረር፣ የህትመት መሳሪያ፣ የእንፋሎት እንፍርፍሪት፣ የኮረንቲ ሞተር፣ የአሜሪካንን መገኘትና ታላላቅ የጦር ሜዳ ውሎዎችን ሳይቀር ከተፈፀሙበት ዘመን በኋላ ያላቸውን ጫናና ተጽእኖ ለማመዛዘን ሞክሬያለሁ፡፡ በየክፍለዘመኑ ከተነሱት ታላላቅ ገዢዎች እና ነገስታትም፤ ለአብነትም ያህል፡- ሃሙራቢን፣ ሙሴን፣ ቀዳማዊ ዳሪዎስን፣ ፐርክሊዝን፣ ታላቁ እስክንድርን፣ ቄሳርን፣ ቻርለስ አምስተኛን፣ ንጉስ ሊዊስ አስራ አራተኛን፣ ታላቁ ጴጥሮስና ፍሬድሪክን፣ ሄነሪ ስምንተኛውን፣ ንግስት ኤልሳቤጥ ቀዳማዊትን፣ጆርጅ ዋሽንግተንን፣ ሊንከንን፣ ሚኒሊክን እና ቸርችልን የመሳሰሉ ታላላቅ መሪዎች የህይወት ታሪክና ገድል በግድ ማንበብ ያሻል፡፡
ከፈላሳፋዎቹም፡- ለምሳሌ ኮንፊሽየስ፣ ሶቅራጥስ፣ ፕሌቶ፣ አሪስቶትል፣ ሄግልና ማርቲን ሃይዲገር እንዲሁም ሌሎቹንም ለማጥናት መጣር ያስፈልጋል፡፡ ከሳይንቲስቶቹም የኮፐርኒከስን፣ የጋሊሊዮ ጋሊሊን፣ የአይዛክ ኒውተንን፣ የዳርዊንን፣ ፣ የቶማስ ኤዲሰንን፣ የኒኮላ ቴስላንና የአልበርት ኤነስታይንን የመሳሰሉ ሰዎችና የዘመናቸውን ተጨባጭ ኩነት መመርመርም ግድ ይላል፡፡ የዓለማችንን የሩቅና የቅርብ ጊዜ ቅዱሳንና ሰማዕታትን ለምሳሌም፤ የነብዩ ኢሳያስን፣ የጉተማ ቡድሃን፣ የእየሱስ ክርስቶስን፣ የማርቆስ አውሬሊየስን፣ የአውግስቲንን ፣ የኦሲሲው ፍራንሲስን፣ የሎያላን፣ የማርቲን ሉተርንና የማኅተማ ጋንዲን ምግባሮች ከነአስተምህሮቶቻቸው እና ከነሃይማኖታዊ ፈለጋቸው በነፃ አእምሮና በፈራጅ ሕሊናም ለማነፃፀር ያሻል፡፡
በየዘመኑ የተነሱትን አንጋፋ ባለቅኔዎች፣ ለአብነትም እንደሆሜር፣ ዳዊት፣ ዩሪፒደስ፣ ቨርጂል፣ ሆራስ፣ ሊ-ታይ-ፓ፣ ዳንቴ፣ ሼክስፒር፣ ሚልተን፣ ጐተ፣ ፑሽኪን፣ ኪት፣ ባይሮን፣ ሼሊ፣ ሁጐ፣ ኤድጋርአለንፖ፣ በርናንድሾውንና ታጐርን፤ እንዲሁም ከታላላቆቹ የዜማና የሙዚቃ ቀማሪዎች መካከል እነቅዱስ ያሬድን፣ ፓሌስትሪናን፣ ባቺን፣ ሔንዴልን፣ ሞዛርትን፣ ቤቶቨንን፣ ቶፒንን፣ ሊሲዚትን፣ ፓጋኒኒን፣ ብራህማስን፣ ፃቻይኪውስኪን፣ ቨርዲን፣ ዋግነርን፣ ፓዴሬውስኪንና ስትራቪንስኪይንም ላይ የተፃፉት ሂሳዊ ዳሰሳዎች ጐድፍሬያለሁ፡፡ እግረ መንገዴን ከፍተኛ ክብርና  ዝና የተቀናጁትን የስዕልና የቅርፃቅርጽ ጠበብት እነካርናክና ሉክሶርን ብሎም እንደግብጽ ፒራሚድና የአክሱም ሃውልቶች ያሉትን ቀራጺያን ባለታሪኮች ታሪክ፣ እንደ’ነ  ፊዲያስና ፕራክሲቲለስ፣ ው - ታቲዙና ሴሲሂኡ ብሎም ሆኩሳይ፣ ቻርትረስና ታጂማል፣ ጐይቶና ዱሬር፣ ሊዎናርዶ ዳቬንቺ፣ ራፋኤልና ሚካኤል አንጄሎ፣ ቲቲያንና ኮሬግሎ፣ ኤልግኮና ቨላስኩዌዝ፣ ሬምብራንትና ቫን ዲይክ፣ ሬይኖልድስና ጋይንስብሮፍ፣ ተርነርና ዊስለር፣ ሚሌትና ቼዛኔ፣ ፒካሶንና አፈወርቅ ተክሌንም አጥንቻቸዋለሁ፡፡ በተለይም፣ ሊዎናርዶ ዳቬንቺ ያሳደረብኝን ግርምትና ተጽዕኖ ለመሸሸግ አልሻም፡፡
ታላላቆቹን የስድ-ንባብ ፀሐፊያን ባልዘነጋቸውም ቅሉ፣ ለጊዜው ትቻቸዋለሁ፡፡ በመሆኑም አንባቢያንን ቢካተቱ ኖሮ ምን ነበረበት ያሏቸውን የምግባረ-ሰናይ፣ የድርሰትና የጥበብ ባለሙያዎች በጎደለው ቦታ እንዲሞሉልኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡ ምናልባትም ደግሞ እንደንግስት ሃሺፊስተና እቴጌ ሰብለወንጌል፣ ከኖቤል ተሸላሚዎቹም እነሜሪ ከዩሪንና እማሆይ ተሬሳን ቢያካትቷቸው ተገቢ ነው፡፡
“ታሪክ ራሱን ይደግማል!” የሚል ይትብሃል አለ፡፡ የታሪክ አተረጓጎምና አተናተን ስልቶች እንደእስስት ተለዋዋጭ ቢሆኑም ቅሉ፤ አንዱ ታሪካዊ ክስተት ሲታወስ ሌላኛው ኩነት በአእምሮአችን መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ (……በመግቢያዬ ላይ ያልኩትን ሁሉ ብዬ፣) ቀጣዮቹን 15 ታላላቅና ድንቃይ ቀናት በዘመን ቅደም ተከተል መሰረት እነሆኝ ብያለሁ፡፡ (የዘመን አቆጣጠሩ በሙሉ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ) መሆኑን ላስታውስ አወዳለሁ፡፡ ቅ.ል.ክ ስልም ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው፡፡ 
1.   ግብፃዊያን የዘመን መቁጠሪያ (ካሌንደር) ያስተዋወቁበት አመት (4241 ቅ.ል.ክ.)
ይህ የዓመትና የዘመን መተመኛና መቁጠሪያ ቀመር ቀዳሚው “ድንቅ” ግኝት ነው፡፡ የተወሰኑትን ሚስኪን ሰዎች ደግሞ ሊያበሳጫቸው ሁሉ ይችላል ፡፡ በተለይም ዓለም የተፈጠረችው 4004 ቅ.. ነው የሚሉትንና፣ “ዓለምም መጥፊያዋ ቀርቧል”  እያሉ ለሚያላዝኑ ሟርተኞች፣ ይህ ግኝት “እህል-ውኃም” የማያሰኝ መርዶ ነው፡፡ ለነዚህ ወገኖች፣ የጥንታዊት ግብፅ የጥናት ባለሙያዎች የሚያረዷቸው “ወሽመጥ-በጣሽ” ሰብር ዜና ቢኖር፣ የሰው ልጅ የቀን መቁጠርያን “ዓለም ተፈጠረች” ብለው ከሚያምኑበት ጊዜ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በታችኛው ናይል ተፋሰስ ላይ መቀመሩን ማወቃቸው ነው፡፡
ለብዙ ተመራማሪዎች እና አጥኚዎች የዚህ የዘመን መቁጠሪያ ትርጉምና ፋይዳ የትየሌሌ ነው፡፡ የስነ ክዋክብትና የሂሳብ ስሌት ድንጋጌዎችን ከማጎልብቱም ሌላ፣ሰዎች የመርከባቸውን አቅጣጫ፣ ፀሀይ በመሬት ዙሪያ የምታደርገውን ኡደታዊ የወቅቶች መፈራረቅም አብስሯል፡፡ የዓመቱን ወራት በአስራ ሁለት ከፋፍሎ፣ ወርሀ ጶጉሜን በየአራት አመቱ ስድስት፣ በየስድስት መቶ አመቱም ሰባት አድርጎ ከበየነ በኋላ፣ በግብፃውያን አዕምሮ ውስጥ የአባይን መሙላትና መጉደል (ወይም እየሞላና እየጎደለ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ የዳበረን ስልጣኔ ስለመሆኑ በብቃት ቀምሯል)፡፡ ከዓመት ዓመት እንደ ወቅቱና እንደ ጊዜው የሚያሥተማምን መንግስታዊ ስርዓትን፣ ምርታማ ኢኮኖሚን፣አስተማማኝ ፀጥታንና የሀብት ክምችትን፣ የውሃ ግደባና የመስኖ ጥበብን፤ ምቾትን ለሰውነት፣ መዝናናትን ለስሜት፣ መመሪያ ሕግን ለአዕእምሮ ደንግጓል፡፡ የዓባይ ጅረት ያመጣውን ሸክላማ ደለል ወደጡብነት ቀይረው ታላላቆቹን ፒራሚዶች ሲገነቡ፣  የካርናክን ቅጥር በሳልሳዊ ቱቲሞስ ሲከተምና ንጉስ ኤከናተንም ንግስናውን በአንዲት ልብ የምታማልል ዜማ ምክንያት ሲሸጠው፣ እና በዚያች ትንግርተኛ ዜማም መነሻ ስለ “ዘላለማዊው አንድ ዓምላክ” ህልውናና ስለአንዲት ፀሀይ ብቻ መኖር፣ ሲዘምርና ሲያሸበሽብ ሳለ፣አይሬሴዋ ክሊኦፓትራ አንቶኒን በቤተ-መፅሐፍቷ ውስጥ በድብቅ አንገቷን አስግጋ፣ እርሱም አፍንጫውን አሰልክኮ ሲቃለጡ ሳለ - ሰዓትና ቀናትን ፣ወራትንና ዘመናትን መቁጠሪያ ካሌነደር ነበራቸው፡፡ ይህንን ዘመን የመጀመሪያው ታላቅ ቀን ነው ለማለት ያሰደፍራል፡፡ ተፅዕኖው ዛሬ ድረስ ዘልቋልና፡፡

2.   የጉተማ ቡዲሃ ሕልፈተ-ህይወት - 543 ቅ.ል.ክ.
እንደምረዳው ከሆነ፣ የትኛዋም ምድራዊ ነፍስ የጉተማ ቡድሃን “ነፍስና መንፈስ” ያህል በህንዳዊያን ላይ ተፅዕኖ አላሳረፈችም፡፡ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶች የጌታ ቡድሃን እምነትና አስተምህሮቶች ተቀብለው በቡዲሃነት ይኖራሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣በተለያዩ ጣኦታት አምልኮ የተጠምዱት ህንዳዊያንና የቡዲዝም ተከታዮች፣ የጌታ ቡድሃን አስተምሮቶች ተከትለዋል ማለት ይከብዳል፡፡ በስሙ የሚቆምሩ በርካታ አፈታሪኮችንና መለኮቶችን እየጠቀሱ፤ ልክ ካልቪን፣ ቶረኩውሜዳና ቴነሲ በክርስምቶስ ስም እንደ ወነበዱት ሁሉ - ጌታ ቡዲሃንም ማላገጫ አርገውታል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ቡዲሃ ማለት ህንድ ናት! ምክንያቱም፣ ህንድነቷ መንፈስ ያለው በቡዲሂዝም ሃይማኖቷ እንጂ በሳይንሳዊ ምርምሯ ላአይደለም፡፡ በቡዲሃዊ በጐ ምግባሯ እንጂ፣ በምድራዊ ምግባሯም አይደለም፡፡ የወንድማማችነት እሴት በመፍጠሯ እንጂ፣ ሒሳብን ለጠመንጃ መስሪያነት፣ ኬሚስትሪን ለፈንጂ መቀመሚያነትና ፊዚክስንም ለኒውክለር መሳሪያ መስሪያነት ስላዋለች አይደለም፡፡
ጌታ ቡዲሃ እንደሚለው ከሆነ፣ “ህይወት በአሳርና በመከራ የተሞላች” ናት፡፡ ስለዚህም፣ አሳርና መከራውን ለማለዘብ የሚቻለው በማንኛውም ህይወት ባለው ፍጡር ላይ ጉዳት ባለማድረስና ክፉን ነገርም ለማንም ወንድም ሆነ ሴት ባለመናገር ነው፡፡ ክፉን ነገር ሁሉ በበጎ መመለስ አስፈላጊ ነው” ይላል፡፡ (ቅጠል የማይበጥሱትንና ሱባዔ የሚይዙትን መነኮሳት፣ እንዲሁም ተባይና ዝንብ እንኳን የማይገሉትን ባህታዊያን ልብ በሉ፡፡ ቅሌን ጨርቄን የማይሉት የክርስቲያን መነኮሳትና ባህታዊያን የቡዲሂዝምን አስተምህሮቶች የህይወታቸው መመሪያ አድርገው ይኖራሉ፡፡)
መቼም ጎራ ለይተው፣ አንጃና-ገራንጃ ፈጠረው ከቡዲሂዝም የተለዩት የሂንዱ ኃይማኖት ተከታዮች- የላም ወተቷንም ሆነ ስጋዋን የማይመገቡት፤ በላሟ ለይ ክፉን ላለማድረስ ሲሉ ነው፡፡ የቡዲሃ መነኮሳት በየትኛውም ኢ-ፍትሐዊነት፣ ባርነትና መድሎ ላይ ክንዳቸውን ያነሳሉ! ቡዲሃ በብልሆቹ የህንድ መሪዎች ላይ ከአሶካ እስከ ጋንዲና ታጎር የዘለቀ ተፅዕኖና ስነ-ሥርዓት አስርጽዋል፡፡ የቲቤታዊያን መንፈሳዊ መሪ የሆኑትን ዳይላ ላማንም ለግማሽ ከፍለ-ዘመን በፅናተና በቁርጠኝነት “ነፃነት ወይም ሞት፻” የሚያስብላቸው ይሄው ምንኩስናቸው ነው፡፡ (የእጆቻችንን መዳፎች አገጣጥመን ጌታ ቡዲሃንና ህንዳዊያንን “ናማስቴ” ወይም “በእናንተ ውስጥ ላለው አምላክ እጅ እነሳለሁ!” ልላቸው እወዳለሁ፡፡ “ናማሰቴ! ናማስቴ!”)  
3.   የኮንፊሽየስ እልፍተ ሞት - 478 ቅ.ል.ክ.
ሀገረ ቻይናን በምን ምሳሌ እንመስላት? (ግዕዙ፣ “ናስተለ ምስለኪ ወሀገረ ቻይና!” እንዲል፡፡ ለቻይና መቼም ከባንዲራዋ በላይ የሆነ አርማዋና ተምሳሌቷ ኮፊሽየስ ነው፡፡ ከግዛቷ ስፋት የትየለሌነት ሌላ በህዝቧም ቁጥር ስለምትመካ፣ “ሁሉም ነገር ከመንግስተ-ሰማያት በታች!” አለኝ ትላለች፡፡ ከአራት ሺህ ዓመት በላይ በንጉሳዊ ዘውድ ጥላ ስር የቆየችውን ቻይናን፣ ኮንፊሺየስ ፍጹማዊ በሆነው ጥበቡ፣ በትንሽዬ ክፍል ውስጥ በከበሩ ማዕድናት የታጨቁ በሚመስሉ አስተምህሮቶቹ የቻይናን ኪነ-ጥበብ፣ ስነ-ጥበብና ፍልስፍና አንቦግቡጎታል፡፡አድምቆታል፡፡  
እስቲ፣ ከዛሬ 2,500 አመታት በፊት፣ “ትልቁ መማሪያ” (ወይም The Great Learning ከሚለው ክፍለ-ትምህርቱ አራተኛውንና አምስተኛውን ክፍል እንቃመስለት፡፡ እንዲህ ብሎ ይጀምራል፤
ነገርን በምሳሌ መዘርዘር የሚያምኑት ጥንታውያን ሊቃውንት፣ በዓለም ላይ ያለውን የላቀ መልካምነት በማያሻማ ሁኔታ ሲገልፁት ሀገር በትክክለኛው ሥርዓት መቀመጥ አለባት፡፡ ሃገር በስርዓት ከመቀመጧ በፊት፣ ቤተሰብ ሥርዓት የያዘ መሆን አለበት፡፡ ቤተሰብም ሥርዓት ከመያዙ በፊት፣ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ነፍሱን ኮትኩቶ ብፂዒት ያድርጋት፡፡ ከነፍሳቸውም ብፅዕና በፊት፣ አስተሳሰባቸው ለራሳቸው ታማኝ መሆን መጣር አለባቸው፡፡ በአስተሣሰብም ታማኝ ለመሆን ከመጣራቸው በፊት፣ እውቀታቸውን እስከመጨረሻው የዕውቀት አድማስ ጫፍ ለማድረስ መፍጨርጨር፤ እስከፍፃሜውም ለማወቅ የሚቻለው ነገሮችን በመመርመርና እውነታውን ሳይቀንሱና ሣይጨምሩ በማጤን ነው፡፡ ነገሮችውን በእንዲህ ያለ ሁኔታ የሚያጤኑና የሚመረምሩ ከሆነም ምሉዕ የሆነ ዕውቀት ይገኛል፡፡ ዕውቀት ምሉዕ ሲሆን፣ አስተሳሰብም ተዓማኒ ይሆናል፡፡ አስተሳሰባቸውም ተዓማኒ ሲሆን፣ ነፍሳቸው ፍፁም ትሆናለች፡፡ ነፍሳቸው ፍፁማዊት ስትሆን፣ ማንነታቸውም የተኮተኮተ ይሆናል፡፡ ማንነተም በትክክል ሲኮተኮት፣ ቤተሰብም ስነ-ሥርዓት ያለው ቤተሰብም ሥርዓት ያለው ሲሆን፣ መንግስትም በትክክለኛው ሥርዓት ይመራል፡፡ መንግስትም በሥርዓት ሲመራ፣ ሞላዋ ዓለም በሰላምና በደስታ የተሞላች ትሆናለች፡፡ 
መቼም ምሁራን ስንባል፣ “ከቁንጫ መላላጫ” ለማውጣት  ስንጣጣርና ነገሮችን እንዳሉ፣ ፀጉር  ሳንሰነጥቅ ለመቀበል (ማለትም፣ ዲሞክራሲን፣ አገዛዝን፣ ትንሳኤን፣ ጓደኝነትን፣ ግብረ-ገብነትን፣ ምርጫን፣ ሥርዓትንና የመሳሰሉትን)፣ ለአስተሳሰቦቻችን ተዓማኒ አይደለንም፡፡ ምክንያቱም ነፍሳችንን ስላነፃነው ነው፡፡ ነፍሳችንንም ኮትኩተን ስላላነፃነውም፣ ራሳችንን ስነ-ሥርዓታዊ አላደረግነውም፡፡ ሥርዓታዊ ማንነትም ስለሌንም፣ ቤተሰቦቻችንንም በሥርዓት አናስተዳድርም፡፡  ቤተሰቦቻችንንም በትክክለኛው ስርዓት ካላሰተዳደርን፣ ሀገራችንም ሥርዓት አልበኝነት ይነግስባታል፡፡ (እንዴት ያለ ጥልቅ አስተምህሮት ነው ጃል!)
ለዚህም እኮ ነው፣ “ቻይና ስትታሰብ ኮነፊሺየስ ከባንዲራዋም በላይ ተምሳሌታዊ አርማዋ ነው” ያልኩት፡፡ እስኪ ከኮንፊሽየስ ጀርባ የተንጠለጠሉትን የኪነጥበብ ሰዎች እናንሳቸው፤ የታንግ ስርወ-መንግስት ገጣሚዎችና አቀንቃኞች ጥዑም ዜማዎች፤ በሕብረ-ቀላማት የተንቆጠቆጡትን ሕልማዊ መልክዓ-ምድሮች የሳሉትን ቻይናዊ ሰዓሊዎች፤ ከእንከን-የለሾቹ የቻይና ሸክላ እና ቅርፃቅርፆች ላይ ያረፉትን ንድፎች፤ ዓለማዊና ሥነ-ፈለካዊውን ጥበብ የመሩትን ፈላስፎች እና ምናልባትም ቻይና ውስጥ የተደረጉትን ሁሉ ታላላቅ የሥልጣኔ እርምጃዎች በሙሉ በአንድ ቃል ቢጠቃለሉ ኖሮ “በስመ-ኮንፊሺየስ” ነው ሊባሉ የሚችሉት፡፡  
4.   ተፍፃሜተ ህይወት ዘሶቅራጥስ - 399 ቅ.ል.ክ.
የእባብ መርዝ ጨልጦ፣ የዚህ ታላቅ ሰው ህይወት  ሲፈፀም፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረውዘመነ-ፐርክሊዝ”ም ተፈፀመ፡፡ በዘመነ-ፐርክሊዝ ስለነበረው ፍልስፍናና ክንውን ለጊዜው ተወት ሳደርገው፣ ከሶቅራጥስ ጀርባ ጓደኞቹና አፍቃሪዎቹን፣ አልኪቢያደስ እና እጅግ አፍራሽ እና አሳዛኝ የነበረውን የፔሌፓንያስን ጦርነትን ያስታውሰኛል፡፡ ዝነኛው የሕግ ሰው አስፓሲያን ከፍ ያለ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ፣ ከእግሩም ስር ድንጋይ ላይ ከፐርክሊዝ ጋር ተቀምጠው፣ ፐርክሊዝ ሆዬ የአቴንስን ድራማ በገንዘብ እንደጉመው “እባካችሁ-እባካችሁ” እያለ፣ የአማልዕክቱን ስም እየጠራ ሲማጠን ይታየኛል፡፡ ዩሪፒደስና ሶፎክለስ በዳዮነስስ አመታዊ የቲያትር ዝግጅት ላይ “እኔ እበልጥ! እኔ አበልጥ!” እያሉ ለድራማ ጥበብና ሽልማት ሲወዳደሩ ፊቴ-ድቅን ይልብኛል፡፡
ኤክቲነስ በዝግታ እየተራመደና እየተንጎራደደ እለታዊውን የወሬ/ጋዜጣ አምዱን በሃሳቡ ሲያረቅ፤ ፊዲያስም የአማልዕቱንና የግሪክን ታላላቅ ጀግኖች ፊትና ገጽታ ሰቀርጽ ይታየኛል፡፡ ወጣቱና አፍለኛው ፕሌቶ በፓንቴኒያን እስፖርታዊ ጨዋታዎች ላይ ተወዳድሮ ክብረወሰን ሲሰብር ገጭ ይልብኛል፡፡  ከሁለት ሺህ አራት መቶ አመታትም በኋላ እነዚህ የሶቅራጥስ ተከታዮች በስልጣኔ ለመኖር ቆርጠው፣ በከዋክብት፣ ፀሃይ፣ በጨረቃ፣ በባሕር እና በውቅያኖስ ማምለክ አቁመው፣ ሳይንስን፣ ድራማን፣ ዲሞክራሲን እና ነፃነትን ፈጥረው ለሮማ እና ለአውሮፓ የኪነጥበብ፣ የፖለቲካ እና የሳይንስ ተመራማሪዎች በትረ-ስልጣኔያቸውን ለዓለም አቀበሉ፡፡
የደልፊ ቤተ-መቅደስ ውስጥ፣ “መጀመሪያ ራስህን እወቅ!” የሚለውን አስተምህሮት (Maxim) ተቀብሎ፣ ለደቀመዛሙርቱ ማስረጽ በመቻሉ፣ “የፍልስፍና አባት” ለመባል በቅቷል፡፡ በተለይም፣ ላመነበትና ለፈለጉ ሲል፣ አደገኛ የከይሲ መርዝ አጠጥተው ገደሉት፡፡ ነፍስ-ሔር ለሶቅራጥስ!
5.           የጁሊያስ ቄሳር መገደል - 44 ቅ.ል.ክ.
“የሮማን ሪፐብሊክ ወደ ግሉ ዘውዳዊ ስረወ-መንግስት ሊቀይር ይፈልጋል፤” በሚል ከንቱ ጥርጣሬና ስጋት፣ የተከበረው (አጅሬ) ብሩተስ ምንም እንኳን በውንብድና ቢገለውም፣ ሞቱ የሮም “ወርቃማ-ዘመን” የመጀመርያውን በር ከፍቷል፡፡ የሶቅራጥስ ህልፈት፣ ልክ ዘመነ -ፐርክሊስን ፍፃሜ እንዳረጋገጠው ሁሉ፤ የጁሊየስ ቄሳርም ሞት፣ የሮምን መልሶ ግንባታ መጀመር፣ የኪነጥበብንና የስነፅሁፍን ዳግም ማበብ፤ ያማሩ የውይይትና የመማሪያ መድረኮችን ከሚያማልሉ ቅርፃቅርፆችና ኪነ-ህንፃዎች ጋር ዘመነ-ልደታቸው ተበስሯል፡፡
ፍትሃዊ የነበረውን የሃዳሪያንን እና የአንቶኒነስን አገዛዝ መጢቃነት አሀዱ ብሎ አብስሯል፡፡ የመንገዶች መገንባትን፣ የሕጉን መከለስ እና ሮማን ታሪካዊ ዝና ለማጎናፀፍ የተደረገውን አድካሚ “ዘፀአት” ያስታውሰናል፡፡ በቄሳር ሞት መነሾ ሮም እነዚህን ሁሉ የስልጣኔ በረከቶች በሙሉ ወልዳ ለዓለም አሳቅፋለች፡፡ ቪቫ ቄሳር! ቪቫ ቄሳር!
6.   ልደተ ክርስቶስ - ? ዓ.ም.
ይህን ቀን እርግጠኛ ሆኖ መገመት ያስቸግራል፡፡ በአውሮፓውያንም ሆነ በኢትዮጵያዊያን የዘመን አቆጣጠር መሰረት  ቢሰላ ማንም  እርግጠኛውን ቀን ሊነግረን አይደፍርም፡፡ (በሉቃስ ወንጌል የመጀመርያው ምዕራፍ እስከ ቁጥር አምስት ድረስ) ይህ ቀን ለመላው ክርስትያናትም ሆነ ምዕራባውያኑ እጅጉን የላቀ ዕለት ነው፡፡ ታላቁን ጀግናቸውን እና አርአያቸውን፣ በተለይም “ጌታችን መድሃኒታችን” የሚሉትን መሲህ ያገኙበት ቀን ነው፡፡
በተዓምራትና በአፈ-ታሪክ፣ በወንገልም እንደሚወሳው ከስነ-መለኮት ወደ “ስንነት” ተቀይሮ፣ ዘመኑ የክርስትናን ኃይማኖት መጀመር አብስሯል፡፡ እስከ 21ኛው መቶ ክፍለ-ዘመንም ሆነ ከኛ በኋላ በሚመጡት ትውልዶችም ጭምር በርሕራሔም ሆነ በጭካኔ የክርስቶስን ስም እየጠሩ ነው የየራሳቸውን ቀኖናና ጉባኤ አደራጅተው ገና ይሰብካሉ፡፡ 
7.   የነብዩ ሞሐመድ ዜና እረፍት - 632 እ.አ.አ.
ከሂጅራ ጉዞአስር አመታት በኋላ፣ ነብዩ ሞሐመድ ከዚህ ዓለም አፀደ-ህይወት አለፉ፡፡ የእስልምናን ኃይማኖት በሰሜን አፍሪካ፤ ከካይሮ እስከ ሞሮኮ፣ በደቡብ አውሮፓም፤ ከቱርክ እስከ እስፔን፣ በግማሹ የእስያ አህጉርም፣ ከየሩሳሌም እስከ ባግዳድ እና ቴህራን፣ እንዲሁም እስከ ኒውደልሂ አስፋፍተው አይቀየሬውን ጉዞ ነጎዱ፡፡ ኃይማኖትን ለማስፋፋት ሲል “ቅዱስ ጦርነትን” የሚያጧጡፍ አንድም እምነት የለም፡፡
እስልምና ከጃሃዳዊ አቅሙ በተጨማሪ፤ እጅግ ክቡር እና ብርቅ የሆኑ እሴቶችን ሰብስቧል፡፡ በአንድ አላህ ብቻ በማመንን፣ ምንም አይነት አምልኮተ-ምስልንም ሆነ የሰማዕታት አማላጅነት ባለመቀበሉ፤ በላቀ ወታደራዊና የኃይማኖት ተጋዳይነት የሚሰለፉ ተከታዮችን (ሙጃሂዲንን) በማሰልጠን ችሎታው፣ በካርዲቫ፣ በግራናዳ፣ በካይሮና በደልሂ የላቁ የባህልና የኃይማኖት ማስተማርያ ማዕከሎችን (ዩኒቨርስቲዎችን) አቋቁሟል፡፡ አሳድጓል፡፡ በዓለማችን ከፍተኛ ሥልጣንን ተቆናጦ የነበረው ህንዳዊው አክባርን አንግሶ፣ ከስፔን እስከ ፍልስጤም እና ግብፅ የተንሰራፋውን እስላማዊ ክብርና ዝና ተቀናጅቶ ነበር፡፡ ከአክናባህር እስከ ታጅማል ያሉትን ግዙፍ ህንፃዎች ግንባታ ጀምረው፣ እንደወርቅ አንጣሪ ለብጠውና ከሽነው ያጠናቅቁታል፡፡
ምንም እንኳን ዛሬ፣ በተለያዩ ሀገራትና የፖለቲካ ሊጎች ውስጥ ተከፋፍለውና ተቃቅረው የማይግባቡ ቢመስሉም ቅሉ፣ በእያንዳንዱ ቀን በቻይናና በህንድ እንኳን ሳይቀር በርካታ ምዕመናንን ወደ ኃይማኖቱ ተከታይነት በመቀየር ተግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ በዚህ አካሄዳቸውም ከገፉበት፣ የወደፊቷ ዓለማችን በእስልምና ሃያል ተጽዕኖ ስር የማትወድቅበት  ምንም ሰበብ የለም፡፡
8.   የሮጀር ቤከን ሞት ገሥግሦ መጣ - 1294 እ.አ.አ.
ይህ ቀን በመልካም ከሚታወሱትና የመጀመሪያውን የጠመንጃ አረርና ቀለህ መጠቀም የተቻለበት ወቅት ነው፡፡ ያ! አመጸኛና ሞገደኛ (እንግሊዛዊ) መነኩሴ ተቀጣጣይና አቃጣይ የሆነውን ጥይት ፈልስፎ መሞት አይቀርምና ሞተ፡፡ ይህን መነኩሴ አማፂ” የምለው ወድጄን አይደለም ፡፡ በፈጠረው ጥይት ሰበብ፣ የወሊድ ቁጥጥር እንዲደረግ ይጥሩና ይጎተጉቱ የነብሩትን አስተዳዳሪዎች እፎይ ብለዋል፡፡ በአንድ አዳፍኔ ድርግም በማድረግ ከመኖር-ወደ-አለመኖር በሚቀይሩት ርካሽ የጥይት አረሮች አማካኝነት ተተኪ መላ ዘየደ፡፡
ሮጀር ቤከን እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር፤ “ከአንዲት የነሐስ ቀለህ ውስጥ ተወንጭፋ የምትወጣው መብረቃዊት ፍንጣሪ ኢላማዋን በመምታት-አቅሟ፣ ተፈጥሮን ራሱ ታስንቃለች፡፡ ጥቂት የሆኑ ተቀጣጣይ ውህዶችን አደባልቆ፣ የፈካና የሚንቦገቦግ ፍንዳታዊ ብርሃን መፍጠርም ይችላል፡፡ ይህንንም ክስተት በመቶዎችና በሺህዎች እጥፍ በማባዛት የእውቀት-ጥበብ፣ አንድን ክፍለ ጦር ወይንም ከተማ ሳይቀር ማጋየት ይችላል፡፡” እንዳለውም ሆነ፡፡ ተፈፀመ፡፡
በመካከለኛ ዘመን፣ በከተሞቻቸው ቅጥርና በአይበገሬ ግንቦቻቸው (ጀጎሎቻቸው) ታጥረው፣ የጭሰኛውን ላቦት ሲመዘብሩና ሲመጠምጡ የነብሩትን “መዥገር” የመሬት ከብርቴዎች ሁሉ፣ በምትሀታዊ ፈንጂ አማካኝነት ጭቁኖቹ ዶግ-አመድ አደረጓቸው፡፡ እነዚህም ተቀጣጣይ ጠብ-መንዣዎች የኔብጤውን ድሃ-አደግ ህዝብ ለአመጽና ለአብትም አነሳሱት፡፡ የልብ-ልብ ሰጡት፡፡ ጦርነትም፣ ፊትለፊት ተጋጥሞ በጦርና በጎራዴ ከሞሞሻለቅ፣ በሻሞላና ከፋለምና በጨበጣ ከመተላለቅ፣ በአንዲት ቅጽበት በርካቶችን በርቀት ሆኖ አልሞ በመተኮስ ወይም የመጠባበቂውን ቁልፍ ስቦ በመወርወር ብቻ፣ የድሉን ዜናና የጦርነቱን ውሎ ለመቀየር ስለሚያስችል፣ ለብዙ መቶ ሺህ ባለሙያዎች የስራ እድልም ተፈጠረ፡፡ ምናልባትም ደግሞ ሰውን ልጅ ኑሮ ወደ ምድራዊ እንጦሮጦስነት የሚቀይረውን “ጦርነት” የሚሰኘውን “ሰይጣን” ጉልበት ሰጠው፡፡ ሮጀር ቤከንን ባሰብኩት ቁጥር መራራ የሆነ፣ እጅግም ሰቅጣጭ ስሜት ይሰማኛል፡፡ በተለይም ደግሞ ሰውን በዘርና በመልክዓ-ምድር ለይተው ጦርነት በሚባል ሲዖል ውስጥ የሚዶሉት፣ ሰብአዊነት የጎደላቸው ጅሎች እጅ  መግባት ያልነበረበት የአዛዝኤል (መልዓከ-ሰይጣን) የሰው መግደያ የሚሆን የጦር መሳሪያ ለቃየል ልጆች እንደሰጠው ሳስበው ያንገበግበኛል፡፡ “ሮጀር ቤከን የሚባል ሰው ባልተፈጠረ ኖሮ ምን ነበረበት፤” የሚል ቅን መንፈስ ይወዘውዘኛል፡፡ (ግና ምን ያደርጋል! አህ!....)
9.   ዮሐንስ ጉተንበርግ የጋዜጣ ማተሚያ ማሽን ፈጠረ - 1454 እ.አ.አ.
በዚህህትመት ቀንንና ዘመንን ከትቦ ለመጀመሪያ ጊዜ አተመ፡፡ከዲሞክራሲ በስተቀር ምንም ያልተሞከረባት ነገር የለም !” በምትባለው ቻይና በ1041 እ.አ.አ. የማተሚያ ማሽን ተሰርቶ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ በ1900 እ.አ.አ. የተገኘው ሰነድም እንደጠቆመው ከሆነ፤ በግልፅና በጉልህ ፊደላት በ866 እ.አ.አ. የተፃፈ መጽሐፍ ተገኝቷል፡፡ ምንም እንኳን፣ ቻይናውያኑ የማተሚያ ማሽኑን ቀድመው ቢፈለስፉትም፣ ዕለታዊ ጋዜጣን፣ የወንጅል ነክ ልቦለዶችንና ወሲብ-ቀመስ የህይወት  ታሪኮችን ለማሳተም አልተጠቀሙበትም፡፡
የወረቀት ገንዘብን ለማተም በመቻሉና  ብዙ ወርቅንና ብርንም፣ በወረቀት የመገበያያ ገንዘብ መተካቱ፣ የሽፍቶችና የቀሳውስቱ የበላይነት እንዲያከትም  በር-ከፋች ሆነ፡፡ የመፅሐፍ ቅዱስን እንደልብ ለማተም በመቻሉና ሕዝቡም እንደወረደ ለማንበብ በመቻሉ የተሃድሶው (Rennaisance) ፋና እንዲለኮስ አስገዳጅ ሆነ፡፡ ኅትመት ከመነኮሳት ቁጥጥር ስር ወጥቶ፣ “የሰይጣን ስራ” ነው በሚባለው ማተሚያ ማሽን ስር ዋለ፡፡ የተሻለ ቅስቀሳንና የሃሳብ ነፃነትን በመግለፅ፣ ዲሞክራሲያዊ መብት እንዲጎለብት አስችሏል፡፡
10.  ክርስቶፎር ኮሎምበስ አሜረካንን አገኘ - 1492 እ.አ.አ.
ኮሎምበስ አሜሪካንን እንዳገኘ ገደማ፣ የኢጣልያን የህዳሴ ዘመን ማክተሚያ ሆነ፡፡ ምክንያም፣የንግዱ መስመር ከሜድትራንያን ባህር ወደአትላንቲክ ውቂያኖስ በመዞሩ፣ የሀብት አኪሩና ሲሳዩ በመጀመሪያ ወደ ስፔን፣ ከዚያም ወደ እንግሊዝ ተዛውሮ ማርሎውን፣ ሼክስፔርን፣ ሚልተንን፣ ቤከንንና ሆበስን በገንዘብ ደጉሟል፡፡ ወደ ኔዘርላንድም ተሻግሮ ሬምብራንዲትንና ስፒኖንዛን፣ ሩቤንስንና ቫን-ዲክን፣ ሁቤማንና ቬርመርን በጣም ከፍተኛ ዝና አጎናጽፏቸዋል፡፡ ወደ ፈረንሳየም ሄዶ ሩቢያስንና ሞንታኝን፣ ፓውሴይንና ሎሬይንን ታዋቂ አድርጓቸዋል፡፡
1564 እ.አ.አ. ሚካኤል አንጀሎ በሞተበትና ዊሊያም ሼክስፒር በተወለደበት ዘመን ላይ፣ የጣሊያናውያን ህዳሴ የማክተሚያው ደውል ሲደወል፣ በእንግሊዝ “የዳግማዊ ልደቱን” በይፋ አከበረ፡፡ ኪነ-ጥበብና ፍልስፍና ኢጣልያ ውስጥ ሞቶ፣ በሀገረ እንግሊዝ ተወለደ፡፡
ይኸው የኮለምበስ የአሜሪካንን አሰሳ፣ ለአፍሪካ፣ ለኤሲያና ለአውስትራልያ አህጉራትም የአሰሳ ጀብድ መነሳሳት ጥንስሱ ሆነ፡፡ ከ1492 እ.አ.አ. በኋላም ታሪኳና ዝናዋ እየጨመረ የመጣችው አሜሪካን፣ ህዝባዊነትን የተላበሰ የሉዓላዊነትና ህዝባዊ የሆነ የትምህርት ቤተ-ሙከራ ለመሆን በቃች፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፣ “አሜሪካን” የተባለችው ሀገር ልክ እንደ ሆሊውድ ፊልሞቿ፣ በትንግርተኛ ገድሎቿና ገደሎቿም የተሞላች ልትሆን በቃች፡፡ (“ወይ አሜሪካ፣ ሲገኝ በጄሪካ፣ ሲታጣም በማንካ!” ማን ነበር ያለው?......በቃ እኔ ነኝ ተውት፡፡)
11.  የእንፋሎት ሞተር 1769 እ.አ.አ. እና የቴስላ ተፈራራቂ የኤሌክትሪክ ፈረሰኛ ሞገድ 1886 እ.ኤ.አ በተግባር ላይ ዋሉ፡፡
ሀ) ከጀምስ ዋት ቀደም ብሎ፣ በ130 ..ክ. - የአሌክሳንድሪያው (ስሙ ያልታወቀ) ጀግና በእንፋሎት የሚሰራ ሞተር ሰርቶ ነበር፡፡ ዴላ ፓርት፣ ሳቬሪይና ኒውኮመን 16011698 እና 1705 .ኤ.አ. ከጀምስ ዋት የተሻሉ ሞተሮችን ሰርተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን፣ 1769 እ.አ.አ. በጀምስ ዋት የተሰራው ሞተር የኢንዱስትሪውን አብዮት መጀመር ያበሰረና የዓለምን የለውጥ ጉዞ መጀመር የመሰረት ድንጋይ አጽንቷል፡፡
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሁለት መሰረታዊ የአኗኗር ለውጥን ያመጡ አብዮቶች ተከስተዋል ፡፡ አንደኛው፣ የሰው ልጅ ከአደንና ወፍ-ዘራሽ የሆኑ የዕፅዋት ፍሬዎችን ከመመገብ በአንድ መንደር ሰፍሮና አርሶ መኖር የጀመረበት የስልጣኔ ደረጃው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፣ የኢንዱስትሪው አብዮት ነው፡፡ በዚህም የስልጣኔ  ጎዳና ውስጥ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩት በገጠር የእርሻ መሬትን አርሰውና አምርተው ይኖሩ የነበሩ  የእንግሊዝ፣ የአሜሪካን፣ የጀርመን፣ የጣልያን፣ የፈረንሳይና የጃፓንም ገበሬዎች፣ የቻይናና የህንድ (የኛም አገር ገብሬዎች ሳይቀሩ) ዛሬም ድረስ የእርሻ መሬታቸውን እያሰተወ፣ ቀያቸውን አስጥሎ ወደ ከተሞችና በቅናሽ ጉልበታቸውን ወደሚሸቅጡባቸው ፋብሪካዎች እያንከወከወ አምጥቷቸዋል፡፡
ይኼው ጉደኛ የእንፋሎት ሞተር በቀደደው ጎዳና ላይ፣ መንግስታትንም ሕዝቡን ለመቆጣጠር በመሬት ይዞታና በወታደራዊ ጉልበት ብቻ ሳይሆን፣ የትልልቅ ማምረቻ ማሽኖችና የንግድ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በበላይነት  እንዲይዙ አስገድዷል፡፡ በሃይማኖትም ረገድ፣ ብዙ ሰዎች በሚሰበኩበት መጪው ዓለምና መንግስተ-ሰማያትን ተስፋ በማድረግ “ብቻ” ሳይሆን፣ በነገሮች ምክንያት እና ውጤት ላይ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማሰብ እንዲችሉ አስገድዷቸዋል፡፡ የሴቶችም የስራ መስክ በቤት ውስጥ ብቻ ከመወሰን አልፎ ተርፎ፣ ፋብሪካዎች ውስጥ እንዲገቡ በመፈቀዱ፣ ግብረገብነትን በቁሳዊ ህይወት በመተካቱ፣ ጋብቻና ወሊድም በማዘግየቱ፣ የስራ ባልደረቦችን ቁጥር በመጨመር አጋጣሚነቱ፣ ሴቷን ከቤት-እመቤትነት “ነፃ” በማውጣቱ፣ ኃይማኖትንና ቤተሰባዊ ሥልጣንን በማዳከም ቀላል ለውጥ አላመጣም፡፡ ምን ይህ ብቻ፤ ኪነ ጥበብ ለጥቂቶች ብቻ መደሰቻና መደመሚያ ከመሆን አልፋና-ተርፋ ወደ “ብዙኃኑ የአድናቆትና የግል አተያይ ዘይቤነት” ተቀይራለች፡፡
ከፖለቲካ ስርአቶችም ውስጥ “የካፒታሊዝም፣ የሶሻሊዝም እና የኢምፔርያሊዝም” ስርዓቶች ምንጫቸው የጀምስ ዋት እንፍርፍሪት ነው፡፡ በኢንደስትሪ እየለሙ የነበሩት አገሮች የውጭ ገበያና ምግብ ሲፈልጉ፣ እነዚህንም ለማግኘት ሲሉ ጦርነት ሲከፍቱ፣ በጦርነት የተሰላቹትም የተወራሪ አገር ሕዝቦችም ሲያምፁ፣ አመፃቸውም ወደ ካፒታሊስትነት፣ ወደ ሶሻሊስትነትና ቀኝ-ገዢነት ጎራ ለውጧቸዋል፡፡ የታላላቆቹ ጦርነቶች፣ የፈረንሳይና የሩስያም አብዮቶች ዘመነኛ አስተሳሰቦች መነሻቸው 1769 እ.አ.አ ነው፡፡
ለ) የኒኮላ ቴስላን ያህል፣ ዓለምን በብርሃናዊ ፈጠራዎችና ግኝቶች ያንቦገቦገ ሰው ማን አለ? “ሊካ” በተባለች የኦስትሪያና የኃንጋሪ ድንበር ከተማ የተወለደው ይህ ሳይንቲስት፣ የሰው ልጆችን ኑሮና የዓለምን እጣ-ፈንታ ለመቀየር ከ700 (እደግመዋለሁ፣ ከሰባት መቶ በላይ) የፈጠራ ግኝቶቹን አስመዝግቧል፡፡ ከጄኔሬተር እስከ ፍሎረሰንት፣ ከሬዲዮ እስከ ቴሌቪዥን፣ ከባለገመድ ስልኮች እስከ ገመድ አልባ የፈጠራ ውጤቶች (የሞባይል ስልኮችን ጭምር) ከ1900 እ.አ.አ. በፊት ባለሉት 15 አመታት ጊዜ ውስጥ አሳክቷል፡፡ የመርከብ፣ የአውሮፕላን፣ የመኪናና የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በሞላ ፈጣሪያቸው ማንነው ቢባል ቴስላ ነው፡፡ በፊዚክስ የዶክትሬት ዲግሪውን በቪዬና ዩኒቨርሲቲ አጠናቆ፣ የፈጠራ ስራዎቹን በፓሪስና በኒው-ዮርክ፣ እንዲሁም በኮሎራዶ አከናውኗል፡፡
የኒያግራ ፏፏቴ ላይ የተሰራውን የኃይድሮ-ኤሌክትሪክ መመንጫ በ1890ዎቹ ሰርቶ ሲያጠናቅቅ፣ ከቶማስ ኤዲሰን የተሻለ ተፈራራቂ የኤሌክትሪክ ፈረሰኛ ሞገድ (Alternative Current) ፈጣሪ ስለሆነ ነው፡፡ መቼም ቢሆን፣ የኒኮላ ቴስላን ወኔና ቁርጠኝነት ያለው፣ የዓለምንና የሰውን ልጅ መፃዔ ዕድል በአዎንታዊ ጎኑ የቀየረ የፈጠራ ባለሙያ እንዳልነበረ ማወቁ ነፍስን ሰማየ-ሰማያት እንድተመጥቅ የደርጋታል፡፡ ኧረ ምኑ ተነካና! (ስለቴስላ ዝርዝር መረጃ ልታገኙ ብትወዱ፣ www.tesla.hu የተሰኘውን ድረ-ገፅ ይጎብኙ!)   

12.  የፈረንሳይ አብዮት አብጦ-አብጦ ፈነዳ - 1789 እ.ኤ.አ.
ምናልባትም ማበጥ የጀመረው ኮፐርኒከስ በ1543 እ.አ.አ. “On The Revolution of The Celestial Orbs” የተባለውን መፅሐፉን ካሳተመ በኋላ ነው፡፡ ለሁለት መቶ ሠላሳ አምስት አመታት ያህል የተቋጠረው የአመፅ ብጉንጅ  “አመፅ” ሆኖ ማዠት ጀመረ፡፡ ደምና ሞትን ምሱ ያደረገ፡፡ “አብዮት” የሚባለው ብጉንጅ ፈርጦ፤ ፈረንሳውያንን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በስነልቦናም ፈርጆች ሁሉ የሚያም ሥርዓት አልበኝነት ሰፈነ፡፡
የአብዮትነት ቅርፅም መያዝ ሲጀምር፣ “ፈጣሪ የለም!” “እናት ሃገር ወይም ሞት!” “ያለምንም ደም ፈረንሳይ ትቅደም!” ምናምን የሚሉ መፈክሮች መደመጥ ጀመሩ፡፡ (እኛም አገር መጥተው የነበሩት ኮሚኒስቶች ላይ አድሮ የነበረው አጋንንት፣ የፈረንሳይ አብዮተኞች ላይ ሰይጥኖ ነበር፡፡ በፈረንይ አምላክ ላይ የጠለቀችው ጀንበር፣ ፈረንሳያውያን ሰብዓዊ እሴቶቻቸውን እንዲያደንቁ አስገደዱአቸው፡፡ ወሲብ፣ ልብወለድና ስነ-ጥበብ በፈረንሳይ ውስጥ የሰው ልጅ እሴቶች ማሳያ ሆነ፡፡ የፈረንሳይን ከተሞች የባህላዊ አብዮቶች ማዕከላት አደረጋቸው፡፡
በዚህ ምድር ሰው ሲኖር፣ ሰብዓዊነቱ የሚገለጸው በስነሕይውት (Biology) ሆነ፡፡ ስነሕይወቱም የሚገለፀው በሰነምድር (Geology) ሆነ፡፡ ማለትም፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በእሳተ-ገሞራ፣ በሱናሚ፣ በአውሎ-ነፋስ……በቶርኒዶ፣ ወዘተርፈ፤ መሆኑ ታወቀ፡፡ ምድርና በከርሰ-ምድሯ የደበቀቻቸውም ነገሮች የሚገለፁጽ በስነ-ፈለክ (Astronomy) ስለሆነ፣ የሰው ልጅ የማያየውን ፈጣሪ ማሰብ ትቶ፣ ሰው ስለራሱ ተፈጥሮና ምንትነት ማሰብ ጀመረ፡፡ ያለገደብ ማሰብና መደነቅም ቀጠለ፡፡ እንደልቡም፣ ፈጣሪን ሣይቀር መኮነን ተጀመረ፡፡
ለዚህ ማሳያ የሚሆኑትን ሁለት ፈረንሳያውያን ልጥቀስ፡፡ ባለቅኔው ቮልቴር እንዲህ አለ፤ “በትረ አሮን ባይኖረኝ፣ ዘውድስ ባልጭን-ምን ቸገረኝ፤ ብዕር አለኝና ማነው የሚመክተኝ!” ሲል ተቀኘ፡፡ ፈላስፋው ሩሶም፣ “አሁን እኮ እኔ ያለሁት፣ አለሁኝ ብዬ ስላሰብኩ ነው!” ሲል በነፃ መንፈስ ተፈላሰፈ፡፡ እነዚህ ሁለት ሊቃውንት ልበ-ብርሃንነት (Enlightment) የተባለ የፍልስፍናን ስልት አስተዋውቀው፣ ከፐርክሊሳውዋ ግሪክና ከአውግስቶሳዊቷ ሮማ የሊቃውንት እንቅስቃሴ ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ምሁራዊ እድገትን ጀመሩ፡፡ ምሁራንም በወኜ መናገር፣ በግልፅ ቋንቋ መፃፍና መተቸት ጀመሩ፡፡ ታላቅ የባህልና የአካዳሚክስ ዘመቻ ተካሄደ፡፡
በአንድ ቤተ መቅደስ ውስጥ በቁም እስረኝነተ የጠበቅ የነበረው ሊዊስ 16ኛ፣ በታሰረባት ክፍል ውስጥ የተደረደሩትን የ ቮልቴርና የሩሶ መጽሐፍት አንብቦ ሲጨርስ፣ መጽሐፍቱን እያየ፤ “ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ! እነዚህ ሰዎች ናቸው ለካ ፈረንሳይን ድራሽዋን ያጠፏት!” ሲል ተቆጭቷል፡፡ ልክ ነበረ ሊዊስ፡፡ የጥንታዊቷን ፈረንሳይን ዐይነ-ስብ አጥፍተው፣ በአብዮት ላይ የቆመችው ፈረንሳይ በ1789 እ.አ.አ ተቋቋመች፡፡ ናፖሊዮን የተባለውንም ጀግናዋ በአብዮቱ ማግስት አገኘች፡፡ ቪክቶር ሁጎንና አሌክሳነደር ዱማስ የተባሉት ፀሐፊዎችዋም የአመናቸውን ጣጣ-ፈንጣጣ ለማጋለጥ ጥሰው ወጡ፡፡ 
በፈረንሳይ ሕዝብ ድል መነሻነት፤ የእነዋሺንግተን፣ የነፍራንክሊንና የነጄፈርሰን ልብና ዓይን ብልጥጥ ብሎ ተከፍቶ፣ አሜሪካን ከእንግሊዝ ቅኝ-ግዛት ነፃ ወጣች፡፡ የፈረንሳይ አብዮትና የሕዝባዊውንም አመፅ-ዜና ከሩስያ እስከ አርጀንቲና፣ ከቻይና እስከ ኢራቅና ኢራን፣ ከፔሩ እስከ ኢትዮጵያ ተሸጋግሮ እንደቋያ እሳት የሚፈጀውን ፈጅቶ፣ የሚያቃጥለውን አቃጥሎ በላ-ቀረጠፈ፡፡ አብዮትን በቀሪዎቹ የዓለማችን ክፍሎች ያሰረፁት የቮልቴርና የሩሶ መናፍስት ናቸው ብንልስ? (ማን ከልክሎን፡፡)
13.  የአድዋ ድል እና የጥቁር ህዝቦች ተጋድሎ ዜና - 1888 ዓ.ም.
የአድዋ ጦርነት በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ከተከናወኑት ጦርነቶች ከፍተኛውን ስፍራ የያዘ ነው፡፡ አኒባል የአልፕን ተራሮች ዞሮ የአውሮፓን ኃያል መንግስት ካሸነፈ ወዲህ፣ አንድ አውሮፓዊ ጦር በአፍሪካውያን ሲሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ ጦርነቱ የስልጡኗ አውሮፓ እና የኋላ ቀሯ አፍሪካ ጦርነት ከመሆን ይልቅ “የዘር ታፔላ” ተለጥፎበት፣ የጥቁሮችና የነጮች ፍልሚያ አድርገው ያራገቡትም ጉዶች አልጠፋም ነበር፡፡ ለገሚሶቹ ደግሞ፣ የካቶሊካዊቷ ሮማና የኦርቶዶክሳዊቷ ኢትዮጵያ ፍልሚያ አድርገው አስበውታል፡፡ በተለይም ከአርባ አመታት በኋላ የሮማው ሊቃነ-ጳጳስ የፋሺስቱን ጦር በሮማ አደባባይ ላይ ተገኝቶ ባርኮ ላከ፡፡ (ፖለቲከኛን ጳጳስም ሆነ ኢማም አንተ ብዬ ነው የምጠራው፡፡) ጦርነቱ የአራደውን ጊዮርጊስ ታቦት ተሸክመው የዘመቱት ኦርቶዶክሳዊያንና በሊቀ-ጳጳሱ የተባረኩት ኮተሊኮች ጦርነት ሆነ፡፡
ጦርነቱ ግን፣ በኢንደስትሪ አብዮት እየተጥለቀለቁና ከውስጣዊ አመፃዎችና ትኩሳቶቻቸው እፎይ ለማለት ሲሉ፤ የውጭ ገበያ እና የጥሬ እቃ፣ እንዲሁም የርካሽ ጉልበት እና የቅኝ ግዛት መስፋፋትንም በዋነኛነት አጀንዳው ያደረገው “ስልጡን ነኝ” ባዩ ጥልያን ኢምፔሪያሊስታዊ እቅዱን ነደፈ፡፡ ጦርነቱንም ባሸናፊነት እንደሚወጣ ቅንጣት ያህል እንኳን ጥርጣሬ አልነበረውም፡፡ አውሮፓዊውን ጦር በትጥቅም ሆነ በስልጠና ሊስተካከል የሚችል እንኳን አፍሪካዊ ጦር ይቅርና፤ ምንም አይነት የደቡብ አሜሪካ፣ የእሲያና የአውስትራሊያም ጦር ኃይል አልነበረም፡፡ ምናልባትም፣ አንድም አህጉር ላይ ጠንክሮ የሚመክት ተዋጊ ሃይልም ሆነ መንግስት አልነበረምና፣ ከቅኝ-ግዛት ዘመቻቸው በፊት በኃይማኖት ስም በገቡ “ሰባኪ” ሰላዮች አማካኝነት በተጠናው ሃገርና ህዝብ ላይ በቀላሉ አስተዳደራቸውን እንደቆዳ ይገደግዱት ነበር፡፡ በዚሁ ቀቢጸ-ተስፋም የተነሳሳው የኢጣልያ ጦር በርካታ ቀሳውስቱን (እነ አባ ማስያስን) ልኮ ከሰለለ በኋላ፣ ድሉን በወታደራዊ መስክም ለማረጋገጥ ቆርጦ ተነሳ፡፡
በአንፃሩ - ጓንዴ፣ ውጅግራና ሰኔኔ የመሳሰሉትን ኋላቀር መሳርያዎች የታጠቀው የአፍሪካ ጦርም፣ መካናይዝድ ከሆነው አውሮፓዊ ጦር ጋር ጦርነት ገጠመ፡፡ በጦርነቱ በወኔና በቁጣ ከተነሳሳው የአፍሪካ ጦር ጋር ሲነፃፀር አላማውና ግቡ “ኢምንት የሆነው” ወራሪ ኃይልም ተንኮታኮተ፡፡ ዜናውም፣ በቅኝ ግዛትና በባርነት ጥላ ስር ለነበሩት ከደቡብ አሜሪካ እስከ አላስካና ደቡባዊ አፍሪካ፣ ከናይጄሪያ እስከ አውስትራልያና እስያ ያሉትን ቅኝ ህዝቦች ሁሉ ለሰብዓዊ ክብራቸውና ለነፃነታቸው እንዲታገሉ የአዋጅ አንቢልታውን ከአድዋ ተራሮች ላይ ነፍቶት ኖሮ አድማሳትን ተሻግሮ አስተጋባ፡፡ አድዋም የመላው ህዝቦች የ“ነፃነት ፋና” የበራባት፣ የሰብዓዊ እኩልነትና የዘር በድሎ ቀንበር የተሰበረባት፣ ዳር እስከዳርም ድሉ የተሰበከባት ደጀሰላም ሆነች፡፡ የጥቁር ሕዝብ የዜማ፣ የግጥም፣ የስዕልና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ማጠንጠኛ የሆነ እንደአድዋ ማን አለ? ነፍስ ሔር ለክቡር እመ ክቡራት - ሰማዕታት!
14.  የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ - 1945 እ.ኤ.እ.
የአቶሚክ ኃይል በሄሮሺማና ናጋሳኪ ላይ በግፍ የተሞከረበት ዘመን ነው፡፡ የአንድ አምባገነናዊ ግለሰብና የአንድ ፓርቲ የበላይነቱ መዘዝ በጉልህ የተረጋገጠበትና አውሮፓና አሜሪካ ወደ መድብለ-ፓርቲ ስርዓት የተሸጋገሩበት ወቅት ነው፡፡ በጀርመን፣ በጣልያን በጃፓን ያሉ ገዢዎች እና  አምባገነኖቻቸው መላውን ሥልጣን በቁጥጥራቸው ስር ሰብስበው፣ ለጥፋት እና ለእልቂት ዳግመኛ ሊጠቀሙበት እንደማይገባ በጉልህ ያስተማረ ሆኖ አለፈ፡
ፅዮናዊት እስራኤልም እንደሉዓላዊ መንግስትና ሃገር እውቅናና ሕዝብ አገኘች፡፡ እነዚያ አሳረኛ ፍልስጤማውያንም መሬታቸውን የተነጠቁበት፤ ኩርዶችም መንግስትና ሃገር ፍለጋ የትጥቅ ትግል የጀመሩት ከዚህ ጦርነት በኋላ ነው፡፡ “የራስን እድል በራስ መወሰን” (Self-Determination) የሚለው ስታሊናዊ አስተምህሮት በገቢር የታየበትና፣ የቫስክ ሕዝቦች ከስፔን፣  የዩጎዝላቪያ የቀድሞ ግዛቶች እነቦሲኒያ፣ ሰርቭና ክሮሺያም ነፃ ለመውጣት የሽምቅ ውጊያ የጀመሩበት ዘመን ሆነ፡፡ ከኤርትራ እስከ ካሽሚር፣ ከቆጵሮስ እስከ ኮሪያና ቬትናም ድረስ ገፍቶ የዘለቀ የርዕዮተ-አለም ትግል ተካሂዷል፡፡ የግራ ክንፍ ደጋፊዎች የነፃነት ትግል ነው ያሉትን ሁሉ በጅምላ የሚደግፉበትና የሚያስታጥቁበት ዘመን ከዚህ ጦርነት በኋላ የተለመደ ሆነ፡፡
በሳይንስ እና ቴክኖሎጂም ረገድ - ከአቶሚክ ቦንብ ወደ ኒውክለር ኃይል፣ ከአውቶማቲክ ጠብ-መንዣ ወደ ዲጂታል እና ሱፐር-ዲጂታል የጦር መሳሪያ ባለቤትነት ሃገሮች ተሸጋገሩ፡፡ ደረጃ በደረጃም የወታደራዊ መሳርያዎች እድገት ገስግሶ፣ የቀዝቃዛው ጦርነት በምስረቁና በምዕራቡ ወይም በዋርሶ በኔቶና  ደጋፊዎች መካከል ተደረገ፡፡ በአጭሩ ሁለተጋው የአለም ጦርነት የአሜሪካን ደጋፊዎችና የሶቭየት ሕብረት አጋሮች ጎራ ለይተው እንዲፋለሙ ሰበብ ሆነ፡፡  
15.  የኮምፒውተርና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ መፈጠር - 1940-1989 እ.ኤ.አ.
የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ መፈጠር ለሌሎች ብዙ ሺህ ፈጠራዎች ምክንያት ሆኗል፡፡ የኮምፒውተር መፈጠር ለዘመናዊዋ ዓለም የልብ ትርታዋ ነው ተብሎ ቢቆጠር ምን አለበት? ከማዕድ-ቤት እስከ ሲሚንቶ ማቡኪያ ስፍራዎች፣ ከአውሮፕላን ዳሽቦርድ እስከ ግለሰብ ኪስ ውስጥ፣ ከኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እስከ መዋዕለ-ሕፃናት ድረስ ዘልቆ የገባ የፈጠራ ውጤት ካለ አለጥርጥር ኮምፒውተር ነው፡፡
ክላውዲ ሻነን የተባለች አንዲት አሜሪካዊ ሳይንቲስት በ1940 ለመጀመሪያ ግዜ የፕሮግራሚንግ ቋንቋን፣ ኮምፒውተሮች መረዳት እንዲችሉ ለማድረግ ቻለች፡፡ ይህም ድንቅ ፈጠራ ለአውቶማቲክ ፕሮግራሚንግ እና ለግል ኮምፒውተሮች መፈልሰፍ የአቋራጩን በር ከፈቱ፡፡
የኮምፒውተርን አብዮት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ በ1990 እ.ኤ.አ ዓለምአቀፍ የድረ-ገፅ (world wide web or www) ፈጠራ፣ ቲም ባርነስ-ሊ በተባለ ንግሊዛዊ መፈልሰፉ፣ የኮምፒውተርን አብዮት በእጅጉ አግዞታል፡፡ ይህ በአውሮፓ የኒውክሌር ምርምር ማዕከል (በጄኔቫ) ውስጥ በተመራማሪነት ይሰራ የነበረ ለጋስ ሰው ራሱን የቻለ የመረጃ ልውውጥ አብዮትን በግንባር ቀደምትነት ለኮሰ፡፡ ሰውዬው፣ ከዚህ የዓለምን - የእውቀት፣ የባሕል፣ የማሕበራዊ-ኤኮኖሚ፣ የመረጃ ማስተላለፊያና የመዝናኛውን ዘርፍ ከአፅናፍ-እስከ-አስፅናፍ፣ ድንበርና ርቀት ሳይመክተው መገናኝትና ማገናኘት የሚያስችል ተዓምራዊ ፈጠራቸውን ቤሳ-ቤስቲን እንኳ ሳያገኝበት ለሰው ልጆች በገፀ-በረከትነት ለገሰ፡፡
የፈጠራ መብትን ለማስከበር ሲባል በሚደረገው ጨረታ፣ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ በነጋዴዎች እጅ ገብቶ የሰው ልጅ መረጃ ለማግኘት ሲል ውድ ዋጋ እንዳይከፍል አስቦ የሚያስመሰግነው ሰብአዊ አድራጎት ፈፀመ፡፡ የኢንተርኔት መፈጠር፣ አዲስ ባህልና የዓለም ስርዓትን (New- Order) በነፃ፣ በፈጣንና በጅምላ ለሁሉም የሰው ዘር ለማድረስና ለማዳረስ የተፈጠረ “አንድ-አርጌ” “እኩል-አርጌ” ሆነ፡፡ ወይም ነው፡፡ ይህንን ተልዕኮውን ምን ሊያስቆመው ይችላል? ምንም፡፡ ኧረ ምንም ነገር ፈፅሞ አይገታውም፡፡ መንግስታት እንኳ እሬት-እሬት እያላቸው የአለም-አቀፉን ድረ-ገፆች ከመጠቀምና አፈናቸውን ዲጂታላዊ ከማድረግ ወደኋላ አላሉም፡፡
                 ************************************************
እንግዲህ ዓለማችንን በፈጣን ሁኔታ ወደላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ ታሪካዊ ቀናት እነዚህ ናቸው፡፡ ከአዘጋጁ፤እርስዎም (አንባቢ) ዓለምን የቀየሩ ክስተቶች እና ፈጠራዎች ለብሎጋችን ቢልኩልን ወይም በሌሎች ድረ-ገፆችም ላይ ቢያወጡ፣ ሃሳብዎትን የምናስተናግድ መሆናችንን በአክብሮት እንገልፃለን፡፡

አስተያየቶች

  1. First i would like to thanks you since we gain sufficient info from your blog.
    Next; please keep it up what you you take more infos about Ethiopian and world and i promised you to read your blog what call it Semnaworek.blog.SPOT

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

አስተያየት ይለጥፉ

Thanks a lot for your comments.