ከመጠላለፍ፤… ወደ ጥሎ ማለፍ
(በሰሎሞን ተሰማ ጂ /ከአዲስ አበባ/) semnaworeq.blogspot.com
ዘመኑ፣ “ከመለፍለፍ ይልቅ፣ ዓይቶና መዝኖ ከቻሉም ጥሎ ማለፍ!” እያለ ይመስላል፡፡ ፈጣንና ስልታዊ የሆነን የማመዛዘን ክህሎትንም ጠይቋል፡፡ “ለፍልፎ-ከመጠለፍ፣ ፈጥኖ ዓይቶ፣ ፈጥኖ መዝኖ፣ ከዚያም ጥሎ ማለፍ ይሻላል!” ሲል፣ በፀጥተኛ አንደበቱ ይመክራል፡፡ ለአንዳንዶቹ ባይዋጥላቸውም፣ እንዲመለፍለፍና ማስለፍለፍ ሁሉ፣ ዓይቶም ማለፍ ከፍተኛ ክህሎት /ወይም skill/ ነው፡፡
በ1953ቱ የታህሳስ የመፈንቅለ መንግሥት ማግሥት፣ የገርማሜ ነዋይንና የሁለት ክብር - ዘበኛ ጓዶችን አስክሬን፣ ገነተ - ልዑል ቤተ መንግስት መውጫና መውረጃ ደረጃዎች ላይ አምጥተው እንደ ሹሮ ክክ አሳጧቸው፡፡ ግዳይ እነደጣሉ የተሰማቸው “የግርማዊ” ታማኞችም፣ እየፎከሩና እሸለሉ አስከሬኑን ሲዞሩትና ሲመቱት በህይነ-ህሊናችሁ አስተውሏቸው፡፡ ሶስት ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸውን የገደሉና ያስገደሉ ሌሎች የንጉሱ “ታማኝ ነን“ የሚሉ ኢትዮጵያንም፣ ያዙን-ልቀቁን እያሉ አስክሬኖቹን እየዞሩ ሲፎክሩና ሲሸልሉ ልብ አርጋችሁ እዩአቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያዊያን ላይ በግብዝነት መንፈስ ቢመፃደቁም ስሟቸው፡፡ “የጠቅል አሽከር!” ምንትስ እያሉ ነበር!…
ከአራት ወይም ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም፣ ግርማዊነታቸው (“ቀ.ኃ.ሥ”)፣ “የሞት ትራፊ” የሆኑትን አጀቢዎቻቸውን አስከትለው ወደ ደረጃዎቹ መጡ፡፡ ሶስቱን አስክሬኖች በጋራ፤ በተለይም፣ የገርማሜን አስክሬን በአርምሞ አዩት፡፡ ዓይናቸውንም ሳይነቅሉ ከአስር ደቂቃዎች በላይ፣ “የህሊና ፀሎት” ማድረስ በሚመስል አኳኋን አጤኑት፡፡ ምንም ቃል ሳይተነፍሱም ወደ ጽህፈት ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም፣ የሰማንያኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን በማስመልከት፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሠራጭ ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ላይ፣ ጋዜጠኛው እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፡፡ “ለመሆኑ ከጥቅሶች ሁሉ፣ የትኛውን ያደንቃሉ?” ግርማዊነታቸውም በዚያች በምናውቃት ለዛቸው፣ “እኛ” ሲሉ ጀመሩ፡፡ “እኛ፣ የዳንቴን ዓይቶ ማለፍ!” የምትለዋን ጥቅስ እጅግ እንወዳታለን፡፡ እንተገብራታለንም፡፡” ሲሉ ተደመጡ፡፡
እኔም ሆንኩ እናንተ፣ ስለንጉሱ ግለ-ሰብዕና እና ታሪክ አድናቆት ያለን ሁሉ፣ ከላይ ከጠቀስነው ትዕይንትና ቃለ-መጠይቅ ውስጥ የምንመዛቸው ሶስት ቁምነገሮች አሉን፡፡ እነርሱም፡- እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ናቸው፡፡ ንጉሱ፣ በሐረር ሚሲዬን ት/ት ቤት፣ በፈረሳይኛ ቋንቋ፣ ከፈረንሳይ በመጡ መምህራን ስር በመማራቸው፣ የፈረንሳይኛ ቋንቋና የፍራንሴስ ዳንቴንም ተውኔቶችና መጽሐፍት ጠንቅቀው ያውቋችዋል፡፡ ሁለተኛ አራቱንም የቋንቋ ክህሎቶች (በፈረንሳይኛ መናገር፣ ማዳመጥ፣ ማንበብና መፃፍንም) ይችሉ ነበር፡፡ ሶስተኛም፣ ያወቁትንና የተካኑትንም ከራሳቸው አስተዳደግ፣ አካባቢና ባህል ጋር ኣዎንታዊ በሆነ ሥልት የማዛመድ አመለካከትን አዳበሩ፡፡ ስለዚህም፣ “ዓይቶ ማለፍ፣” የሚለውን እውቀታቸውን፣ በጽሞናና በጥልቀት የመመርመር ክህሎታቸው ጋር ተግብረውት ሲያበቁ፣ በኢትዮጵያዊ አስተዳደጋቸውና ባህላቸውም ለአስክሬን የሚሰጠውን ክብር ያለመንፈግ አመለካከት በተግባር አከናወኑ፡፡ ይህ ከሆነ እንግዲህ አርባ ዘጠኝ ዓመት ሞላው፡፡ ጃንሆይ የእውቀትን፣ የክህሎትንና የአመለካከትን አንድም ሶስትምነት ካስመሠከሩ ግማሽ ምዕተ-ዓመት ሊሞላው ወራት ብቻ ቀሩት፡፡
ሌላም ተያያዥ ጉዳይ እናንሳ፡፡ ርዕሳችንንም፣ “ከመጠላለፍ፣ ከመለፍለፍና ከማስለፍለፍ ወደ ዓይቶ ማለፍ” ደረጃ መቼና እንዴት ይሆን የምንደርሰው?” ወደሚል ቁጭት አዘል ጥያቄ ልታሻሽሉት ትችላላችሁ፡፡ ያሳደገን ቤተሰብ፣ ህብረተሰብና ባህል በብዙ ነገሮች ላይ እንድንቆጭ፣ ጢማችንንም አንድንቋጭ፣ ፀጉራችንንም እንድንነጭ፣ በትንሽ በትልቁም እንድንበሳጭ አድርገው አሳድገውናል፡፡ ስለዚህም አንድ የተበሳጨ ሰው ፀጉሩን እየነጨ፣ ወይም እየተወራጨ እንደሚበሳጭም ጭምር አስተምረው አሳድገውናል፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እንደዚያ እናደርጋለን፡፡ ጢማችንን እየቋጨን በብስጭቱ መንሥኤ ላይም እንድንቆጭ ወይም እንድንነጫነጭ የብድር አመላለስ ክህሎቱን ሳይቀር አሰልጥነውናል፡፡ ቀሪው እንግዲህ፣ በተበሳጨውና በተቆጨው ሰው አመለካከት ላይ የሚወሰን ነው፡፡ የሰውዬው አመለካከት ደግሞ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ በሆነ መንገድ ሊገለጥ ይችላል፡፡ ጃንሆይ አስክሬን ፊት ያሳዩት አመለካከት ዓዎንታዊ ነበር፡፡ እነዚያ ታማኞቻቸው ግን፣ ለሹመትና ለሽልማት “ቅልውጥ” ሲሉ፣ ግብዞች ሆኑ፡፡ “ግብዝነት” ደግሞ አንድ ሰው የፈለገውን ያህል እውቀትና ክህሎት ቢኖረው አሉታዊ አመለካከት ነው፡፡
ትንሽ ላብራራው፡፡ እውቀቱና ክህሎቱ ያላቸው ሰዎች አዎንታዊ አመለካከት ከሌላቸው፣ አጥፊ ይሆናሉ፡፡ ያሳደጋቸው ቤተሰብ፣ ህብረተሰብና ባሕልም ቀንደኛ ጠንቆች ይሆናሉ፡፡ አንድ ምሳሌ ላንሳ፡፡ በገቢዎች ሚኒስቴር ውስጥ በገቢ ግብር ውሳኔ ላይ የሚሰራ ባለሙያ፣ የፈለገውን ያህል ሰቃይ የ ”Tax Accounting” እውቀትና፣ የገቢ አወሳሰን ችሎታ ቢኖረው፣ ዘራፊና ገፋፊ አመለካከት ካለው የወጣለት “ሙሰኛ” ይሆናል፡፡ ሌላ ምሳሌ ልጥቀስ፣ ከህግ ትምህርት ቤት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀ፣ የከሳሽንና የተከሳሽንም ሙግት በአንክሮ የመከታተል ክህሎት ያለው ዳኛ፣ “ወንጀል ማየት ጠላሁ!” የሚል አመለካከትም ከያዘ፣ ማጣፊያው ያጣራል፡፡ የህግን የማረም፣ የማስተማርና የመቀጣጫ ማድረግ ፋይዳዎች በሙሉ ጨፍልቆ፣ “እከሌንና እከሊትን አይታችሁ ተቀጡ!” ወደሚል ቁልቁለት ይገፈትረዋል፡፡ (አደገኛ፣ በጣም አደገኛም አዝማሚያ በፍትህ ስረዓቱ ላይ ይፈጠራል፡)
ህዝብ በተሰበሰባቸው መድረኮችና አደባባዮች ላይ ተወዝፈው የሚለፈልፉና፣ መልሰውም ሕዝቡን የሚያስለፈልፉ ወገኖች አሉ፡፡ ሕዝቡ ከእያንዳንዱ መድረክና አደባባይ ጀርባ የሚደረገውን መጥለፍና መጠላለፍ ያውቃል፡፡ በከፍተኛ ጥንቃቄና ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ የሚደረጉትን ጠለፋዎችና ጠላፊዎች አብጠርጥሮ ያውቃል፡፡ በእግር ኳስ ጨዋታ ሜዳዎች ውስጥ ያሉት እንቅስቃሴዎች በተመለካቾችና በካሜራ ዓይኖች እንደሚታዩት ሁሉ ሀገራዊ እንቅስቃሴዎችንም ተመልካቹ ሕዝብ ያያል፡፡ ታሪክም፣ ያለምንም ፍርሃት “ቢጫ” ለሚገባው “ቢጫ”፣ “ቀይ”ም ለሚገባው “ቀዩን” እየሰጠ፣ የጨዋታው ማብቂያ ሲደርስ ፊሽካውን ይነፋል፡፡ ታሪክ ያለምንም ፍርሃት ፍርዱን ሰጥቶ፣ የጨዋታውም ፍፃሜ ሲደርስ፣ “የበቃችሁ!” ዋይታዊ ፊሽካውን ይነፋል፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን፣ የሚጠለፈው መጠለፉ፣ የሚመታውም መመታቱ፣ የሚሰበረውም ተሰብሮ በቃሬዛ መውጣቱም አይቀሬ ነው፡፡ ተጨዋቾቹ በፍርሃትም በብልሃት ተጫወቱም አልተጫወቱ፣ ዳኞዉ አቶ “ታሪክ” ያለማመንታት ይፈርዳሉ፡፡
(አንባቢያን ሆይ ጨዋታው ሜዳ ውስጥ ያለው ጣጣ የተጋጣሚዎቹና የአጫዋቹ ዳኛ ብቻ ነው እያልኳችሁ አለመሆኔን በታላቅ ጩኸት ላሳውቃችሁ እወዳለሁ፡፡)
የተከበሩ አንድ አንባቢ፣ “ ከመጋረጃው ጀርባ ያለውን መጠላለፍና መለፋለፍ፣ እንዴት አይቶና ሰምቶ፣ ጥሎስ ማለፍ ይቻላል?” የሚል “ጨዋ” ጥያቄ ሲጠይቁኝ ይሰማኛል፡፡ ልክ ብለዋል፡፡ ዙሪያችንን እግር ተወርች ታስሮ በሚጠላለፍና፣ ሆድ እያስባሰ በሚያስለፈልፍ ኑሮና የኑሮ ውድነት ተተብትበን ሳለ፣ አይቶና ሰምቶ፣ ጥሎም ማለፍ ይከብዳል፡፡ ኑሮ፣ ብዙዎቻችን እንደተሰነጠቀ ደወል፣ ለዛችንን አጥፍቶት፣ “ጥሎ ማለፍ” ይከብዳል፡፡ ሆኖም፣ “ጥሎ ማለፍ!” የምትለዋን ሀረግ፣ ለምን የግማሽና የሩብ ፍፃሜ እግርኳሳዊ መግለጫ ብቻ አድርጋችሁ ታነቡታላችሁ፡፡ ለፍፃሜ ወይም ለዋንጫ ለመብቃትም ሆነ፣ ዋንጫውን ለማንሳት “የግድ ጥሎ ማለፍ” ያስፈልጋል፡፡ “ጥሎ እንጂ አንጠልጥሎ ማለፍ!” አለማለቴን ልብ አርጉልኝ፡፡
በመጨረሻም፣ በጥሎ ማለፉ ጊዜ፣ አሸናፊውንም ሆነ ተሸናፊውን ቡድን ደግፋችሁ ስትተፉዙ የነበራችሁ ወገኖች፣ ውድድሩ እንደነበርና፣ የጨዋታውም ጊዜ ማብቃቱን እንዳትዘነጉ፡፡ በመሆኑም፣ የተጨዋቾቹንም ሆነ የተሸናፊውን ቡድን ደጋፊዎች “ክብረ-ነክ” በሆነ ፀያፍ ስድብና ማስፈራሪያ፣ ወይም ዛቻ እንዳትፈታተኗቸው፡፡ አዎንታዊ የጨዋታና የፉክክር አመለካከት እንዳታጡ እንመክራለን፡፡ ብትችሉ ግን፣ አይታችሁ ስታበቁ፣ እንዳለያችሁ ሆናችሁ “ጥላችሁ እለፉ!” ታሪክ አቧራውን አራግፎ የወደቀውን በጥንቃቄ ያነሳዋል፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡
-
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ
Thanks a lot for your comments.