ዓባይና የዲሞክራሲ አባዮች! (ሊያነቡት የሚገባ)
የአፄ
ምኒልክ የጦር ምኒስትር የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) እጅግ በጣም መለኛ (ዘዴኛ) እንደነበሩ ያልሰማ
ማን አለ? የፊታውራሪውን የሕይወት ታሪክ የፃፉት
ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ስለአባ መላ የሚያስገር የዲፕሎማሲ ክህሎቶችና
የሚያስደንቁ የፍርድ አሰጣጥ ችሎታዎች በሰፊው ይነግሩናል፡፡ ከሁሉም-ከሁሉም የመሠጠኝ ግን፣ የእንግሊዙ ቆንስል በሱዳን በኩል
ባለው ድንበራችን በኩል ያለኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ዘልቀው የገቡ የእንግሊዝ ዜጎች ተገለውብናልና፣ እነርሱ የሞቱበት መሬት
በደም ካሳነት ለእንግሊዝ ይገባታል ሲል ጠየቀ፡፡ ጥያቄው የቀረበላቸውም አፄ ምኒልክ፣ “መክረን እንነግርሃለን!” ብለው ከሸኙት
በኋላ፣ የጦር ምኒስትራቸውን አባ መላን አስጠሯቸው፡፡ ሀብቴ እንዲህ አሉ፤ “ጃንሆይ! እነዚህ እንግሊዞች በምን ምክንያት
እንደተገደሉ ለመጠየቅና ለመረዳት ስለምፈልግ፣ ቆንስሉን ወደኔ ዘንድ ይላኩት፡፡” አፄ ምኒልክም ለቆንስሉ ላኩበት፤ “የጦር
ምኒስትራችንን ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስን ሄደህ አነጋግር!” አሉት፡፡ እያመነታ ሄደ፡፡ ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ጋር
እንደተገናኙ፣ ቆንስሉ አቤቱታውን አሰማ፡፡ “ሰዎቻችን ያለአግባብ ተገድለውብናል፤ ደማቸው የፈሰሰበት መሬት በደም ካሳነት
ይሠጠን!” አላቸው፡፡ አባ መላም ተጨማሪ ጥያቄ አቀረቡለት፤ “ለመሆኑ በናንተ አገር ይኼንን መሳይ ደንብ (ሕግ) አለወይ?”
ብለው ጠየቁት፡፡ አዎን አላቸው፡፡ አባ መላ ቀጠሉ፣ “እንግዲያውስ እኛም የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ዓለማየሁ ከኢትዮጵያ ሄዶ
በሀገራችሁ ተገድሎብናልና ለእኛም ሎንዶንን ስጡንና ከጣና ጀምሮ ያለውን መሬታችን ውሰዱት!” አሉት፡፡ የውል ሰነድም አርቅቀው
አዘጋጅተው ኖሮ፣ “ና ፈርም!” አሉት፡፡ ሰውዬውም “አልፈርምም!” ብሎ ተመናጭቆ ሄደ! (ታደሰ ዘወልዴ፣ 1997፣ ገጽ-106
እና 120)፡፡
በዓባይ
ጉዳይ ላይ ዘዴኛና መለኛ የዲፕሎማሲ አካሄድ የሚያውቅ (አባ መላ) ጠፍቶ በዲፕሎማሲያዊ አሰጥ-እገባ ውስጥ ከገባን
ሰነባብተናል፡፡ ጉዳዩ ከፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሙርሲ ከስልጣን መውጣትና መውረድ ጋር ለማያያዝ የሚሞክሩ ወገኖችም አሉ፡፡ በተለይም
በገዢው ፓርቲ አካባቢ ያለው ግንዛቤ ይኼው ነው፡፡ የኮሚንኬሽን ሚኒስትሩና ሚኒስትር ዲኤታው መግለጫዎች በዚሁ መሠረተ ሃሳብ
ላይ የተመረኮዙ ነበሩ፡፡ የውኃ ሀብት ሚኒስትሩም ቢሆኑ ከዚህ የተለየ አቋምና ሙያዊ አመለካከት ሲሰጡ አልታዩም፡፡ ከዚህ
ይልቅ፣ የአደባባዩን በጆሮ የሚባል ዓይነት ዲስኩር አሰሙን፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ቢሆን የተለየ መረጃ ለማቅረብ
አልቻሉም፡፡ ባጠቃላይ፣ የወያኔ/ኢህአዴግ መንግሥት ባለሥልጣናት በጅምላ ዋናውን ድክመታቸውን ለማለባበስ ተሯሯጡ፡፡ ይህም
ድክመት ከፍተኛ ኪሳራን የሚያስከትልና ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ ሲነገራቸው ደግሞ፣ በተለመደው ዘዴያቸው የብስጭትና
የተስፋ-መቁረጥ ስድባቸውን ያለገደብ ይለቁት ጀመር፡፡ በቅርቡ በሁለት ክፍሎች “በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት”
አማካይነት በተደረገው የፓርቲዎች ውይይት ላይ የኮሚንኬሽን ሚንስትሩን ያልተገራ ቋንቋና ድንፋታ ለተመለከተው ግልጽ ሆኗል፡፡
የወያኔ/ኢህአዲግ
መንግሥት ከዚህ ቀደም እንዳደረጋቸው ሁሉ ነገሮችን ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት ሸሽጎና ሰውሮ ለዓመታት አቆያቸው፡፡ ማቆየቱና
ምስጢር ማድረጉ ባልከፋ ነበር፡፡ ሚኒስትር ዲኤታው በፓርቲዎች ውይይት ላይ እንደነገሩን፣ “ከባዕዳን ጥቃትና ምቀኝነት ለመጠበቅ
ነው፤” ብለዋል፡፡ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮም፣ በፖርት ሱዳን በኩል “ለፕሮጀክት ኤክስ” እየተባለ ይገባ የነበረውን የግንባታ
ቁሳቁስና ጥሬ-ዕቃ እያወቅን-እንደማያቅ ለመሆንም የጣርነው ሀገራዊ ፋይዳውን በቅንነት በማሰብ ነበር፡፡ ከዚሁ የጥሬ-ዕቃ
ማስገባትና ከዝግጅቱም ጋር በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል የተዘጋጀውን ወሳኝ ጉዳይ ችላ አሉት፡፡ በተለይም “የናይል
ተፋሰስ አገሮች ውይይት” እየተባለ ይደረጉ የነበሩት ስብሰባዎች “የብቻ አቋም” ለመያዝ አስቸጋሪ መሆናቸው ቢታወቀም፣ ዋናው
አንጓ ጉዳይ ቸለል ተባለ፡፡ ይህም ችግር፣ የዲፕሎማሲያዊ ጡንቻን በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር ነው፡፡ (ሥልጣናቸው አልባረክልህም
ያላቸው፣ ፕሬዝዳንት ሙርሲና የካቢኔ አባሎቻቸው ከሦስት ሳምንት በፊት፣ በኢትዮጵያ በኩል በቂ የዲፕሎማሲያዊ ሥራ አለመሰራቱን
ይፋ አደረጉት፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ነገሩ ፈር ለመያዝ የቻለው፣ የሁለቱ አገሮች የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሁለትዮሽ ዝግ ስብሰባ
ካደረጉ በኋላ ይመስላል፡፡ እርሱም ቡሆን ሁለቱም አገሮች ሃይለ-ቃላትን ላለመጠቀምና ጠብ-አጫሪ ቅስቀሳዎችን ላለማድረግ ነው፡፡
ከበቂ በታች ነው፤ እጅግ-እጅግ ከበቂ በታች!)
የዛሬን
አያድርገውና፣ እ.አ.አ. በ1952 ዓ.ም ግብፅ “የታላቁን
ግድብ” (The Highest Dam) ግንባታ ፕሮጀክቷን ተግባራዊ ለማድረግ ስትወጥን ሱዳን ትልቋ ደንቃራ ነበረች፡፡ ሁኔታውን
አስመልክቶ አይ.ኤች. አብዳላ (I. H. Abdalla) በ1963 ዓ.ም እንደፃፈው ከሆነ፣ “ታላቁ የግብፅ
ግድብ” እ.አ.አ እስከ 1952 ድረስ ምስጢራዊ ስሙ “ፕሮጀክት ዜድ” ነበር፡፡ ግብፅ ለሱዳን ስለፕሮጀክቱ ዝርዝር ማብራሪያ
የሠጠችው ከስንትና ስንት ውትወታ በኋላ በ1954 እ.አ.አ ነው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ፣ ውኃው የሚጠራቀምበት ሥፍራ “ዋዲ
ሃልፋ” የተባለው የሱዳን አስተዳደር ግዛት ላይ ስለነበረ፣ ከሥፍራው ለሚፈናቀሉት ሱዳናዊያን የሚከፈለው የሠላሳ ሚሊዮን ፓውንድ
ካሳ ጉዳይ ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ የሱዳን የውኃ ዘርፍ ባለሙያዎች ከአንድ ታላቅ ግድብ ይልቅ በርካታ አነስተኛ መጠን ያላቸው
ግድቦች ለምን አይገነቡም ሲሉ ተቃውመው ነበር፡፡ በሁለት ምክንያቶች ነበር፡፡ 1ኛ. ሱዳንንና ግብፅን የሚጠይቀው አነስተኛ
ገንዘብ ነው ከማለታቸው ሌላ፣ የሚገነባው ግድብ በደራሽ ጎርፍም እንዳይጎዳ ያደርገዋል ሲሉ ነበር የተከራከሩት፡፡ 2ኛ.
የሚገደበው ውኃ በትነት ከሚባክን ይልቅ፣ ለምን የቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ ግድቡን አንሰራውም? “ምክንያቱም፣ በተፋሰሱ አገሮችም
መካከል የትብብር ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ ያስችለናልና!” ሲሉ ወሳኝ ሀሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ይህ የሱዳን
ተደራዳሪዎች ሃሳብ በካይሮ ባለሥልጣናት በኩል አልተወደደም ነበር፡፡ ካርቱም ጠንክራ፣ ግብፅ ለግድቡ መሥሪያ ብላ የጠየቀችውን
የብድርና የዕርዳታ ስምምነቶች ሁሉ ጥርቅም አድርጋ አዘጋችባት፡፡
እ.አ.አ
በ18 November 1958፣ ግብጽ በበዱላህ ከሊል የሚመራውን የሱዳን መንግሥት በጊዜው የጦሩ ኤታ-ማጆር-ሹም በነበረው
በጄኔራል ኢብራሂም አቡድ (Ibrahim 'Abbud) አስገልብጣ
የፖለቲካ መደላድሏን ሰራች፡፡ መፈንቅለ-መንግሥቱን፣ ፕሬዝዳንት ገማል አብደል ናስር ካይሮ ላይ አሲሮ፣ ካርቱም ላይ አሳካው፡፡
ከዚያ በኋላማ፣ የዲፕሎማሲያዊ መንገዱ ሁሉ ለካይሮ የተሳለጠ ሆነ፡፡ አልጋ-ባልጋ ሆነላት፡፡ ካይሮ በፊልድ ማርሻል አብዱል
ሃኪም አሚር አማካይነት፣ ግብፅ ከሶቪየት ኅብረት ጋር የ400 ሚሊዮን ሩብል ብድር አገኘች፡፡ የዓለም ባንክም የግብፅ መንግሥት
ለሚያስገነባው የታላቁ ግድብ ግንባታ ለማበደር ተስማማ፡፡ ሱዳን፣ ዶሮዋን በቆቅ ለውጣ ሮዚየርስ ግድብ የሚባል መናኛ ለመገደብ
ተስማማች፡፡ እ.አ.አ በኅዳር 1959 የተጀመረው የናይል ውኃ አጠቃቀም ስምምነት በወሩ (በታኅሣሥ 1959) ተፈረመ፡፡ ሱዳን
18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውኃ ለመጠቀም እጇን ተቆልምማ ተስማማች፡፡ ሴረኛዋም ግብፅ፣ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውኃ እንደልቧ
እንድትጠቀም ሆነላት፡፡ (ይህንን የውኃ አጠቃቀም ነው፣ ትነኩና ወየውላችሁ የምትለው፡፡)
ይህ
ስምምነት ለተፈረመ፣ ከ52 ዓመታት በኋላ ከላይ የጠቀስነውን “የናይል ተፋሰስ አገሮች ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነትን” አጀንዳው
ያደረገው የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ቻርተር በኢትዮጵያ አነሳሽነት ተረቀቀ፡፡ አዲሷ አገር ደቡብ ሱዳን ሳትቀር፣ የዚህን ውኃ
ፍትኃዊ ተጠቃሚነት በተመለከተ ድጋፏን ሰጠች፡፡ ይህንንም ተከትሎ፣ እ.አ.አ ከ1958ቱ የሱዳን መፈንቅለ-መንግሥት በፊት፣
ሱዳን ታራምደው የነበረውን አቋሟን አደሰች እንጂ፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጡንቻ አሳምኗት የፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነት ማዕቀፉን
አልደገፈችም፤ አትደግፍምም፡፡ ሱዳን ለዚህ ውሳኔዋ በቂ መነሻ አላት፡፡ ከደርግ ዘመን ጀምሮ፣ ደቡቡን ክፍል በኃይል
ያስገነጠለችባትና የጦር ስልጠና እየሰጠች፣ የኤስ.ኤን.ኤል.ፒን (SNLP) መሪዎች ሳይቀር ሀገረ-ገነት የነበረችውን ኢትዮጵያን
አታምናትም፡፡
ከዚህም
በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በሚጋሩት ረጅም የጋራ ድንበር የተነሳ ዐይንና ናጫ ናቸው፡፡ የመተማው የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ገና
አልተቋጨም፡፡ ስለሆነም፣ ሱዳን የኢትዮጵያን “የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ” በሰጥቶ-መቀበል መርህ መሠረት ትደግፈዋለች ብሎ
ለመቀበል ያዳግታል፡፡ ለሱዳን፣ እንኳን ጠንካራዋና ፈርጣማዋ ኢትዮጵያ ይቅርና ልፍስፍሷ ኢትዮጵያም ትልቅ ስጋት ናት፡፡ ለዚህም
ይመስላል፣ እ.አ.አ በ1954 ሱዳን፣ የውኃ ትነትን ለመከላከል
በሚል ሰበብ፣ ግድቡ ቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ ይገንባ ያለችው፡፡ ከዚህም ሌላ፣ በጃፋር ኑሜሪም ዘመን ሆነ በዑማር አልበሺር የአገዛዝ
ዘመኖች፣ ሱዳን የኢትዮጵያን አንድነት የሚደግፉትን መንግሥታት በመቃወም፣ የተገንጣዮችንና የተቃዋሚ ኃይሎችን በቀጥታም ሆነ
በገደምዳሜ ስትረዳ ነው የኖረችው፡፡ እስከ 1984 ዓ.ም ድረስም፣ ካርቱም ላይ ጽሕፈት ቤት ያልነበረው የተገንጣይ (የታጣቂ)
ቡድን አልነበረም፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ
Thanks a lot for your comments.