“ተነሽ! ዓለም ተባብሮ የጨቆነሽ-ምስኪኒት!”

(እህህህ.....እስከ መቼ?!)
 (በሰሎሞን ተሰማ ጂ.) http://semnaworeq.blogspot.com   Email: solomontessemag@gmail.com


“ፖለቲካና ፖለቲከኞች” የተሰኘውን የአቤ ጉበኛ ተውኔት ካነበብኩት አስራ ስምንት ዓመታት አልፈውኛል፡፡ ፀሐይነሽ የምትባለው (አንዲት ካድሬ) እንደተልባ እየተንጣጣች የኢትዮጵያ ሴቶችን ችግር ስታራግብ ትታያለች፡፡ በገጽ-108 ላይ ወደ ጋዜጠኛው ጎርፉ በቁጣ ስሜት እንዲህ ትላለች፤ “ለመሆኑ እሷንስ ስለደረሰባት ሥቃይ ለምን አልጠየቅኻትም? በባህል፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በናት-ባባት፣ በባል-በወንድም፣ በአስተማሪ ስለተጨቆነችው ለምን አልጠየቅካትም?” እያለች ታፈጥበታለች፡፡ ከዚያም ከበደች ወደተባለችው ባለመጠጥ ቤት ዞራ፣ “ተነሽ! ጭፍልቂት-ተነሽ!...ተነሽ ብዝብዢት-ተነሽ!...ተነሽ ብርብሪት-ተነሽ! ተነሽ! ዓለም ተባብሮ የጨቆነሽ-ምስኪኒት ተነሽ! ተነሽ! ብርጭቆ አዳሪት-ተነሽ! ተነሽ! ገላ-አዳሪት....ተነሽ!” እያለች ባመረቀዘው የከበደች የሴተኛ አዳሪ ቁስል ላይ ግንድ-ግንድ የሚያካክል እንጨት ትሰገስግባታለች፡፡ (ላለፉት ምዕተ-ዓመታት፣ የኢትዮጵያን ሴቶች ከመደልልና ከማማለል የዘለለ፣ የረባ-ፋይዳ የከወነላቸው አንድም አገዛዝ አልነበረም! በመሆኑም፣ በዛሬው መጣጥፋችን ገዢዎቹ፣ ስለሴቶች ያላቸውን ምልከታ አጮልቀን ለማየት ጥረት እናደርጋልን፡፡) 

“ዘመን” የተሰኘው በ“ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት” እየታተመ የሚወጣው መጽሔት (ቁጥር 52፣ ነሐሴ 2005ዓ.ም) ዕትምን አነበብኩት፡፡ በዚህ መጽሔት ውስጥ ያሉት አምዶች ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱም፣ “አብይ ርዕስ”፣ “የዘመን እንግዳ”፣ እና ኪነ-ጥበብ የሚሉት ናቸው፡፡ “ቅንጭብጭብ” የተባለችም የገጽ ማሟያ አለችው፡፡ (“ዘመን” ሆዬ፣ “ዜና፣ ፖለቲካ፣ ታሪክ፣ ኢኮኖሚ፣ ምርምር፣ ስፖርትና የመሳሰሉት የሚሉት አምዶች ሆን ብላ ጠረማምሳቸዋለች፡፡) ነገሩ በዋናነት ከሰው ኃይል ጋር የተያያዘ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ በመጽሔቷ ውስጥ ያሉትን አምዶች በሙሉ (64 ገጾች ሁሉ) የጻፏቸውም ሦስት “ጎበዞች” ናቸው፡፡ (ለዚያውም ደግሞ በብዕር ስም የተጻፈ ካልሆነ ነው፡፡) ይህ አገዛዝ፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ ላይ ምን ያህል እያላገጠ እንደሆነም ያሳብቃል፡፡ (ብዙዎች ሲበርዳቸው እንደ አንሶላና ብርድልብስ የሚጠቀሙባቸው አሮጌው “አዲስ ዘመን” እና ታናሽ ወንድሙ “The Ethiopian Herald”ም ቢሆኑ፣ ብቃት ባለው የሰው ኃይል እጥረት ማኽል-አገዳቸው ደቆ፣ የውርስና የስራ ማስታወቂያ መመልከቻ ብቻ ሆነዋል፡፡)

ያም ሆኖ፣ ቁጥር 52ን የ“ዘመን” መጽሔት ሳነብ እጅግ አስደማሚ ቃለ-መጠይቆችን አነበብኩ፡፡ ቀዳሚዋ “የዘመን እንግዳ” ወ/ሮ ዘውዴ ዜናዊ ናቸው፡፡ ወንድማቸው አቶ መለስ “ምን ያህል ባተሌ እንደነበሩና እድሜ-ልካቸውን (እናታቸውና እህታቸውን እንኳን ማዋሪያ ጊዜ ሳይኖራቸው) ያለረፍት እዳለፉ” ነገሩን፡፡ ትንሽ ወረድ ብለው ደግሞ፣ ሟቹ ጠ/ሚኒስትር ምን ያህል ሩህሩህ አንጀትና ሰፍሳፋ ሆድ እንደነበራቸው በገደምዳሜ ነገሩን፡፡ “ዘመን” የቤት ጣጣ ለምን ሊነግረን እደፈለገ ትንሽ ተወዛግቤ ነበር፡፡ ነገሩ የገባኝ (ገጽ 25፣ 26፣ 35-37 እና 46-7) ላይ የወጣውን የወቅቱን “ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬን” ረጅም ቃለ-መጠይቅም ሳነብ ነው፡፡ ጠያቂው ደረጀ ትዕዛዙ እንዲህ ሲል ጭውውቱን ጀመረ፤ “ቀዳማዊ እመቤት ከሆኑ ወዲህ፣ እንዲህ ዓይነት ቃለ-መጠይቅ ሲያደርጉ የመጀመሪያዎት ነውን?” “አዎን!” አሉት ቀዳማዊቷ፡፡ “ዕድለኞች ነን ማለት እችላለኋ?!” ሲል ጥያቄውን አከለ፡፡ የቀዳማዊቷ መልስ ቀልድ አዘል ነበር፤ “በጣም!” የሚል በሳቅ የታጀበ፡፡...ዝቅ ብለው ስለጠ/ሚኒስትሩ ባህሪም ይጨዋወታሉ፡፡ ቀዳማዊቷ እመቤት እንዲህ ሲሉ ይጀምራሉ፤ “ኃይለማርያም ዋና ባህሪው ሩሀሩህና ቅን ነው፡፡ አንድ የተቸገረና የተጎሳቆለ ሰው ካየ በጣም ያዝናል፡፡ አቅሙ ከቻለም ከኪሱ አውጥቶ የሚሰጥ ርህራሄ ያለው ሰው ነው፡፡” እያሉ ስለባቤታቸው ያትታሉ (ገጽ-37)፡፡ (የ “ዘመኗ” አዘጋጅ ቀድማ የሰራችው ይሄንን ቃለ-መጠይቅ ነበር፡፡ ወ/ሮ ሮማን ስለባላቸው ባህሪ የሰጡት ምስክርነት ግን፣ የፕሬስ ድርጅት “ሰዎችን” አስደነበራቸው፡፡ ስለዚህም ሚዛናዊ ለማድረግ ሲሉ፣ የአቶ መለሰ ታናሽ እህትም ስለአቶ መለሰ ሩህሩህነትና ሰፍሳፋነት እንድትመሰክር አደረጓት፡፡... አንባቢ የሁለቱንም ሴቶች ጭውውት አንብቦ የራሱን ፍርድ ይስጥበት፡፡)  

ወደ ዋናው ጉዳዬ ለመግባት እጅግ ቋምጫለሁ፡፡ እኚሁ እመቤት የባላቸውን ባህሪ ከብዙ ሩህሩህ ሴቶች ባህሪ ጋር እያነጻጸሩ ለምን መግለጽ እንደፈለጉ የገባኝ ገጽ-36 እና 46 ላይ ያሉትን ሁለት ጥያዎች በቅጡ ሳጤናቸው ነው፡፡ ሁለቱም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከምንሊክ-ፀዐዳ ቤተ-መንግሥት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው “ጉድ” የሚወጣው፣ የቤተ-መንግስቱ ኑሮ ተመችቷቸው እንደሆነ ሲናገሩ ነው፡፡ “ለማንም ተመኝቼው አላውቅም፡፡ ....ሴቶች ጉዳይን ስናቋቁም ለስምንት ወራት ያህል ተመላልሼበታለሁ፡፡...እና ስገባ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተሰቦች መኖሪያ ማዶ-ማዶ እያየሁ አዝላቸው ነበር፡፡ ግን ለሰው አላወራም፡፡....” እያሉ ይቀጥላሉ፡፡ ዋናው ቁም-ነገር ያለው፣ እኚህ “ሴት” “የሴቶች ጉዳይ” ሲቋቋም ከግንባር ቀደሞቹ ተዋናዮች መካከል አንዷ እንደነበሩ መታወቁ ነው፡፡ በገጽ-46 ላይ ደግሞ ጠያቂው እንዲህ ይላቸዋል፡፡ “ወይዘሮ አዜብ በሴቶች ጉዳይ፣ በኤች አይ ቪ መከላከልና በሌሎችም ጌዳዮች የራሳቸውን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል፡፡...የእርስዎስ ተሳትፎ ምን ሊሆን ይችላል?” ወ/ሮ ሮማን እንዲህ ሲሉ መመለስ ጀመሩ፡፡ “እኔ እደሳቸው ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥመኛል ብዬ አልሰጋም፤ ምክንያቱም ከርሳቸው በፊት እንደዚህ የረባ እንቅስቃሴ ያደረጉ ቀዳማዊት እመቤቶች አልነበሩም፡፡” እያሉ ይቀጥላሉ፡፡ 

በወይዘሮዋ ንግግር ውስጥ በርካታ ጉንጭ-አልፋ ነገሮች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው ችግር፣ የግምታቸው ስታስቲካል ያለመሆን የሚያስከትለው ዳፋ ነው፡፡ በሙያቸው የኢኮኖሚክስ ምሩቅ ስለሆኑ፣ ስለናሙና አወሳሰድና ስለስታስቲክስ ለርሳቸው መንገር ማለት፣ ለቀባሪ እንደማርዳት ነው፡፡ ሁለተኛው ችግር ያለው ደግሞ፣ ጥያቄውን በጽሞና አለማዳመጣቸው ላይ ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች ጉዳይና የኤች.አይ.ቪ ጣጣ አሁንም ቢሆን ከማስጋትም አልፎ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ይህ ፈተና እያስቸገረና እየከፋ ባይሄድማ ኖሮ፣ ለምን የሰቶች ጉዳይን ለማቋቋም የተዋቀረው ግብረ-ሃይል ውስጥ ገብተው ተወኑ? ሌላም ሊታረም የሚገባው ስህተት አለ፡፡ እርሱም፣ “የቀዳማዊ እመቤት/First Lady” የሚባለውን ጽንሰ-ሃሳብ በተመለከተ ነው፡፡ እስከ የካቲት 9/1954 ዓ.ም (ማለትም እቴጌ መነን አስፋው እስካረፉበት ጊዜ ድረስ) ኢትዮጵያ እቴጌዎች እንጂ “ቀዳማዊ እመቤቶች ኖሯት አያውቅም፡፡ የጠ/ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ሚስትም ቢሆኑ፣ “ቀዳማዊ እመቤትነትን” ስማቸው ላይ ቀጽለው አልተገኙም፡፡ በኅዳር 5/1970 ኮሎኔል አጥናፉ አባተን ከረሸነ በኋላ ሚንሊክ-ፀዐዳ ዘው ብሎ የገባው የመንግሥቱ ኃ/ማርያም ሚስት፣ ጓድ ውባንቺ ቢሻውም ቢሆኑ አንድም ቀን “ቀዳማዊ እመቤት ነኝ” ብለው አያውቁም፡፡ ከአስር ዓመታት በላይ የደርግ መንግሥት ጠ/ሚኒስትር የነበሩት ሻምበል ፍቅረ ሥላሴም ሚስት “ቀዳማዊት እመቤትነትን” ጨርሶ አንስተውትም አያውቁም፡፡ እንኳን “የረባም” አሉት “ያልረባ” እቅስቃሴ ሊያደርጉ ቀርቶ፣ ጽንሰ-ሃሳቡንም ኮርጀውት አልተገኙም፡፡ የወ/ሮ አዜብም “ቀዳማዊ እመቤትነት” ጉዳይ ወሬ ሆኖ በመገናኛ ብዙኃን መለፈፍ የጀመረው ከ1998 ዓ.ም በኋላ ነው፡፡ (እንደምገምተው ከሆነም የቴዲ አፍሮን “ቴጌ...አህህ..እቴጌ” የሚለውን የ1997ዓ.ም ዜማ ተከትሎ የተቀየሰ ስልት ነው፡፡ (እንደወረደ ከፈረንጅ መኮረጅ!)

ስለ“ዘመን” መጽሔትና ስለ“ዘመን እንግዶች” ይሄንን ያህል ካልን ወደለጣቂው አንኳር-ርእሳችን እንመለስ፡፡ በኢትዮጵያ “ወጣቶችና ሴቶች ስም የሚቆመረውን የፖለቲካ ጨዋታ” በተመለከተ ያለኝን ሃይለ-ሃሳብ ለመግለጽ ነው፡፡ ከላይ ያነሳሁት ሀተታም ፋይዳው ወከክ ብሎ እንደሚታያችሁ አልጠራጠርም፡፡ በወ/ሮ ሮማን ተስፋዬና በአጋሮቻቸው አማካይነት ስምንት ወራት ያህል ፈጅቶ የተቋቋመው “የሴቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት ጉዳይ” የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሆኖ በ1998ዓ.ም ሹም ተሰጠው፡፡ በዚህም ወቅት፣ ወ/ሮ ሮማን የአንድ መምሪያ ኃላፊ ነበሩ፡፡ በዚህ መሥሪያ ቤትም አማካይነት በአፋጣኝ የተቋቋሙትን የ “የወጣትና የሴቶች ሊጎች” በበላይነት ይመሩ የነበሩት እርሳቸው ናቸው፡፡ የታሪክ አጋጠሚም ሆነና ባለፈው ቅዳሜ (ኅዳር 7/2006ዓ.ም) የተጀመረውን “የኢትዮጵያ ወጣቶችና የሴቶች ሊጎች ጉባኤ፣” ባለቤታቸው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በንግግር ከፈቱት፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ፣ ተሰብሳቢዎቹን ከኪራይ-ሰብሳቢነት፣ ከሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦቶችን ለማስወገደ የሚደረገውን ትግል “እንዲደግፉ” መመሪያ አስተላለፉላቸው፡፡ የጉባኤውን መዝጊያ ደግሞ፣ ም/ጠ/ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ተመሳሳይ ንግግር አድርገው በተኑት፡፡ በቀቀኖቹ ተሰብሳቢዎችም የተለመደችውን እንጀራ-ማብሰያቸውን ተገበሯት፡፡ “አዎን! አዎን! ዋነኛዎቹ ችግሮቻችን ኪራይ-ሰብሳቢነት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦቶች ናቸው፤” ብለው ወጡ፡፡ ይህ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ ከ“በቀቀን”ነትም አልፎ ወናፍነት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች የባህል፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የኤኮኖሚና የፆታ መድሎዎችን ሲሸከሙ ኖረዋል፤ እየተሸከሙም ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን አሲድ የሚደፋባቸው፣ ዐይኖቻቸው በስለት የሚወጉት፣ ፊቶቻቸው በሴንጢ የሚተለተሉት፣ የቤት ውስጥ ድብደባም የሚደርስባቸው ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ በትምህርት ቤቶች፣ በመስሪያ ቤቶቻቸው፣ በሚነግዱበት ስፍራና በሚጓጓዙባቸው መንገዶች ላይ ፆታዊ ጥቃት የሚፈፀምባቸው ምን ያህል እንደሆኑም ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ በንስሃ አባቶቻቸው፣ በፓስተሮቹና በሼኪዎቹ ተጽዕኖም ተገፋፍተው ያላለሙትን ኑሮ የሚኖሩት ስንቶቹ ይሆኑ? ቀላል ቁጥር እንደሌላቸው እንገምታለን፡፡ በወ/ሮ አዜብና በባለቤታቸው ፊታውራሪነት ተጠንስሶ፣ በእነወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ መሪ-ተዋናይነት የተቋቋመው “የሴቶች ጉዳይ”ም መሥሪያ ቤት በሴቶች ስም ምንያህል ዕርዳታና ብድር ከUNDP እና ከሌሎችም የዓለም-አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች እንደተቀበለ ይታወቃል፡፡ በአቶ ክፍሌ ወዳጆና በፕ/ር አንድሪያስ ጠንሳሽነት የተቋቋመው “የሴት ህግ ባለሙያዎች ማህበርም” ሆነ፣ ሙሉ ሰሎሞን ትመራው የነበረው “የሴት ደራሲያን ማህበር” እንዲሁም ሌሎች “ሴት-ሴት” እያሉ የሚያላዝኑት ቡድኖች የእንስቷን እግር ፈቀቅም እንዳላደረጉት የሚታወቅ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቷ ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ በማኅበር መደራጀት የተጀመረው በ1956ዓ.ም ነበር፡፡ ለነዚህ ማኅበራት መቋቋም ዋነኛ ምክንያቶች የነበሩት ሁለት ናቸው፡፡ 1ኛ) የ1956ቱ የሶማሊያ መንግሥት ወረራ ለመመከት ወደዖጋዴን ዘምተው በህይወት ሳይመለሱ የቀሩትን የጦሩ ባልደረቦች ሚስቶችና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የታለመ ነበር፡፡ የዚህ ማህበርም የበላይ ጠባቂ ልዕልት ተናኘ-ወርቅ ሲሆኑ፣ የማኅበሩ ሬዝዳንት ደግሞ ወ/ሮ ደስታ ገብሩ (የጀኔራል ከበደ ገብሬ ሚስት) ነበሩ፡፡ ማኅበሩ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁትን ህፃናትና ወጣቶች እጓለ-ማውታን (በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በአዲስ አበባ-ቀጨኔና ጉለሌ ላይ) ከፍቶ ከማስተማሩም በላይ፣ አቅሙ በፈቀደ መጠን ወደውጭ አገርም ልኮ ወጣቶችን ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፣ እ.አ.አ በ1950ዎቹ የተጀመረው የ“እንስቷ እንቅስቃሴ/The Feminist Movement” ነው፡፡ ይህ የ“እንስቷ” የመብትና የእኩልነት እንቅስቃሴ አውሎ-ንፋስ ውጪ አገር ተምረው በመጡት ኢትዮጵያዊያት በኩል በኢትዮጵያ ከተሞች አካባቢም መንፈስ ጀምሮ ነበር፡፡ 

የ“እንስቷ እንቅስቃሴ” በብዙ መልኩ ማርክሲስት ነው፡፡ የካርል ማርክስን የጨቋኝ-ተጨቋኝ አስተምህሮት ተከትሎ፣ ሴቶች ከጨቋኝ ወንዶች ተጽዕኖ በኃይል ነፃ-መውጣት አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ የማርክስን እሳቤም ተመርኩዞ፣ ሴቶች ለዘመናት ሲበዘበዙና ሲቦጠቦጡ ስለኖሩ፣ አሁን ለእኩልነት መነሳት አለባቸው ይላል፡፡ ስለሆነም፣ የዚህ ንቅናቄ መሪዎችና ደቀ-መዛሙርቶቻቸው ባል አያገቡም፡፡ ርስ-በርሳቸውም ወሲብ እስከመፈጸምና እስከመጋባት የሚደርስ መብት እንዳላቸው ያምናሉ፡፡ (ጌጡ አየለ ወይም “ቱቱዬ-ቱታዬ” በ1973ዓ.ም “አብዮት ጥበቃዋ ሚስቴ፣ በካራቴ በጁዶ እያለች” ቁም-ስቅሌን አሳየችኝ ያለው፣ ከዚህ የ“እንስቷ” ከልክ-ያለፈ የእኩልነት አዝማሚያ ነው፡፡ ከነሐሴ 1972ዓ.ም ጀምሮም የተጠነሰሰው የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር (አኢሴማ)፣ ዋነኛ አላማው ሴቶችን ከወንዶች እኩል ማድረግ ነበር፡፡ ሆኖም፣ የኢሠፓአኮ ምስረታን ለማሳካትና የእናት ሀገር ጥሪን እውን ለማድረግ በሚል ሰበብ ሴቶች የዘማች-ወንዶችን በሶና ቋንጣ ማዘጋጀት ሆነ፡፡ አኢሴማ፣ አስር አመት ሙሉ፣ ለኢትዮጵያ ሴቶች የረባም-ፋይዳ ሳይከውን በግንቦት 1983ዓ.ም ግብዓተ-መሬቱ  ተፈፀመ፡፡ በዘመነ-ደርግ የሴቶችን ጉዳይ ደርቦ ይሠራ የነበረው የከተማ ነዋሪዎች ማኅበርና የከተማ ልማት ሚኒስቴር ነበር፡፡ ከ1975ዓ.ም በኋላ ደግሞ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቅሎት ነበር፡፡ 

በደርግ መንግሥት እግር የተተካው የወያኔ መንግሥትም የሴቶችን ጉዳይ በፓርቲ ፕሮግራሙ ላይ ቢያካትተውም ቅሉ፣ እስከ 1998ዓ.ም ድረስ ለሴቶች የተለየ ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተል የሚኒስቴር መስሪያ ቤት አላቋቋመም ነበር፡፡ እስከ1997ዓ.ም ድረስም የሴቶች ጉዳይ ከደርግ የተለየ አደረጃጀት ቢኖረው እንኳን፣ ማኅበር የሚለው አደረጃጀት ተቀይሮ ፎረም መባሉ ነው፡፡ የፎረሙም መሪ ታጋይ ጥጉ የተባለች የሕወሃት የበረሃ ታጋይ ነበረች፡፡ ከ1998ዓ.ም በኋላ ግን ወደ ሊግ ደረጃ አደገ፡፡ (ውድ አንባቢያን፣ ማኅበር ማለት የግለሰቦች ስብስብ ሲሆን፤ የማኅበራት ስብስብ ደግሞ ፎረም ይሆናል፡፡ የተለያዩ ፎረሞች በአንድ ላይ አብረው ደግሞ፣ ሊግ የሚባል አደረጃጀትን ይፈጥራሉ፡፡ የወያኔ መንግሥት አንዴ ማኅበር፣ ሌላጊዜ ደግሞ ፎረም፣ ቆየት ብሎም ሊግ እያለ የአደረጃጀት ስያሜውንና የወር-ተረኛ ሹማምንቱን እንደሸሚዝ ቀያየራቸው እንጂ፣ ለሴቷ የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ አኗኗር መሻሻል ለውጥ ያመጣ እርባና አላመጣም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አቶ መለስ ይመሩት በነበረው የኢህአዲግ ማዕከላዊ ኮሚቴ (37 አባላት ያሉት ነው፣) ሴቶች የተወከሉት በአንዲት ሴት ነበረ፡፡ (እርሳቸውም፣ የአቶ መለስ ሚስት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ብቻ ነበሩ፡፡ ከ2005 ወዲህ ግን ከህወሃትና ከኦህዴድ አንድ አንድ ሴቶች ተጨምረውላቸው፣ የኢህአዲግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሴቶች ቁጥር ሦስት ደርሷል፡፡) በተመሳሳይ መልኩ፣ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያለውን የሴቶች መቀመጫ ቁጥር ብንወስደው፣ ድልድሉ 1 ሴት፡22.3 ወንዶች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ታዲያ! ቀዳማዊ እመቤቶቻችን (ወ/ሮ አዜብም ሆኑ ወ/ሮ ሮማን) የሚያሰጋ ችግር የለብንም፣ የሴቷ/የ“እንስቷ” ኑሮ ተሻሽሏል ብለው አርፈው ሊቀመጡ የሚችሉ ይመስላችኋልን፡፡ መልሱን ለእናንተ ለአንባቢዎቼ ትቼዋለሁ፡፡ (በቸር እንሰንብት)   (አዲስጉዳይ-ቅዳሜ ቅጽ7 ቁጥር 191 ኀዳር 14 2006)

  

አስተያየቶች