ታሪክ ያላነበቡ ታሪክ ሰሪዎችና፣ ታሪክ ያላነበቡት ታሪክ ዘካሪዎች፣ ጉድ አፈሉብን!

(ለፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም በተለይ)

                 (ሰሎሞን ተሰማ ጂ.) (ከአ.አ)              semnaworeq.blogspot.com


0. መግቢያ

ፍሬድርክ ቼ በደስታና በፈንጠዝያ የምፎልሉትን እንሰሳት ተጠጋና ጠየቃቸው። "ለምንድነው እንደዚህ  ደስተኛ ልትሆኑ የቻላችሁት?" የሚል ነበር ጥያቄው። እነሱም ባንድነት፣ ባንድ ቃል መለሱለት። ምንም ሳይወያዩ፣ ምንም ነገር ሳይፎካከሩ፣ መንፍሳቸውም ሳይቀናና፣ አንዱም ሌላውን    ሳይተች፣ ደመ-ነሳቸው በሚነግራቸው መሰረት፣   "ምንም ታሪክ (memory of things) ስለሌለን ነዋ!" አሉት። ከአፍታ በሁዋላ "ምን አላችሁኝ? እስኪ ድገሙልኝ?" ሲል ጥያቄዎቹን አጅጎደጎደባቸው። እነሱ ግን የሰጡት መልስ አጭርና አስገራሚ ነበር። "ምኑን ነው የምንደግምልህ?" የሚልና  ክው አድርጎ የሚያስቀር መልስ።  ሁሌም የሚደንቀኝ አይነት፣ "ቅስም-ሰባሪ" መልስ ይሉዋችሁዋል እንዲህ  ያለው ነው-እንጂ! ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
                                                                   ****** 
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ወይም በግል አጠራሬ "ጋሼ  መስፍን" ባለፈው አርብ ሚያዝያ 26 ቀን 2004 ዓ/ም በወጣው የፍትህ ጋዜጣ ላይ "በፍትሕ ጋዜጣ ላይ ለምንጽፍ ሁሉ እየተናገሩ አለማነጋገር፣ እያሰቡ አለማሳሰብ"፣ በሚል ርዕስ ሥር ያሰፈረውን ጣጥፍ አነበብኩት።  ሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነበር የፅሁፉ ትኩረት። አንደኛ፣ ሀሳብን በጋዜጣ ወደ አደባባይ ስለማውጣት ሲሆን፤ የሁለተኛው ጉዳይ  መሪ  ሃሳብ ደግሞ፣  "ሳይነጋገሩ የመናገሩ ፈሊጥ የሚታየው በባለስልጣኖችና በተቺዎቻቸው መሀከል ብቻ አይደለም፤ በተቺዎቹም መሀከል ነው፤ ተቺዎቹም መናገሩን እንጂ 'እርስ-በርሳቸው' መነጋገሩን ገና አለመዱትም፤" ይልና፣  በሦስተኛነትም፣   "በእኩልነት ደረጃ ሆነን ለመነጋገርና ለመከራከር" የሚያቅተን፤ "በየፊናችን ስንናገር ራሳችንን ከላይ አውጥተን ሰሚውን ከታች አድርገን መደመጥን እንጂ እኛም  በተራችን ሌሎችን ማድመጥ እንዳለብን" ያለማወቃችንን   ባህላዊ አዚም አንስቶ  የገለፃቸው ነጥቦች ትክክለኛነት እቀበላለሁ። በኔ አስተያየት የቀሩ ሌሎችም ነጥቦች አሉና ላካትታቸው ወደድኩ።
1ኛ. ታሪክ፣ አእምሮና ስሜት (የፖለቲካ ልፈፋ)

በመጀምሪያም  "ፍትህ ጋዜጣ"ም ላይ ሆነ ሌሎች ጋዜጦች እንዲሁም ድረ-ገፆች ላይ  ስለታሪካዊ ኩነቶች ለመፃፍ ስለሚሞክሩት አምደኞች እርስ-በርስ ያለመናበብ ሁኔታ ምጠነኛ መግቢያ ልስጥ።  ዩሪፒደስ የተባለው የጥንት የግሪክ ታዋቂ  ገጣሚ፣  "ታሪክን ጠንቅቆ ያነበበ እርሱ የተመሰገነ ነው፣"  ይላል። ገጣሚው ሆን በሎ  የሸሸገው ቃል ግን አለ። የሄውም "ዕድል" የሚለውን ቃል ነው። ዕድል የሚለው ቃል ድንገተኛ ከሆነ ጣልቃ-ገብ ነገር (ወይም ሳይታሰብ በመካከል ተከስቶ ከሚፈፀም ድርጊት ጋር በቅርብ የተያያዘ ኃይል ነው (ለዚያዉም 'ኃይል' ከተባለ)። ማለትም፣ ዕድል ለሰው ዓላማ እንግዳ የሆነ ነገር ነው። ስለዚህ፣ በዕድለኝነት በአዎንታም ሆነ በአሉታ  የሚገኝ ወይም የሚደርስ ሁሉ፣ እርሱ ታሪክን የማተት የዋጋ ድልድል የለውም። እንኩዋን ታሪክን የሚያህል ግዙፍ ቁምነገር ሊፅፍ  ይቅርና ሲያነብም ቢሆን መጠንቀቅ እንዳለበት ዩሪፒደስ ይመክራል። (በዚህ ዙሪያ በየጋዜጣው ላይ የምፅፉትም ሆኑ የሚዘፍኑት "ጎበዛዝት" እና "ቆነጃጅት"  ምስጉን ያልሆነ ስሕተት ሲሰሩ ይታያሉ። በቅርቡ አንዱ ጉምቱ የወያኔ ሹም (ብትፈልጉም "ጎበዝ"  ወይም የጎበዝ አለቃ  በሉት)፣ ስለአክሱም የፈጠሩት ውጅምብርም  ሆነ፣ ዘፋኙ ስለ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአድዋ ድልና ስለ ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው እንዲሁም ስለ ራስ አባተ ቧያለው አባ ይትረፍ የተፈፀሙት የታሪክ ግድፈቶች በሙሉ፣ ታሪክን ጠንቅቆ ካለማንበብና፣ እውቀት ከስልጣን ጋር ወይም ከዝናና ከገንዘብ ጋር የሚገኝ፣ የጠቢቡ ንጉስ ሰሎሞን ወልደ ዳዊት- "አምሳል ነኝ"- ብሎ ከመገበዝ የሚመነጭ ነው።)

ዩሪፕደስ፣ ሆን ብሎ ነው ዕድል የሚለውን ቃል ያልተጠቀመው። በዚያ ፈንታ "መመስገን" የሚለውን ማሰሪያ አንቀፅ አድርጎታል። ቃሉም ከሁዋላው አንድ ዘይቤን ያዘለ ነው። ምስጋና ተከታይ ወይም ፍፃሜ እንጂ መነሻ አይደለም። ስለዚህ ከፍፃሜው በፊት አንድ መነሻ ነገር መኖር አለበት። ያም 'ተግባር' ነው። ሰው የሚመሰገነው፣ የሚገባውን ተግባር በጊዜው የፈፀመ እንደሆነ ነው። ሰው ማህበራዊ ፍጡር ነውና፣ በመሰሎቹ መካከል ሲኖር፣ ከሌሎች የሚጠይቀው መብት ሲኖረው፣ ሌሎችም ከእርሱ የሚጠብቁበት ግዴታ አለ። መብቱን ሲጠይቅ ብቻ ሳይሆን፣ ከርሱም የሚጠበቅበትን ግዴታም ሲፈፅም፣ ያንግዜ ከሌሎች ሰዎች ዘንድ መሰጋናን ያገኛል። መስጋና ሲባልም ራሱን የቻለ ቃል እንጂ የሙግሳ፣ የዉዳሴ ወይም የማንቆለጳፐስ ጥገኛ አይደለም።

የምስጋና መሰረቱ አእምሮ ነው። የዉዳሴና የሙገሳም መሰረቱ ስሜት ነው። አእምሮ መቼም ቢሆን ካላወጣ፣ ካላወረደና ካላመዛዘነ ውሳኔውን አይሰጥም። ስሜት ግን ማውጣትና ማውረድ፣ ማሰላሰልና ማመዛዘን ሲያልፍም አይነካካው። ስሜቱን ለነካውና ለቀሰቀሰው ነገር ከመቅፅበት ሙገሳውን ያጅጎደጉዳል። (ሙገሳውም "ውዳሴ-ከንቱ" የሚባለው አይነት ነው።) በመሰረቱ አእምሮ የሚሳሳትበት እድሉ በእጅጉ አናሳ ነው። ሁለት ነገሮች አእምሮን ወደ ስህተት ይመሩታል፤ አንደኛው ከእውቀት ማነስ የሚመጣ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አእምሮን ስሜት ሲጫነውና ስሜትም የአእምሮ የበላይ አዛዥና-ናዛዥ ሲሆን ነው። በነዚህ በሁለቱም  ምክንያቶች "እየተናገሩም አለማነጋገር፣ እያሰቡም አለማሳሰብ" አይቀሬ ይሆናል። ተነጋግሮም ሆነ በጋዜጣና በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ላይ ትርፋማ የሆነ ውይይት ማካሄድ ያንጊዜ ይከብዳል።

ዛሬ ላይ የመንግሥትንም ሆነ የግሉን ጋዜጠኞች የታሪክ፣ ፣ የፖለቲካና የሌሎችም ዲስፕልኖች/ ማለትም የአእምሮ ማመዛዘኛ ዘርፎችን በወጉ አለመረዳት ችግር ሰለሚንፀባረቅ፣ በተለይም በመንግሥታዊው አመቃና አሸማቃቂ ሳንሱር  ሰበብ፣ ጋሽ መስፍን (አንተም) እንዳልከው፣ "በማስፈራራት የተካኑ ሎሌዎች"ና የለት ጉርሳቸዉን የሚቀላውጡ ጎበዞች ስለሚዝቱና ሰለሚያሳድዱም ጭምር፣ እንኩዋን የታሪክን ሁንኛ አውድ አውጥተውና አውርደው ሊፅፉ ቀርቶ፣ እንኩዋን አመዛዝነውና አሰላስለው ሊመረምሩ ቀርቶ፣ የሚፅፉትንም "አሸባሪ" እያሰኘ፣ ዘብጥያ ሊያወርዳቸው ስለሚችል (ስለቻለም ጭምር) ፣ ገሚሱንም አስደንብሮ ወይ በባሌ ወይ በቦሌ ሲያስምርሻቸው እየታየና፣ የሳምንትና የወራት እድሜ የቀራቸውም ቢሆኑ በየፍርድ ቤቱ ደጃፍ እየተጉላሉ ለሚያይ አእምሮ፣ የፍርሃት ስሜት ኮርኩዶና ቀፍድዶ ቢይዘው፣ ጥፋቱን  ያንድ ወገን ብቻ አድርጎ ማሰቡም ሆነ ማሰላሰሉ ይከብደኛል። እረ እንዲያውም ያሳምመኛል። 

ለዚህ ታዲያ ዋነኛው ተጠያቂ የእውቀት እጥረትና የአእምሮ በስሜት ጫና ስር ማጎብደድ መሆኑን ደግሜ ላወሳ እወዳለሁ። ፍርሃቱን የፈጠሩት "ጎበዞችም"፣ ሆኑ በፍርሃት የምርዱት 'አንበሶች' መሃል ያለው በእኩልነት መነጋገር  ያለምቻሉ የ"ነፃነት እጦት" ጣጣ መሆኑን ላፍታም ቢሆን ከቶ ልዘነጋው አልችልም። አንችልም።

ስለዚህ ምን ብናደርግ ይሻላል?  ኧረ ምን ብናደርግ ይሻለናል?....................................................! በኔ ግምት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ ሆኖ የማሰብ መብት እስኪከበር ድረስ ወይም የሃሳብ ሙሉ ነፃነት እስከሚከበር ድረስ ጋዜጠኞቹም ሆኑ ፀሐፍቱ ፍርጠጣውንና ስደቱን ጋብ አድርገን፣ በእውቀት ላይ በተመሰረተ ትችትና ሂስ ወደፊት መግፋት አለብን። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምና ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ እንደምያደርጉት ያለ፣ በአእምሮ ምርምር ላይ ፀንቶ የቆመና ከስሜታዊነት የራቀ  ሂስና ትችት ያለመታከት መታገል ያስፈልጋል።

በነፃነት የመፃፍና የመሄስ በሎም በነፃነት የማሰቡ 'ችሎታ' እንጂ "ችሮታ" አለመሆኑን ገዢዎቻችን በውድም ሆነ በግድ እስኪያምኑና እስከምያከብሩትም ድረስ፣ ትግሉ መቀጠል አለበት። አንዳንዴ ሳስበው፣ ትግሉ በአንድ የፈረደበት አንበሳና ባደፈጡ ተኩላዎች መካከል የሚደረግ ይመስለኛል። "ለዳኛም ዳኛ አለው ላንበሳም ተኩላ አለው" እንደሚባለው ተረት ነው። ተኩላዎቹ ያለምንም ጠንካራ ድርጅትና ማህበር፣ ጥላ-ከለላዬ ነው ወይም ናችው፣ የሚላቸው ሌሎች መከታዎች ሳይኖርው፣ ባውላላ ሜዳ ላይ የተገኘውን "አንበሳ" ጋዜጠኛ፣ ልብልቡን ማሳጣት ሥራ ሆኗል። የፖለቲካውና የስርዓቱ አይነትኛ መገለጫም ሆኗል። ስለሆንም፣ ያለፈቃድ ወይም ያለገደብ የማሰብ መብት፣ ተፈጥሮአዊና ሰብአዊ መብት እንጂ  ፖለቲካዊ መልክ ተላብሶ  መለዋወጥ የለበትም።

ተፈጥሮአዊና ሰብአዊ መብቶችን ተለዋዋጭና ሸውራራ ይሚያደርጉትን  ሁለት ነጥቦች እንደሚ ክተሉት  በጨረፍታ ላቅርባችው ፈልጌያልሁና አብረን እንዝለቅ። 

2ኛ.  ስለሰይጣናዊ ሥልጣን (ያልተገራ ሥልጣን)

ወደሁለትኛው ነጥቤ ላመራ ነው። በሃሳባችሁ አብራችሁኝ እየተግዋግዋዛችሁ እንደሆነ ላፍታም ቢሆን አልጠራጠርም። ለመሆኑ የፍትህ ጋዜጣም ሆነ የሌሎች ህትመት ውጤቶች ላይ ያሉት ትናጋሪዎች (ወይም አምደኞች) የማይደማመጡበት  ምክንያት ምንድነው? ከእውቀት መብዛት ጋር የተያያዘስ ይሆንዴ? አይመስለኝም። በዙዎቹ ስለአፄ ቴዎድሮስም ሆነ ስለጃፓን ስልጣኔ ሲያወሩ በ፩፱፵ዎቹ በ፩፱፶ዎቹና (in the 1940's and 1950's) ክቡር ከበደ ሚካኤልና ክቡር ተክለፃድቅ መኩሪያ ይፅፉት ከነበረው ፅሁፍ ጋር  ሲነፃፀር፣ በእጅጉ የሰዋሰው፣ ርዕሰ-ጉዳይን አብስሎና አዳውሮ ከማጠንጠንም አንፃር ቢሆን፣ ወደሁዋላ የሚሄዱ አይነቶች ናቸው። ለምን ሆኑ? ብሎ መጠየቅም የተገባ ነው። አንድ ሁለቱን ብቻ ላንሳ። ገጣሚው መንግስቱ ለማ እንዳሉት፣ "ወረቀትና እስክርቢቶ አገናኝቶ፣ የብእሩን አፍንጫ ማናፈጥ" መፃፍና የመፃፍ ችሎታ የሚመስላቸው ሰዎች፣ የሌሎችን ሃሳብ ለመቀበልም ሆነ ለመመርመር "በጄ" አይሉም። ሌላኛው መሰረቱ ደግሞ ከማን አንሼ ወይም "እኔ እበልጥ-እኔ እበልጥ" የሚለው ባዶ ፉክክር (ወይም ድንፋታም ሊባል ይችላል) ነው። በጋሽ መስፍን አማርኛም፣ ከባሕላዊው የስልጣን-ጥም የበላይንትን ለመቀዳጀት፣ ወይም ምስፍንናን ከመመኘት የመጣ ሾትላይ ነው። በምቀኝነትና በንፍገት አይን የሌሎችን አስተዋፅዖ እንክት አርጎ ከመብላት የመጣ ነው።

በተለይም፣ “ባልሽ ከባሌ ይበልጣልና ዱቄትሽን  አሟጠሽ ስጪኝ!” የሚሉ ይሉኝታ-ቢሶች እና ቅንጡ (ሰይጣናዊ) ባለስልጣኖች ባሉበት ሀገር፤ እንደምን አድርጎ በእኩልነት ለመነጋገር ይቻል ይሆን? ሰይጣኑ የእኩልነትን መንፈስ ገዝግዞ፣ የወንድማማችነትንና የመተማመኛን ቅን ልብ በጥርጣሬ ሰቅዞ ይዞ፤ እንደመፃጉዕ ሸክም ጫንቃችን ላይ ተኮፍሶ ቁልቁል እያስጎነበሰን፤ እንደምን አድርጎ በእኩልነት መንፈስ መናገርም ሆነ መነጋገር ይቻላል?

አያቴ፣ ነፍሳቸውን ይማረውና፤ ልጅ ሳለሁ መሬት በነፃ ተመርተው (እንደዛሬው ሊዝ፣ ኪራይ “ምንትስ” ሳይመጣብን በፊት)፣ አባቴም  ሌሎች አስራ አራት (14) የቀበሌ ቤት የተከራዩ አባወራዎች ባሉበት ግቢ ውስጥ በወታደር ደሞዙ ስድስት ቤተሰብ እያስተዳደረ ይኖር በነበረበት ጊዜ፤ እያንዳንዱም ተከራይ አባወራ በስሩ ቢያንስ አምስት-አምስት ቤተሰው ያስተዳድር ነበር፡፡ ሆኖም፣ ለዚህ ሁሉ ሰው (ማለቴ ለሰባ አምስት ሰዎች ገደማ) የነበረው መጸዳጃ ቤት፣ አንድ እንደነገሩ ባሮጌ ቆርቆሮ የተከለለ፣ ሸረሪት ያደራበት ባለሁለት ቀዳዳ ጉድጓድ ነበር፡፡ እንደነገርኳችሁ መግቢያ በሩ አንድ ብቻ ነው፡፡ ወንድና ወንድ (ወይም ሴትና ሴት) እንኳን አብሮ ለመግባት በጣም መቀራረብና “ፈስ ለማዳመጥም” መታመን ያስፈልግ ነበር፡፡ ጎን ለጎን ተቀምጦ በእኩልነት ለመጸዳዳት ብዙ ብዙ መስፈርቶች ነበሩበት፡፡ መስፈርቶቹ ሁሉ ቢሟሉ እንኳ፣ ኧረ ቀላል የማይባል የመንፈስ ጥንካሬን መቀዳጀት ይጠይቃል! አለበለዚያማ ወረፋ ጥበቃው እልህ አስጨራሽ ነበር፡፡

ታዲያን በአንድ የተረገመ ቀን፣ አብዮት የተባለው አብሮ-አደጌ፣ የእትዬ ሽታዬን የሰኔ ሰላሳ የፈጫሳ ቅንጬ ሰልቅጦ-ሰልቅጦ ሲያበቃ፣ ላይበሌና ታችበሌ አለቅጥ ያጣድፈው ጀመር፡፡ በዚያው ቅጽበትም አቶ ጎበዜ የተባለው አባወራ የመጸዳጃ ቤቱን ጉድጓድ አፍ በሞኖፖል ተጎልቶበታል፡፡ (ኧረ! ተሰይሞበታል ብንል ይሻላል!) ልጅ አብዮት ሆዬም ወደውስጥ ለመግባት ሲሞክር፣ አቶ ጎበዜ “እህህህ....ም፣ አሃሃሃ...ኡሁሁሁ” እያለ ጉሮሮውን ብቻ ይጠራርጋል፡፡ ቃላት አውጥቶ፣ “ሰው አለ” በማለት ፋንታ ገብስ ቅሞቅሞ እንደጠገበ ፈረስ “አህህህ....ም” ብቻ ሆነ፡፡ አብዮትም በሱሪው ላይ “እንትኑን” ሊለቀው ምንም አልቀረው ነበር፡፡ አብዮትም፣ “ኧረ ጉድ ልሆንልህ ነው፡፡ ፍጠንልኝ!” እያለ መለማመጥ ጀመረ፡፡ ከውስጥ ያለው ምላሽ ግን፣ “እህህህ....ም” ብቻ ቢሆንበት ጊዜ፣ ዝገታሙን የቆርቆሮ በር በርግዶት ገባ፡፡ አቶ ጎበዜ ታዲያ፣ “እንዴት የመጸዳጃ ቤት ቅርናታም ቀዳዳ ላይ የመቀመጥ ልዩ ስልጣኔ ተነካብኝ” ብሎ በእለቱ የተፈጠረው የቀለጠ ጠብ ዛሬ ድረስ ወከክ ብሎ ይታየኛል፡፡

ጎበዜ ተገሰለ፡፡ ሱሪውን እንኳ ከፍ ሳያደርግ፣ “ዱታ ነኝ!” አለ፡፡ “ጆቢራ ነኝ!”ም አለ፡፡ በሽንት ቤት ጉድጓድ ላይ፣ ሰገራና ሽንት ልዩ ማዓዛ ላይ ለፈለኩት ያህል ሰዓታት “የመቀመጥ ልዩ ስልጣኔን ተጋፋኸኝ! ደፈርከኝ!” አለ፡፡ ኧረ! ካልተማታሁም እያለ ተንጀላጀለ፡፡ አብዮትም ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ተስኖት ሱሪው ላይ “እንትኑን” ለቀቀው፡፡ በዚያች ቅፅበት፣ አብዮት ውርደቱን ውጦ ጭጭ ሲል፤ ጎበዜ ግን፣ “አሳየሁት! ወይም አስ..ንኩት!” በሚል ትምክህቱ፣ ተመፃደቀ፡፡

ከዚያን ቀን ጀምሮ፣ ጎበዜም “ጎበዝ ነኝ!” እንዳለ፤ የአብዮትም ታዳጊ ልብ እንደታበየ ቀረ፡፡ ሳስበው ታዲያ፣ እንደምን አድርገን በእኩልነት መንፈስ ልንተያይ እንደምንችል ግራ ይገባኛል፡፡ በውስጣችን ያደፈጠው ሰይጣናዊ ሰይጣን መቼ ከች እንደሚልና ዛሩ እንደሚገዝፍ ወይም አዶከቢሬው መቼ ከፍጡራንም ከግንቡም እንደሚያላትመው አይታወቅም፡፡

ኧረ ለመሆኑ፣ ሰገራ ቤት ድረስ ተከትሎ ጨዋነት የሚያሳጣን የከማን-አንሼ፣ የማነአክሎኝነት፣ የእኔ-እበልጥ፣ የእኔ-እበልጡ ነቀርሳ ባህላዊ መሰረቱ ያው ያልሰለጠነ-የሥልጣን ሰይጣን አይደለምን? ሰይጣኑ የሚጋተውን የጭዳ ደም እስከሚጨልጥ ድረስ፣ የሚሰለቅጠውን ምሱን እስከሚያኝክና ውጦ እስሚያገሳው ድረስ፣ እንደቆሰለ አውሬ እያቅነዘነዘው ነው፡፡ ይኼው ልክፍቱ እስከዛሬም ድረስ አልገራ ብሎ ለስንትና ስንት ዘመናት “ጉልቤ” ኆኖ የበላይና የበታች አድርጎን ያሸናል፡፡

3ኛ. ውይይት፣ ውድድርና ገንቢ ሂስ

የጥንት ግሪካዊያን ለዓለም ካበረከቷቸውና ካበደሯቸው እሴቶች መኻከል ሦስቱ፡- ውይይት (Dialogue)፣ ውድድር (Competition) እና ገንቢ ሂስ (Constructive Criticism) ናቸው፡፡ (እነዚህን ሦስት እሴቶች፣ አንባቢያን እንደድፍረት ካልተቆጠሩብኝ በቀር የሰላም፣ የእኩልነትና የመሠልጠን “ሰለስቱ ስላሴ” ልላቸው ይዳዳኛል፡፡) የግሪክ ሊቃውንት መንፈሳቸው ለጥያቄና መልስ (ውይይት) የተጋ፣ አዕምሮአቸው ለሂስና ለመማማር የተከፈተ፣ ቀልባቸውም ለማሸነፍም ኆነ ሽንፈትን በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ነበር፡፡ ይኼውም ጥረታቸው ከብኂልነትም ባሻገር ባህል ሆኖ፣ ዛሬ ድረስ የምዕራባውያኑ የአስተዳደር፣ የፖለቲካና የመገናኛ ብዙኃኖቻቸው የዕለት ከለት ግዴታ ሆኗል፡፡

ወደ እኛ ቤት (ማለቴ ወደ ጥቁሩ ሕዝብ ጓዳ፣ ካስፈለገም ወደ ኢትዮጵያ) ሲመጣም፣ ጥያቄና መልስ ጰራቅሊጦስን እንደመዳፈር፣ ሂስና አቃቂርም እንደመመቅኘት፣ የመንፈስ ቅናትና ለመወዳደር መጣጣርም ሀገርን እንደመክዳትና እንደሃጢያት ተቆጥሮ፣ በገዢዎች፣ በቀሳውስትና በሼኪዎችም እንደሚያስወግዝና እንደሚያስረግምም አይቻለሁ፡፡ በዚህ ዘመንም ቢሆን በብዙ አጥቢያዎችና መስጂዶች አካባቢ የተቀየረ ነገር አላይም፡፡ “ውጉዝ ከመአርዮስ!” ወይም “ከልቢ! ሼይጣንቲቲ!” ማስባሉን ሁላችንም የምንታዘበው ጉዳይ ነው፡፡ በእኩልነት መወያየትንና በነፃነት መተቸትን፣ ሲያስፈልግም በውድድር ማሸነፍንም ኆነ መሸነፍን ለመቀበል የበቃን የምንሆንበትን ጊዜ በኪነጥበቡ ያፍጥንልን፡፡ ዓሜን አያስፈልግም፡፡ በአካልም በመንፈስም መታገል ብቻ ነው ያለብን፡፡ የምን "ዓሜን-ዓሜን" ነው ደግሞ?! ፍቱኑ መድሃኒት፣ ትግል  ብቻ  ነው፣  ተዋህስያኑን  ጠራርጎ  የሚያጠፋቸው። 

በሌላ አርዕስተ-ጉዳይ እስከምንገናኝ ድረስ ቸሩን ሁሉ ይግጠማችሁ! ይግጠመን!......     
       


     



    

አስተያየቶች